Sunday, 06 January 2019 00:00

ከኢትዮጵያ ክለቦች የሊግ ኩባንያ በፊት…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሊግ ኩባንያን ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ልዩ ስብሰባ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ዘንድሮ በሊጉ በመሳተፍ ላይ ለሚገኙ 16 የኘሪሚየር ሊግ ክለቦችም ለስብሰባው እንዲዘጋጁ ጥሪ አድርጐላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ ላይ ፕሬሚዬር ሊግ ትልቁ የውድድር ደረጃ ነው፡፡ ውድድሩን በክለቦች የሊግ ኮሚቴ ለማስተዳደር ክለቦችና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በጠቅላላ ጉባኤዎች እና በተለያዩ የውይይት መድረኮች ያለፉትን 10 ዓመታት ዋና አጀንዳቸው እያደረጉ መክረውበታል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚም በየጊዜው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ  ቃል ሲገባ ቆይቷል፡፡ የኘሪሚየር ሊግ ክለቦች የሊግ ኩባንያ ምሥረታ ለማድረግ ምን ያህል እንደተዘጋጁ ለመገመት ያስቸግራል፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል ከክለቦቹ ጋር ስብሰባ ለማድረግ ቀጥሮውን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለክለቦች የሊግ ኩባንያን እንዲመሰርቱ ያቀረበው ጥሪ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማነቃቃት ይኖርበታል፡፡ የፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች፣ ደጋፊዎቻቸውና አመራራቸው በተለይ አጋጣሚውን በትኩረት መከታተል እና ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ የስፖርት አድማስ ዘገባ ከኢትዮጵያ ክለቦች የሊግ ኩባንያ ምስረታ በፊት ያሉትን ሁኔታዎች በአፍሪካ እግር ኳስ ካሉት ተመክሮዎች በማያያዝ የቀረበ ነው።
የሊጉ አበይት ምዕራፎች
በኢትዮጵያ በእግር ኳስ ክለቦች መካከል በተለያዩ ፎርማቶች ዓመታዊ ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ የወርቅ ኢዮቤልዩውን አልፏል፡፡ ይሁንና የክለቦች ከፍተኛ ውድድር የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሚል ስያሜ ሲከናወን ከ21 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ በ1990 ዓ.ም ላይ ፕሪሚየር ሊጉ  በክለቦች ፍላጎት የተመሰረተ ሳይሆን ፌዴሬሽኑ ክልሎችን በማሳተፍ ስፖርቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ባነገበው ዓላማ ነበር፡፡ ክለቦች ሊጉን ራሳቸው ለማስተዳደር የጠየቁት ውድድሩ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በሚል ስያሜ ከተመሰረተ ከ9 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በ1999 ዓ.ም ላይ የክለቦች የሊግ አስተዳደር በሚል በሊጉ የነበሩ ክለቦች ከፌደሬሽኑ በመገንጠል  ከብሔራዊ ሊጉ ተጨማሪ ክለቦችን አካተው በአበበ ቢቂላ ስታድየም የክለቦች ህብረት ዋንጫ በሚል ውድድር አዘጋጁ። ይህ እንቅስቃሴ ክለቦች ራሳቸው የሚያስተዳድሩትን ሊግ ለማቋቋም መቁረጣቸውን በይፋ ያስታወቁበት ነበር፡፡  ከዚያን ጊዜ ወዲህም ያለፉትን 12 ዓመታት በተደረጉ የፌደሬሽኑ መደበኛ ዓመታዊ ጉባኤዎች እንዲሁም በየ4 ዓመቱ በሚደረጉት የስራ አስፈጻሚ እና ፕሬዝዳንት ምርጫዎች የክለቦች የሊግ አስተዳደር የማይቀር አጀንዳ ሆኖ ቆይታል፡፡ ከዚህ ባሻገር በፕሪሚዬር ሊጉ ያለፉት 21 ዓመታት ጉዞ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሌሎች ምዕራፎችም አሉ፡፡
