Saturday, 26 May 2012 10:42

ኢቴቪ ተመልካችን ይቅርታ ያለመጠየቅ ችግር አለበት ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ሬዲዮ ፋናና ዛሚ የማስታወቂያ ግነትና የመረጃ ስህተት ይታይባቸዋል ተብሏል

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቴሌቭዥን ጣቢያው በዜና እወጃ ወቅት የተሳሳተ መረጃዎችን እንደሚያቀርብና በምስል አቀራረብ ላይም ችግር እንዳለበት ተገለፀ፡፡ ለተሰሩ ስህተቶች ተመልካችን ይቅርታ ያለመጠየቅ ችግር አለበትም ተብሏል፡፡የብሮድካስት ባለስልጣን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የዘጠኝ ወር የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው፣ ጣቢያው በሚያቀርባቸው የዜና እወጃዎች አንዳንድ የተሳሳቱ መረጃዎችን ከማቅረቡም በላይ በምስል አቀራረቡም ላይ ችግሮች ይታዩበታል በማለት ውጭ ሀገር ሰራተኞችን በህገወጥ መንገድ ስለሚያስቀጥሩ ደላሎች በቀረበ አንድ ፕሮግራም ላይ የታየውን የምስል አቀራረብ ችግር በምሳሌነት ጠቅሶዋል፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ በሪፖርቱ ላይ ከዘረዘራቸው ሌሎች የጣቢያው ችግሮች መካከል ወቅታዊ ያልሆኑና የተዛቡ መልእክቶችን ያዘሉ ማስታወቂያዎችን ማስተላለፍ፣ መረጃዎችን ከምስል ጋር አጣጥሞ አለማቅረብ፣ የሰዎችንና የድርጅቶችን ስም ሊጐዱ የሚችሉ ቃላቶችን መጠቀም፣ የሰዎችን ስምና ማዕረግ አዛብቶ ማቅረብ፣ ፕሮግራሞች ሳይተላለፍ ሲቀሩ ተመልካችን ይቅርታ አለመጠየቅ፣ ማስታወቂያዎች እየተላለፉ ዜና እየተላለፈ መሆኑን የሚያመለክት የዜና ሎጐ ማሳየት፣ ለስህተቱም ይቅርታ አለመጠየቅ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን ያላገናዘቡ ማስታወቂያዎች እንዲተላለፉ ማድረግና የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ከተደነገገው የጊዜ ፍጆታ በልጦ መተላለፍ የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡በ97.1 ሬዲዮ ጣቢያም ሚዛናዊ ያልሆኑ የድርጅቶችን መልካም ስምና ጥቅም የሚጐዱ ፕሮግራሞች እንዲሰራጭ ማድረግ፣ የሌላውን ምርት ወይም አገልግሎት የማጥላላት ወይም የማንኳሰስ አዝማሚያ የታየባቸው፣ ከሚመለከተው ባለስልጣን መ/ቤት የዕውቅና ፈቃድ ባልተገኘበት ሁኔታ ማስታወቂያ እንደሚያስተላልፍ ባለስልጣን መ/ቤቱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ አድርጓል፡፡ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ስለ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች በስፋት መዘገብ፣ ማስታወቂያዎች ከተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በላይ እንዲተላለፉ ማድረግ፣ ወቅታዊ ያልሆነ መረጃን በዜና ማስተላለፍ፣ ስለስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ባለቤት ምንነት፣ ድርጅቱ ስለሚያመርተው ምርት በስፋት መዘገብ፣ በእንግሊዝኛ የተላለፉ መልዕክቶችን አድማጭ ሊረዳው በሚችለው መልኩ በአማርኛ ትርጉም አለማቅረብ እና ሌሎች ችግሮችን  ባለስልጣን መ/ቤቱ በሪፖርቱ ላይ ገልጿል፡፡ በዛሚ ኤፍ ኤም በሚተላለፉ የዜና እወጃዎችም የመረጃ ስህተት እንደሚታይና ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶችን ከፕሮግራም ባለፈ ስለ ድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ ገለፃ ማድረግ፣ ስፖንሰሩ በፕሮግራሙ ይዘት ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ፣ የተጋነኑ ማስታወቂያዎችን ማቅረብ እና የተሳሳቱ ማስታወቂያዎችን ማስተላለፍ ተጠቃሽ ችግሮች እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን የሚፈለግበትን ውዝፍ ክፍያ እንዲከፍል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ክፍያውን ባለመፈፀሙ የተሰጠው የፈቃድ ጊዜ ሲያልቅ ሥራ እንደሚያቆምና የእድሳት ፈቃድ እንደማይሰጠው ባለስልጣን መ/ቤቱ በሪፖርቱ ላይ የገለፀ ቢሆንም ዛሚ ፐብሊኬሽን ያለበትን ውዝፍ ዕዳ ግንቦት 15 ቀን 2004ከፍሎ ማጠናቀቁን ባለስልጣን መ/ቤቱ ለባህል ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ በኢቴቪ 2የፕሮግራም መዘግየትና የወቅታዊነት ችግር እንደሚታይበት ያተተው ሪፖርቱ፤ በሰነድ አልባ ይዞታዎች ላይ የተሰናዳ አንድ ፕሮግራም መቅረብ ከነበረበት ጊዜ ሁለት  ወር ዘግይቶ መቅረቡን ጠቁሟል፡፡ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሞኒተር ከተደረጉ ፕሮግራሞች ውስጥ በሁለት አርቲስቶች ጉዳይ ዙሪያ የተሰራጩ ፕሮግራሞች የሌላኛውን ሃሳብ ሳያካትት መተላለፉ፤ ሴቶችን፣ ህፃናትንና ህብረተሰቡን በአጠቃላይ ወደ መጥፎተግባርየሚገፋፋፕሮግራሞች ማስተላለፍ በጉድለት ተጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ደግሞ ወቅታዊ ያልሆኑ ፕሮግራሞችን ማስተላለፍ፣ አርዕስተ ዜናና ዝርዝር ዜና፣ ምስልና ይዘት የአለመጣጣም ችግሮች እንደተስተዋለበት ተገልጿል፡፡  አፍሮ ኤፍ ኤም 105.3 የተዛቡ ማስታወቂያዎችን የማስተላለፍ ችግሮች እንደታዩበት ሪፖርቱ አትቷል፡፡ በኤፍ ኤም 96.3 ሞኒተር ከተደረጉ ፕሮግራሞች ውስጥ የብሮድካስት አዋጁ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ባለመከተል ትክክለኛ መልዕክት አለማስተላለፍ፣ ለአንድ ወገን ያደላ ዜና ማቅረብ፣ በቅድመ ዜና ዝግጅት በቂ ጥንቃቄ አለማድረግ ባለስልጣን መ/ቤቱ በጉድለት የጠቀሳቸው ችግሮች ናቸው፡፡ በህትመት ሚዲያዎች ላይ መረጃዎችን አጋኖ የማቅረብ ችግሮች በአንዳንዶች ላይ መታየቱን የጠቆመው የባለስልጣኑ ሪፖርት፤ ከ“መሰናዘሪያ” ጋዜጣ ሌላ በስም ተጠቅሶ ችግር እንዳለበት የተገለፀ የህትመት ሚዲያ የለም፡፡ የ“መሰናዘሪያ” ጋዜጣ በዋና አዘጋጅ የትምህርት ደረጃ ላይ ችግር እንደነበር የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአሁኑ ወቅት ጋዜጣው ችግሩን ማስተካከሉን  ገልጿል፡፡

 

 

 

Read 1930 times Last modified on Saturday, 26 May 2012 10:49