Saturday, 12 January 2019 14:08

የፖሊስ ልብስ በመልበስ ዘረፋ የሚያካሂዱ ተበራክተዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የደንብ ልብስ በመልበስና የጦር መሳሪያ በመያዝ ዘረፋ የሚያካሂዱ የፖሊስ አባላት እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ስፍራዎች የደንብ ልብስ የለበሱና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የሆኑ ፖሊሶች፣ ግለሰቦችን በጦር መሳሪያ በማስፈራራትና በማስገደድ ዘረፋ እያካሄዱ መሆኑን ከፖሊስ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዘራፊዎቹ በተለያዩ ቀናትና በተለያዩ ስፍራዎች በመዘዋወር “ዶላር እንመነዝርላችኋለን”፣ በማለትና መንዛሪዎቹን በጦር መሳሪያ በማስገደድ፣ የያዙትን ዶላርና ሞባይል ስልክ ይዘው ይሰወራሉ ተብሏል፡፡
ከፖሊስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ታህሳስ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 አምስት የፌደራል የወንጀል መከላከል ፀጥታ ህግ ማስበር ዳይሬክቶሬት ቲም አዛዥ የሆኑና ሁለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ቦታው ሳሪስ አቦ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ አንድ ግለሰብን “ዶላር እንመንዝርልህ” በማለት ይዘውት ከገቡ በኋላ ለመመንዘር የያዘውን 160ሺ ብር በጦር መሳሪያ አስፈራርተው በመቀማት ላዳ ታክሲ ይዘው ከተሰወሩ በኋላ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት የሆኑ 5 ፖሊሶች ከአንዲት ወጣት “ዶላር እንመንዝርልሽ” በማለት 310 ሺ ብር እና ግምታቸው 16ሺ ብር የሆኑ ሁለት ሞባይሎችን በመሳሪያ አስፈራርተው በመቀማት ከተሰወሩ በኋላ በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በአራዳ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ራስ መኮንን አካባቢ በሚገኘው ኦይል ሊቢያ ነዳጅ ማደያ ውስጥ የማደያው ሰራተኛ የሆነውን ግለሰብ በስለት በመውጋትና እጅና እግሩን በገመድ በማሰር፣ ይዞት የነበረውን ከ55 ሺ ብር በላይ ዘርፈዋል የተባሉ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጃንሜዳ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት  አራት ተጠርጣሪዎችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በፖሊስ አባላት የሚፈፀመው ዘረፋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄዱን ያመለከተው የፖሊስ መረጃ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 22 አዲሱ ሰፈር አካባቢ በሚገኘው ሳንቶያዝ የመጠጥ ማከፋፈያ በተባለው ስፍራ ተጠርጣሪዎች የፖሊስ ታርጋ የለጠፈ አንድ ጋቢና ፒካፕ በመያዝ ወደ መጠጥ ማከፋፈያው መደብር ገብተው “ዶላር መንዝርልን” ብለው ከጠየቁ በኋላ ዶላር እንደማይመነዝር ሲነገራቸው “የፖሊስ አባላት ነን” በማለትና መታወቂያቸውን በማሳየት የድርጅቱን ባለቤት በካቴና አስረው፣ ካዝናውን እንዲከፍት ካደረጉት በኋላ በውስጡ የሚገኘውን 540ሺ ብር እና ግምቱ 50ሺ ብር የሚያወጣ ሞባይሉን በመውሰድ፣ “ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዘንህ እንሄዳለን” በማለት መኪና ውስጥ አስገብተውት፣ ወደ ሰዋራ ስፍራ ከወሰዱት በኋላ ከመኪናው አውርደው ጥለውት ተሰውረዋል፡፡
እነዚሁ ተከሳሾች በድጋሚ ቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው መብራት ኃይል በሚባል ቦታ ጥቅምት 7 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡20 አንድ ግለሰብ ሊፍት እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ ከገቡ በኋላ በመሳሪያ በማስፈራራት በሻርፕ አፍነው፣ ከመኪና ካስወረዱት በኋላ 28ሺ ብር፣ ላፕቶፕና መኪናውን ይዘው ተሰውረው ከአዳማ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሊያዙ እንደቻሉ ፖሊስ ጠቁሟል፡፡

Read 1743 times