ከክለቦች ህብረት በኋላ በ2000 ዓም በኢትዮጵያ ሚሌንየም የተካሄደው  ውድድርም  በሚድሮክ ግሩፕ በ1.5 ሚልዮን ብር ስፖንሰር ተደርጎ ለመጀመርያ ጊዜ የስያሜ መብቱን የተሸጠበት መሆኑ አበይት ምዕራፍ ሆኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡   ከዚሁ የውድድር ዘመን ማግስት ግን ፌዴሬሽኑ የውድድሩን አስተዳደር መልሶ ተቆጣጥሮታል፡፡ ስለዚህም የክለቦች ሊግ አስተዳደር፤ ስፖንሰርሺፕ እና ሌሎች የንግድ ተስፋዎች ገና በማቆጥቆጥ ላይ ሆነው ተቀዛቀዙ። በ2002 ዓም ሊጉ በተጨዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ሂሳብ ማስመዝገብ የጀመረበት ሆኗል፡፡ በተለይ ደደቢት በወቅቱ ቡድኑን በሀገሪቱ ምርጥ የተባሉ ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ሻምፒዮን ለመሆን ሲበቃ  በተጨዋቾች የዝውውር ገበያው የፊርማ ክፍያ ሪኮርዶችን በመሰባበር ነበር፡፡ በ2003 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ13 አመታት ጥበቃ በኋላ የመጀመርያ የሊግ ቻምፒዮን መሆኑ የፕሪሚዬር ሊጉን ትኩረት በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቃ ነበር፡፡ በወቅቱ የሊጉ ጨዋታዎች የቀጥታ ቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የሚያገኝባቸው ፍንጮች ታይተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከፕሪምየር ሊጉ በታች የሚገኝ ሊግ  ሆኖ በመወሰኑ የሊጉ ደረጃው  ከፍ ብሏል፡፡  በከፍተኛ ሊጉ የሚደረጉ ጨዋታዎች ብዛት እና ለጉዞ የሚወጣው ወጪ ከፕሪምየር ሊጉ ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ክለቦችን እየተፈታተናቸው ይገኛል፡፡ በሊጉ መቆየት ያልቻሉ ክለቦች የመፍረስ አደጋ ውስጥ የገቡትም ይህን ተከትሎ ነው፡፡ ሊጉ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበት በመሆኑ ክለቦች ለፕሪምየር ሊግ ፉክክር ተዘጋጅተው እንዲመጡ ያደርጋቸዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡  ዳሽን ቢራ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ተከትሎ የፈረሰ የመጀመርያ ክለብ ሲሆን ከ1992 ጀምሮ በሊጉ የቆየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፈረሰውም በተመሳሳይ የውድድር ዘመን ነበር።
የሊግ ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ
የ2011 ፕሪሚየር ሊግ ላይ የአምናው ሻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር ፤ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ ኢትዮጵያ ቡና፤ መከላካያ፤ ፋሲል ከነማ፤ ባህር ዳር ከነማ፤ ደደቢት፤ መቐለ፤ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፤ ሽሬ እንዳስላሴ፤ አዳማ ከነማ፤ ሀዋሳ ከነማ፤ ወላይታ ድቻ፤ ሲዳማ ቡና፤ ደቡብ ፖሊስ እና ድሬዳዋ ከነማ ተሳታፊ ናቸው፡ ክለቦች ይህን የውድድር ዘመን ሲጀምሩ በየዓመቱ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የተጫዋች ክፍያና አጠቃላይ የበጀት ጫና ምክንያት አደጋ ውስጥ ገብተዋል፡፡ መንግሥት ለእግር ኳስ የሚመድበው በጀትና የተጫዋቾች ክፍያ ነባራዊውን ሁኔታ ያላገናዘበ፣ የክለቦች የፋይናንስ ሥርዓት የሌለበት፣ ዘመናዊ የእግር ኳስ አመራርና አደረጃጀት ያልተጠናከረበት ሁኔታ ውስጥ ሊጉ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአገሪቱ ሁሉም ክልሎች የሚወክሉና የከተማ ክለቦች እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት የተያዙ ክለቦች እየተወዳደሩ ናቸው። ብዙዎቹ ክለቦች ቋሚ ገቢ የሌላቸው ሲሆኑ ከከተማ አስተዳደሮችናበመንግስት  ተቋማት በቀጥታ በጀት የሚመደብላቸው ናቸው። የተጫዋቾች ዝውውርና ሌሎች ክፍያዎቻቸውም ከዚሁ በጀት ላይ የሚታሰብም ሲሆን የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች በየዓመቱ ከ30 እስከ 80 ሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የተጫዋቾች ዝውውር ገንዘብ በየዓመቱ እየናረና በዋጋም እያደገ ሲሆን ተጫዋቾች በአማካይ ከ50 እስከ 100 ሺ ብር በሚደርስ ወርሃዊ ደመወዝ ከአንዱ ክለብ ወደ ሌላኛው ክለብ እየተዘዋወሩ ይገኛሉ። ዘንድሮ በተጨዋቾች የዝውውር መስኮቱ አማካይ ገንዘብ 100ሺ ብር ሲሆን፤ አነስተኛው ደግሞ 25ሺ ብር ነው።  አንድ ክለብ በዓመቱ የሚያስፈርማቸውና ውላቸውን የሚያድስላቸው የውጭና የአገር ውስጥ ተጫዋቾች ከ10-12 እንደሆኑ ቢገመት ከ20ሚሊዮን ብር በተጨዋቾች ዝውውር ብቻ ክለቦች እያወጡ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል፡፡
