Print this page
Saturday, 12 January 2019 14:18

ባለፉት 2 ወራት በግጭት ሳቢያ የ256 ዜጐች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

 በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተፈጠሩ ግጭቶችና በተሰነዘሩ ጥቃቶች ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ 256  ዜጐች መገደላቸውን የሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሠመጉ) አስታወቀ፡፡
የተለያየ መነሻ ምክንያት ባላቸው ብሔር ተኮር ግጭቶች ሳቢያ የሰው ህይወት በከንቱ እየጠፋ መሆኑ እንዳሳሰበው የገለፀው ሠመጉ፤ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ክልሎችና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ውስጥ በህዳርና ታህሳስ 2011 ዓ.ም በተፈጠሩ  ግጭቶች 256 ሰዎች መገደላቸውንና በአስር ሺዎች መፈናቀላቸውን ጠቁሟል፡፡  
በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በጋሪና በቦረና ጐሣዎች መካከል ከህዳር ጀምሮ በተነሳ ግጭት ከ50 በላይ ዜጐች ህይወታቸውን አጥተዋል ያለው የሰመጉ ሪፖርት፤ ታህሳስ 8 ቀን 2011 በሞያሌ ከተማ በቀለ ሞላ ሆቴል ውስጥ በታጣቂዎች በተፈፀመ ጥቃት የ12 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ብሏል፡፡
በነቀምት፣ በነጆ፣ ጋሆ ቀቤ፣ በሀሮ ሊሙ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች ደግሞ ከ30 በላይ ሰዎች ህይወት ሲጠፋ፣ የጊቶ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ባልታወቀ አካል በነቀምቴ ከተማ ተገድለዋል፡፡ በዚሁ እለት ማለትም ታህሳስ 17 ቀን 2011 በነቀምቴ ከተማ ተጨማሪ ሁለት የፀጥታ ሃይሎች ተገድለዋል ብሏል- የሰመጉ ሪፖርት፡፡
ታህሳስ 10 ቀን 2011 በቦረና ዞን ተልተሌ ወረዳ በሚኖሩ የቡርጂና ኮንሶ ተወላጆች እንዲሁም የቦረና ተወላጆች መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለው ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ታህሳስ 13  ደግሞ በሶማሌ ክልልና ኦሮሚያ አዋሳኝ በሆኑት ሲቲ ዞንና ምስራቅ ሃረርጌ ዞን፣ የረር ጐታ አካባቢ በተፈጠረው ብሔር ተኮር ግጭት የ15 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡  
ህዳር 22 ቀን 2011 በወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ የታጠቁ የመንግስት ሃይሎች በተኮሱት ጥይት 15 ተማሪዎች ሲቆስሉ አንዱ ህይወቱ አልፏል ተብሏል፡፡ በአማራ ክልል ምዕራብ ጐንደር ዞን ከህዳር 22 ቀን 2011 ጀምሮ በጭልጋና በደንቢያ አካባቢዎች በአማራና በቅማንት ማህበረሰብ መካከል በተነሳ ግጭት የ50 ዜጐች ህይወት መጥፋቱን ሠመጉ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን፣ በንሣና ቦና ወረዳዎች “መሬታችን ለኢንቨስተር አላግባብ ተሰጥቷል” በሚል የተፈጠረ አለመግባባት፣ “በወረዳው ካቢኔ አንመራም” ወደሚል ተቃውሞ ተሸጋግሮ፣ ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በተቃውሞ ላይ የነበሩ 29 ሽማግሌዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ያመለከተው ሠመጉ፤ ይህን ክልል ከምዕራብ ጉጂ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ በተፈፀመ ጥቃትና ግጭት 35  ዜጐች ሞተዋል ብሏል፡፡
በጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት ደግሞ የ50 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ሪፖርቱ አመልክቷል። በትግራይ ክልል የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ፣ በጥቅምት ወር የ5 ዜጐች ህይወት ማለፉን፣ 761 የማህበረሰቡ ተወላጆች በመቀሌ፣ ማይጨው፣ ውቅሮ፣ ተንቤን በሚገኙ ወህኒ  ቤቶች ታስረው እንደሚገኙም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡  
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ ግጭት  የሟቾች ቁጥር በውል ባይታወቅም 1200 ያህል የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ በባህርዳር ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በድሬደዋ ከተማ በገንዳ ገራዳ፣ ገንዳ ቦዬ እንዲሁም ገንዳ ተስፋ የተባሉ አካባቢዎች ከህገ ወጥ የመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። በሌላ በኩል፤ በድሬደዋ ዙሪያ ቢራ በሚባል ቀበሌ 1 በኦሮሞና በሶማሌ ጐሣዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 12 ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን 4 ሰዎች በጥይት ቆስለው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል፡፡

Read 9201 times