Tuesday, 01 January 2019 00:00

በእያንዳንዷ ሩዝ ላይ የሚበላት ሰው ስም ተፅፏል! የህንዶች ተረት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 “አዝማሪና ውሃ ሙላት” የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም እንዲህ ይላል፡-
አንድ ቀን አንድ ሰው፣ ሲሄድ በመንገድ
የወንዝ ውሃ ሞልቶ ደፍርሶ ሲወርድ
እዚያው እወንዙ ዳር፣ እያለ ጐርደድ
አንድ አዝማሬ አገኘ፣ ሲዘፍን አምርሮ
በሚያሳዝን ዜማ፣ ድምፁን አሳምሮ፡፡  
“ምነው አቶ አዝማሪ፣ ምን ትሠራለህ?” ብሎ ቢጠይቀው፤
“ምን ሁን ትላለህ አላሻግር ብሎኝ የውሃ ሙላት
እያሞጋገስኩት በግጥም ብዛት
ሆዱን አራርቶልኝ ቢያሻግረኝ ብዬ
“አሁን ገና ሞኝ ሆንኩ ምነዋ ሰውዬ
ነገሩስ ባልከፋ፣ ውሃውን ማወደስ
ግን እንደዚህ ፈጥኖ በችኮላ ሲፈስ
ምን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ
ድምፁን አያሽካካ መገስገሱን ትቶ
እስቲ ተመልክተው፣ ይሄ አወራረድ
ያልሰማው ሲመጣ፣ የሰማው ሲሄድ፡፡”
ተግሣፅም ለፀባይ ካ ልሆነው አራሚ
መናገር ከንቱ ነው፣ ካልተገኘ ሰሚ!
*   *   *
ስንናገር ሰሚ መኖሩን እናረጋግጥ፡፡ ለነማንና ለማን ነው የምንናገረው እንበል፡፡ አንዳንድ ሰው ብዙ ጆሮ አለው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ፈፅሞ ጆሮ ያልፈጠረበት ነው፡፤
“አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈለግ፣ የባሰ ደንቆሮ”  ይሉናል ከበደ ሚካኤል፡፡
“አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም”ም ያስኬዳል፡፡ ሥልጣን ልብ ያደነድናል፡፡ ጆሮ ያደነዝዛል፡፡ ዐይንን ያስጨፍናል! ህዋሳት በድን ሲሆኑ አገር የልማት ትኩሳቷ ይደነዝዛል! የንቃት ዐይኗ ይጨለመልማል! ተስፋና ምኞት ያስለመልማሉ! እኛ በምሁራዊ ልቦናችን የምንመኝላት መንገድ ው መንገድ ነው ኮረኮንች፣ አሊያም ሊሾ አስፋልት ደሞም ቀለበት ሊሆን ግድ ነው!
መለወጣችን ግድ ነው! ለለውጥ መዘጋጀት ግን የለውጥ ግድ ግድ ነው! ዋናው ችግራችን የተለወጥን እየመሰለን ዘራፍ ማለታችን ነው! ብዙዎቻችን የለውጥ ዕውነተኛውና ሁነኛው ሀሳብ ሳይገባን የተለወጥን ይመስለናል! ምነው ቢሉ… ለውጥ የአንድ ጀምበር ጉዳይ ስላልሆነ ነው! እናርገውም ብንል ከቶም ባንድ ጀምበር አንስማማም! ስለዚህ በብርቱ ማሰብ ያለብን “ዛሬም ትግላችን መራራ፣ ግባችን የትየለሌ” መሆኑን ነው! መስዋዕትነትን አንፍራ! የአቅማችንን ያህል ሩቅ ዕቅድና ሀሳብ አንሽሽ! ዛሬ ሁሉን ባቋራጭ የማሸነፍ ፍላጎት ዘመን ነው (It is a time of short - term mechanisms) የረዥም ጊዜ ዕቅድ ገና ባላወቅንበት አገር “አቋራጭ መንገድ” ፍለጋ ስንባዝን ዓመታት አልፈዋል! ገና ያልፋሉ፡፡  
አሁን መሰረታዊ ፍላጎታችን ስለ ፖለቲካዊ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አኮኖሚያዊም ነው! ጉዳያችን ማን በልቶ ይደር ማንስ ጠግቦ ይደር? የሚለው ነው፡፡
ህንዶች፤
“እያንዳንዷ ሩዝ ላይ የሚበላት ሰው ስም ተፅፏል” የሚሉት እንደ እኛ ባለ አገር የሚሰራ ሀቅ ነው!! ይሄን ምኔም ልብ እንበል! ነገም ጥያቄያችን ይሄው ነው!

Read 5741 times