በፕሪሚዬር ሊጉ ከሽልማት ገንዘብ ክለቦች የሚያገኙትን ድርሻ መጥቀስም ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ዋንጫውን ከማንሳት ባሻገር የወርቅ ሜዳልያ እና 150000 ብር ተሸላሚ የሚሆንበት ነው፡፡ 2ኛ ደረጃ የ100000 ብር እና የብር ሜዳለልያ ተሸላሚ  ፤ 3ኛ ደረጃ የ75000 ብር እነና የነሀስ ሜዳልያ ተሸላሚ ፤ የአመቱ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው የ25000 ብር ፤የአመቱ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ 25 ሺህ ብር ፤ የአመቱ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን የ25 ሺህ ብር እንዲሁም የአመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ የ15000 ብር ተሸላሚ ይሆኑበታል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛው የስፖርት ክንውን ሲሆን በኩባንያ ደረጃ ክለቡን በሊግ ኮሚቴ ለማስተዳደር በሽልማት ገንዘብ፤ በቴሌቭዥን ስርጭት፤ በስፖንሰርሺፕና ተያያዥ ንግዶች ያሉ ሁኔታዎች መጠናከር እና መነቃቃት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን እንዲሁም በተለያዩ ደረጃዎች የውድድር ዘመኑን ለጨረሱ ክለቦች እና ኮከብ ተጨዋቾች ከፍ ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥበት አቅጣጫም የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ መድረስ ተገቢ ይሆናል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በአገር ውስጥ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች እንዲሁም በድረገፆች ከፍተኛ ሽፋን እያገኘ ቢሆን በተለያዩ ሁኔታዎች የገቢ አቅሙን  ያሳደገ አይደለም፡፡ ስለዚህም በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ክለቦች ከተለያዩ ንግዶች የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች እና ከሽልማት ገንዘብ ተጠቃሚ አይደሉም፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በኩባንያ ደረጃ ተዋቅሮ በክለቦች የሊግ ኮሚቴ መመራት ሲጀምር አብይ ስፖንሰር አግኝቶ በውድድር ዘመኑ መግቢያ ለተወዳዳሪ ክለቦች እንደየደረጃቸው ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የሚገኘውን ዳጐስ ያለ ገቢ ሊያከፋፍላቸው ይችላል፡፡  የገቢ ምንጮች ደግሞ ከፕሪሚዬር ሊጉ የሽልማት ገንዘብ፤ ከጨዋታዎች ቀጥታ የቴሌቭዥን መብት፤ ከማሊያ እና ሌሎች የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች፤ ከስታድዬም የጨዋታ ገቢ እና ከተያያዥ ንግዶች የሚገኙ ናቸው፡፡  ስለዚህም ሊጉን በኩባንያ ደረጃ ለማስተዳደር ሲታሰብ ለሊጉ አብይ የስፖንሰር ሺፕ ውል በማግኘት ውድድሩን ለማንቀሳቀስ በጥናት ላይ የተመሠረተ ርምጃ መፈጠር አለበት፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች የትልልቅ ኩባንያዎችን፣ ባለሀብቶችና፣ የደጋፊዎችን ትኩረት የሚስቡበትን አሰራር በመፍጠር የገቢ አቅማቸውን ለማጠናከር መስራት አለባቸው፡፡
ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሊግ በምርጥ የውድድር ሂደቱ፤ በገቢው ጠንካራነት፤ በቴሌቭዥን ስርጭት ፤ በስታድዬም ተመልካች ብዛት እና ከደጋፊዎች ጋር ባለው መጠነ ሰፊ ትስስር ይለካል፡፡  በየውድድር ዘመኑ የሊጉ ፉክክርና የክለቦች ደረጃ  በፕሮፌሽናል አስተዳደር በተጠናክሮ መቀጠሉ የአገሪቱን እግር ኳስ ያግዛል፡፡ በተለያዩ አህጉራዊ ውድድሮች ክለቦች የሚኖራቸውን ተፎካካሪነት ያሳድጋል። የሊጉ በገቢ አቅም መጠናከር የብሔራዊ ቡደኑንም ውጤታማነት የሚደግፍ መሆኑም መታወቅ አለበት፡፡
የሊግ ኩባንያ በአፍሪካ
በአፍሪካ አህጉር በሚገኙ ከ50 በላይ አገራት ከፍተኛ የሊግ ውድድሮች  መካሄድ ከጀመሩ 50 እና ከዚያም በላይ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ የብዙዎቹ አገራት የሊግ ውድድሮች በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በሚያወጡ ክለቦች መካከል የሚካሄዱ ቢሆንም የአህጉሪቱ እግር ኳስ በፕሮፌሽናል አስተዳደር አለመመራቱ ትርፋማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። በገቢያቸው የተቀዛቀዙና ትርፋማ ያልሆኑት የአፍሪካ ሊጎች በሰሜን አሜሪካ፤ በኤሽያና በደቡብ አሜሪካ የሚካሄዱትን ፕሮፌሽናል ሊጎች በሚስተካከከል ደረጃ አለመገኘታቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡ በአፍሪካ  አህጉር እግር ኳስ ስፖርት በተወዳጅነት የሚስተካከለው ማጣቱ፤ የህዝብ ብዛት ከ1 ቢሊዮንን ማለፉ፤ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ተጨዋቾች እንደመብዛታቸው… እግር ኳስ በከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ  መካሄድ ነበረበት፡፡ የአፍሪካ ሊጎችና ተወዳዳሪ ክለቦቻቸው በስፖንሰርሺፕ ገቢያቸው የተጠናከሩ አይደሉም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች በየሊጎቹ ከፍተኛ የገቢ ምንጮች ዙርያ ምቹ እድሎችን በመፍጠር አይንቀሳቀሱም፡፡ ፌደሬሽኖች  በሊግ ውድድሮች ላይ ጣልቃ በመግባት፤ የስፖንሰርሺፕ እና ስፖርታዊ ንግዶችን በማያበረታቱ የአስተዳደር ስራዎች በመጠመድ በፕሮፌሽናል የሊግ አስተዳደር ሊገኝ የሚችለውን ከፍተኛ የገቢ አቅም የሚያደናቅፍ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በእግር ኳስ በተለይ በሊግ ደረጃ ለሚወዳደሩ ክለቦች ዋንኛ የገቢ ምንጮች የቴሌቭዥን ስርጭት  መብት፤ የሽልማት ገንዘብ እና ስፖንሰርሺፕ፤ የስታድዬም ትኬት ሽያጭ ገቢ እና የማልያና ሌሎች የስፖርት ቁሶች ንግዶች ናቸው፡፡ በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን ለማሳደግ በደጋፊዎች አያያዝ እና በስታድዬም ገቢ፤ በስፖንሰርሺፕ እና የስፖርት ንግዶች እንዲሁም በቴሌቭዥን ስርጭትና የሽያጭ መብት ፕሮፌሽናል የአስተዳደር አቅጣጫዎችን በመከተል መስራት ቢኖርባቸውም በዚህ ረገድ ብዙዎቹ አገራት የተራመዱ አይደሉም። የአህጉሪቱ ክለቦች ፕሮፌሽናል የንግድ እና የእድገት አቅጣጫዎችን ለመከተል እንቅፋት የሆነባቸው ብዙዎቹ በመንግስት ባለቤትነት ስር በመተዳደራቸው ሲሆን ከዚሁ አይነት አስተዳደር ወጥተው በባለሃብቶች፤ በባለአክሲዮኖች ድርሻ፤ በደጋፊዎች ኢንቨስትመንት በሚጠናከሩበት ዘመናዊ ስርዓት ለመግባት መቻላቸው ከፍተኛ ለውጥ የሚፈጥር ነበር፡፡
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ በስታድዬም የትኬት ሽያጭ ትርፍ ለማግኘት የሚያዳግት ሆኖም ቆይቷል፡፡ በዓለም ዙርያ ከክለቦች ዋንኛ የገቢ ምንጮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የስታድዬም ትኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ እንደሆነ ቢታወቅም በአፍሪካ ግን አልተቻለም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ሱፕር ስፖርት እንደዘገበው በአፍሪካ በአንድ የጨዋታ ቀን ትልቁ ገቢ ሆኖ የተመዘገበው በደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ በ1 ጨዋታ በአማካይ የሚገኘው 8ሺ ዶላር  ነው። በአፍሪካ እንኳንስ መደበኛ የአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ይቅርና የየአገራቱ ትልልቅ ክለቦች በአህጉራዊ ደረጃ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ስታድዬሞች ብዙ ተመልካች የማያገኙ ናቸው፡፡ አንዳንድ የስፖርት ትንታኔዎች ይህን የስታድዬም ድርቅ ከ280 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የቴሌቭዥን ስርጭት ከተጠመዱበት ባህላቸው ጋር ያያይዙታል፡፡ የአፍሪካ ሊጎች የውድድር ዘመናት እና የጨዋታ መርሃ ግብሮች ከአውሮፓ ሊጎች ጋር በተመሳሳይ ወቅት ተደራርበው መካሄዳቸው የስታድዬም ተመልካች ማሳጣቱንም ጎን ለጎን ይጠቅሳሉ፡፡
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ ሌላው አዝጋሚ ሁኔታ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ከሽያጭ መብት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዓለም እግር ኳስ የብሮድካስት ኩባንያዎች የስፖርቱ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እና ዋና  ባለድርሻ አካል እንደሆኑ ቢታወቅም የአፍሪካ ክለቦች በውስጥ የሊግ ውድድሮቻቸው እና በአፍሪካ ደረጃ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ሽያጭ መብት ጋር በተያያዘ ለሚገኙ ገቢዎች ትኩረት ሰጥተው ባለመስራታቸው ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የብሮድካስት ኩባንያዎች ከእግር ኳስ ሊጎች ጋር ሲተሳሰሩ ጨዋታዎች በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሽፋን በማግኘት ተደራሽነታቸው ይጨምራል፤ በስፖንሰርሺፕ የሚገኙ ውሎች ተጠናክረው ገቢዎች ይጨምራሉ፤ የተጨዋቾች፤ የክለቦችና የስፖንሰሮቻቸው ብራንድ በተሻለ ደረጃ ይተዋወቃሉ፡፡ የብሮድካስት ጣቢያዎች ከሊጎች ጋር በአጋርነት ለመስራት ሲዋዋሉ በቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት የግዢ ውል ፈፅመው ሲሆን ይህ ገቢም ለሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች በእኩልነት የሚካፈል በመሆኑ በስፖርቱ ያለውን የመዋዕለንዋይ እንቅስቃሴ ያሟሙቀዋል፡፡
የአፍሪካ ሊጎችና ስፖንሰርሺፕ
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ በተለይ በከፍተኛ የሊግ ውድድሮች በስፖንሰርሺፕ ያሉት እንቅስቃሴዎችና የሚገኙ ገቢዎች የተቀዛቀዙ ናቸው፡፡ እንደ አውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ባይሆን እንኳን በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የስፖርት ንግዶች ከሰሜን አሜሪካ እና ከኤሽያ አህጉራት ሊጎች አንጫር የአፍሪካ የእግር ኳስ ሊጎች ደረጃቸውን ማስተካከል አለመቻላቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በአፍሪካ በፕሮፌሽናል የሊግ አስተዳደራቸው፤ በስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴ በመጠናከራቸው፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እና በተሻሉ የገቢ ምንጮች በመደራጀታቸው የሚጠቀሱት የሰሜን፤ ምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት  ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ዞን በእግር ኳስ ሊጋቸው ፕሮፌሽናል አደረጃጀት፤ አህጉራዊ ውጤታማነት ከቅርብ ዓመት ወዲህ መሻሻል ያሳዩት ሊጎች ደግሞ በሱዳን፤ ኬንያ እና ታንዛኒያ የሚካሄዱት ናቸው፡፡ በተለይ በ3ቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ሊጎች በውድድር አብይ የስያሜ ስፖንሰር፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እና በማልያ እና ልዩ ልዩ የስፖንሰርሺፕ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ባለፉት 5 ዓመታት የታዩ አበረታች ተመክሮዎች በኢትዮጵያ ያን ያህል አለመሞከራቸው ተገቢ አይደለም፡፡
በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ የተባለው ነው፡፡ ይህ ሊግ በቲቪ ስርጭት፤ ከአብይ ስፖንሰር በሚያገኘው ገቢ፤ በክለብ ባለቤት ባለሃብቶች ብዛት፤ በከፍተኛ የተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ተመንና የደሞዝ ክፍያ ከአፍሪካ ሊጎች ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ አብሳ በደቡብ አፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ባንክ ሲሆን በሊጉ አብይ ስፖንሰርነት  ስያሜውን በመውሰዱ ለአምስት የውድድር ዘመናት የከፈለው 61 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ ደግሞ በሱፕር ስፖርት የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ በየዓመቱ 1.95 ሚሊዮን ዶላር የሚከፍልበት ውል ነበረው፡፡ የግብፁ ፕሪሚዬር ሊግ ከ2005 እኤአ ጀምሮ በቴሌኮም ኩባንያ ኢስሳላት ስፖንሰር ተደርጎ ነበር፡፡ የቱኒዚያው ሊግ ፕሮፊሲዮናሌ 1 በይፋ የስፖንሰርሺፕ የተገለፀ ባይሆንም ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ተጨዋቾችን በማስፈረም የአገሪቱ ክለቦች ከመታወቃቸውም በላይ በየስታድዬሞች ለደጋፊዎችእና ለስፖንሰሮች የተመቸ አሰራር በመኖሩ ተምሳሌት ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ የጋናው ፕሪሚዬር ሊግ ከ2008 ጀምሮ ለአምስት አመታት በናይጄርያዊ ባለቤትነት በተያዘ የምእራብ አፍሪካ ትልቁ የቴሌኮም ኩባንያ ግሎባኮም አብይ ስፖንሰርነት ሲካሄድ እስከ 23 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈፅሞበት ነበር፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ የየአገራቱ ሊጎች በአብይ እና የስያሜ ስፖንሰርሺፕ ያላቸውን የገቢ ደረጃና ቅደም ተከተል ነው፡፡
1. ደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬርሺፕ- 17 ሚሊዮን ዶላር
2. ናይጄርያ ግሎ ሊግ 4 ሚሊዮን ዶላር
3. ጋና ፈርስት ካፒታል ሊግ 2 ሚሊዮን ዶላር
4. ታንዛኒያ 2 ሚሊዮን ዶላር
5. ሞሮኮ ቦቶላ ሊግ 1.8 ሚሊዮን ዶላር
6 ካሜሮን ኤምቲኤን ሊግ 1.4 ሚሊዮን ዶላር
7. ቦትስዋና ቢ ሞባይል ሊግ 1.4 ሚሊዮን ዶላር
8. ዚምባቡዌ ካስትል ሊግ 1.2 ሚሊዮን ዶላር
9. አይቬሪኮስት ፕሪሚዬር ሊግ 1 ሚሊዮን ዶላር
10. ኬንያ ታስከር ሊግ 645,000 ዶላር
11. ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ ፕሪሚዬር ሊግ 523,000 ዶላር
12. ማላዊ ሊግ  454,000 ዶላር
13. ማሊ ኦሬንጅ ሊግ 450,000 ዶላር
14. ስዋዚላንድ ፕሪሚዬር ሊግ 140,000 ዶላር
15. ዛቢያ ኤምቲኤን ሊግ 83,000 ዶላር
የአፍሪካ ክለቦችና ባለሃብቶች
ቬንቹር አፍሪካ የተባለ መፅሄት ከዓመት በፊት ‹‹ሃብታም የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች በአፍሪካ›› በሚል ርእስ በአፍሪካ እግር ኳስ ኢንቨስት ያደረጉ ሚሊዬነሮችን ያስተዋወቀበት ዘገባ አቅርቦ ነበር። በዚሁ ዘገባ ላይ በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ  በባለቤትነት ብዙ ኢንቨስተሮች የሚገኙት በደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  በአፍሪካ  የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች ከሆኑ ባለሃብቶች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የደቡብ አፍሪካው ክለብ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ባለቤት ፓትሪስ ሞትሶፔ ናቸው። በፕላቲኒዬም እና በወርቅ ማዕድኖች ላይ የሚሰራው ‹‹አፍሪካን ሬንቦው ሚኒራልስ›› ኩባንያ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ፓትሪስ ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት እንዳላቸው ይገመታል። በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት በደቡብ አፍሪካው አንጋፋ ክለብ ካይዘርቺፍ ዩናይትድ 40 በመቶ ድርሻ ያላቸው ካይዘር ሞቱንግ ሲሆኑ በ1970 እኤአ ላይ ክለቡን የመሰረቱ ናቸው፡፡ ባላቸው የሃብት መጠን ከአፍሪካ ሃብታም የክለብ ባለቤቶች በ3ኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ነጋዴ እና ፖለቲከኛ የሆኑት የዲ. ሪፕብሊክ ኮንጎው ክለብ ቲፒ  ማዜምቤ ዋይስ ቻፑዌ ናቸው፡፡ የዲ.ሪ. ኮንጎዋ ካታንጋ ግዛት አገረ ገዢ የሆኑት ዋይስ ቻፑዌ 60 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል። በመጨረሻም በአፍሪካ ከሚገኙ ሃብታም የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች የሚጠቀሱት በደቡብ አፍሪካው ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከ1980 እኤአ ጀምሮ በፀሃፊነት ተነስተው እስከ ከፍተኛው ባለድርሻ ለመሆን የበቁት ኤርቪን ኮሆዛ ናቸው። በኦርላንዶ ፓይሬትስ ክለብ ባለቤትነታቸው ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረጉት ኤርቪን ኮሆዛ በ2010 እኤአ ደቡብ አፍሪካ  19ኛው የዓለም ዋንጫን ስታስተናግድ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የአፍሪካ ክለቦች፤ ሊጎችና ቴሌቭዥን
በአፍሪካ አግር ኳስ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት በተያያዘ የተሻሉ ሁኔታዎች የሚስተዋሉት በደቡብ እና በሰሜን አፍሪካ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ በታዋቂው የሱፕር ስፖርትቻናል ለደቡብ አፍሪካ፤ ኬንያ፤ አንጓላ፤ ዛምቢያ እና ናይጄርያ ለሚካሄዱ ሊጎች ሽፋን ይሰጣል፡፡ ሱፕር ስፖርት ከደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ ጋር በቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት ለ5 ዓመታት ሲዋዋል በ134 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ለናይጄርያ ለአምስት አመት 34 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለዛምቢያ በተመሳሳይ የውድድር ዘመናት  እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በመፈፀም ነው፡፡ ዚምባቡዌ፤ ኬንያ፤ አንጎላ፤ ጋና እና አቬሪኮስት ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ከሽያጭ መብት በተያያዘ በየዓመቱ ከሱፕር ስፖርት 1 ሚሊዮን ዶላር እየተከፈላቸው በእግር ኳስ ሊጋቸው ሰርተዋል፡፡ በነገራችን ላይ የጋና ፕሪሚዬር ሊግ በአሁኑ ወቅት ኦፕቲመም ሚዲያ ፕራይም በተባለ ተቋም የሊጉ ጨዋታዎች በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት እና የተደራጁ ዘገባዎች የሚሰሩለት ሲሆን በየዓመቱ 90ሺ ዶላር በሚከፈልበት የስፖንሰር ውል ነው። በሌላ በኩል የግብፅ ሊግ በአፍሪካ ልዩ የሚያደርገው በስታድዬም የትኬት ገቢ እና በቲቪ ስርጭት ከፍተኛ ሽፋን የሚያገኝ በመሆኑ ነው፡፡ የግብፅ  ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ እና ሌሎች የአገሪቱ ቻናሎች የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ሲሆን ይህም የሊጉን ገቢ በዓመት እስከ 1.3 ሚሊዮን ዶላር ያደርገዋል፡፡
ባለከፍተኛ ዋጋ የአፍሪካ ክለቦች በ2018
የአፍሪካ ክለቦች በ2018 እኤአ ባላቸው አጠቃላይ የዋጋ ተመን ከ1 እስከ 10 የሚሰጣቸው ደረጃ ከዚህ በታች እንደቀረበው ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ የሰሜን አፍሪካ እና የደቡብ አፍሪካ ክለቦች ከፍተኛ ውክልና እንዳላቸው ይስተዋላል፡፡
አልሃሊ ግብፅ 19.25 ሚሊዮን ዩሮ
ኤስፔራንስ ዴ ቱኒስ ቱኒዚያ 12.75
ክለብ አፍሪካን ቱኒዚያ11.80
ካይዘር ቺፍ ደቡብ አፍሪካ 10.48
ሜመሎዲ ሰንዳንስ ደቡብ አፍሪካ - 10.35
ዛማሌክ ግብፅ 10.3
ዩኤስኤም አልጀርስ አልጄርያ  9.65
ኤኤስ ሴቲፍ አልጄርያ 8.6
ራጃ ካዛብላንካ ሞሮኮ 8.13
ቲፒ ማዜምቤ ዲ ሪ ኮንጎ  7.7
የአፍሪካ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ተመን፤ ደሞዝና  ስደት በሚሊዮን ዩሮ
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ ከፍተኛ ደሞዝ ለተጨዋቾች የሚከፍሉት  በሰሜን፤ ምእራብ እና ደቡብ አፍሪካ የሚካሄዱ ሊጎች  ናቸው፡፡ በአልጀርያው ሊግ ፕሮፌስዮናሌ 1 በሚወዳደር ክለብ የሚሰለፍ ተጨዋች በአማካይ  በሳምንት 1334 ፓውንድ በዓመት 69375 ፓውንድ ደሞዝ ስለሚያገኝ ሊጉን ከፍተኛ ክፍያ በመፈፀም በአፍሪካ የአንደኝነቱን ደረጃ ያሰጠዋል፡፡  የደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ  በሳምንት 647 ፓውንድ  በዓመት 33659 ፓውንድ እንዲሁም የናይጀርያው ግሎ ፕሪሚዬር ሊግ  በሳምንት 130 ፓውንድ  በዓመት 6776 ፓውንድ ለአንድ ተጨዋች በአማካይ በመክፈል በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃዎች ይከተላሉ፡፡
የአፍሪካ የእግር ኳስ ክለቦች በገቢ አለመጠናከራቸው፤ የየሊጎቹ ትርፋማነት መቀዛቀዙ ለአገሪቱ ታዳጊ እና ወጣት የእግር ኳስ ትውልድ ስደት ምክንያት እንደሆነም ይገለፃል፡፡ በየአገራቱ በሚገኙ አካዳሚዎች በሚያፈሯቸው ታዳጊዎች እና የእግር ኳስ ትውልዶች ስደት ላይ አዝጋሚው የአፍሪካ የእግር ኳስ ገበያ በተዘዋዋሪ ብዙ ተፅእኖዎችን ፈጥሯል፡፡ የየአገሮቻቸው ክለቦች በሚከፍሏቸው ደሞዞች አነስተኛነት ወደተሻሉት የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መሄድ ያልቻሉ የአፍሪካ ታዳጊዎች ስደታቸው ወደ መካከለኛው ምስራቅ በተለይ ኳታር እና ዱባይ ወይንም ወደ ኤሽያ በተለይ ወደ ቻይና ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፉ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ፊፍፕሮ በ2016 በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ያለውን የተጨዋቾች የስራ ሁኔታ በዳሰሰበት ዓለም አቀፍ የቅጥር ሪፖርት፤ በአፍሪካ የእግር ኳስ ሊጎች በወር ከ1ሺ ዶላር በታች የሚያገኙ ተጨዋቾች 73.2 በመቶ እንደሆነ ከአፍሪካ ክለቦች 55 በመቶው ለተጨዋቾች ደሞዝ በወቅቱ እንደማይከፍሉ እና 15 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ክለቦች ተጨዋቾች ከክለባቸው የፈረሙት ኮንትራት እንደሌለ ማረጋገጥ ተችሏል።  ባንድ ወቅት ከዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ላይ በማተኮር በተሰራጨ መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው በመላው ዓለም በተለያዩ አገራት ሊጎች የተሰማሩ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ብዛት ከ4515 በላይ ነው፡፡ 596 ከናይጄርያ፤ 397 ከሴኔጋል፤ 370 ከኮትዲቯር 336 ከካሜሮን፤ 365 ከጋና ተሰድደው በዓለም እግር ኳስ የተሰራጩ ሲሆን ሞሮኮ፤ ኬፕቬርዴ፤ ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ማሊ፤ አልጄርያ እና ጊኒ ቢሳዎ ቢያንስ እያንዳንዳቸው ከ100 በላይ ተጨዋቾችን በስደት አጥተዋል። ከዚህ በታች የቀረበው የአፍሪካ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስብ ያላቸው አጠቃላይ የዋጋ ተመን መሰረት ከ1 እስከ 10 የሚኖራቸው ደረጃ ነው።
አል አሃሊ - ግብፅ - 19.25 ሚ. ዩሮ
ኤስፔራንስ - ቱኒዝያ - 12.75
ክለብ አፍሪካን - ቱኒዝያ - 11.8
ካይዘር ቺፍ - ደቡብ አፍሪካ - 10 .48
ሜመሎዲ ሰንዳውንስ - ደቡብ አፍሪካ - 10.35
ዛማሌክ - ግብኝ - 10.3
ዩ ኤስ ኤም አልጀርስ - አልጀርያ - 9.65
ኢ.ኤስ ሴቲፍ - ቱኒዝያ - 8.6
ራጃ ካዛብላንካ - ሞሮኮ - 8.13
ቲፒ ማዜምቤ - ዲ.ሪፕብሊክ ኮንጎ -7.3

Read 3002 times