Print this page
Saturday, 22 December 2018 13:39

ማራኪ አንቀጾች

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 የህልም ነገር

   በህልሜ ጭንቅላቴ ከአንገቴ ተለያይቶና ክንፍ አውጥቶ በጡረታ ድልድይ አናት ላይ እንደ ደመና ሲያንዣብብ አየሁ፡፡ የጡረታ ድልድይ እናቶች በመገረም አንጋጠው ሲያስተውሉ በምጽዐት ቀን የተኮነኑ ነፍሳት ይመስሉ ነበር፡፡
በእንቅልፍ ልብ እራሴን አጽናናለሁ…
“….ማየቱም፣ መናገሩም፣ መስማቱም ያለው ጭንቅላት ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ምን ሲሆን ከአንገት በታች ተንዘላዝሎ ተፈጠረ? ቢቀር እጅና እግር ነው፣ ለእሱም ቢሆን ክንፍ አለ፣ ኧረዲያ መኖርስ ከአንገት በላይ…
ህልም ሥር የሰደደ ድብቅ ፍርሃት እንደሆነ በራሴ አረጋገጥኩ፡፡ ረድ ሠርዌና አባቱ በእኔ ሟርት ሲወራከቡ፣ ነገሩን ችላ ያልኩት መሰልኩ እንጂ ፍርሃትስ ነበር ማለት ነው፤ ካልሆነ…
የጭንቅላቴ አከናፍ ደክመው አየሩን አልቀዝፍ ሲሉብኝና መውደቄ እርግጥ ሲሆን የጡረታ ድልድይ እናቶች “ተዘጋጅ” እንደተባለ ሰልፈኛ ንቃት ታየባቸው። ምን ሊያደርጉኝ እንደሆን ባላውቅም ፍርሃት አደረብኝ። መቅዘፊያ እንደሌላት ጀልባ ጭንቅላቴ በንፋስ እየተገፋ ሲሄድ ያሰፈሰፉት እናቶች ይንቀሳቀሱ ጀመር፡፡ አቅጣጫውን እያማተሩ ሲደርሱ ጭንቅላቴ ሲወድቅ እኩል ሆነ፡፡ ለመያዝ ሲሻሙ ብርድ ልብሴን እንደ መቃብር ድንጋይ በርቅሼ ተነሳሁ፡፡ ፍርሃቱ አለቀቀኝም፡፡ ቀን ከጐዘጐዝኩበት፣ ማታ ካሸለብኩበት ምንጣፍ ላይ ተነስቼ በሩን ዘጋሁት፡፡ ሰውነቴ በፍርሃት ይንቀጣቀጣል፡፡
“የህልም ዓለም ፍርሃት ስለምን ወደ እውን ዓለም ፍርሃትነት ይሸጋገራል” ስል እራሴን ጠየኩ፡፡ መንፈሳችን የታበተበት የሞት ፍርሃት ልኩ የሚታወቀው በእውን ዓለም ማገናዘብ ሳይሆን በህልም ዓለም ደመ ነፍሳዊ ድንጋጤ ውስጥ ነው፡፡ የእኔ መኖር ለእኔ ሆነ ለተቀረው አለም አስፈላጊነቱ እምን ላይ ነው? እስከ መቼስ ከህልም ዓለም ወደ እውን ዓለም ፍርሃት ሳመላልስ እኖራለሁ?…
…አንዳች የሚስቅብኝ ህቡዕ ልቡና መርማሪ አካል እንዳለ ተሰማኝ፡፡ ስለ ስንፍናዬ በፊቱ ሊያሳፍረኝ እየሞከረ እንደሆነ የገባኝ መሰለኝ፡፡ ያ ልቡናዬን የሚበረብር ኃያል ህቡዕ አካል እርሱ ማነው? ልቡናን የመፈተሽ ስልጣን ማን ሰጠው? እራሱ የሥልጣኑ ሰጪና ተቀባይ ይሆን? ሰጪና ተቀባይ አንድ የሆነበት አካባቢ እንዴት ያለ ፍትህ፣ ንፅህናና ቅድስና ይኖራል?…ይሄ የሰው ልጅ የአፈጣጠር ትብታብ ነው። ሰጪና ተቀባይን፣ አልፋና ኦሜጋን፣ ግዝፈትና ረቂቅነትን በአንድ የሚያዳብል የሰው ልጅ ተንኮል ብቻ ነው፡፡ ግዴላችሁም፤ “ኑ በአካላችን በአምሳላችን እንፍጠር” ያለው ፈጣሪ ሳይሆን እራሱ ሰው ነው፡፡ “ኑ እግዚአብሔርን በአካላችንና በአምሳላችን እንፍጠር”
ከየት ተነስቼ እምን ጋ እንደደረስኩ ጠፋኝ፡፡ ይሁንና ፍርሃቴ ጠፍቶ በሬን ተንደርድሬ በመዝጋቴ በራሴ ላይ ሳቅሁ፡፡ መንፈሴ ተዛና--ለማንበብ አኮበኮብኩ። ወረፋ የሚጠብቁ ብዙ መጻሕፍት አሉብኝ፡፡ አንዳንዶቹ ጀምሬአቸው መንፈሴን ስላጨፈገጉብኝ የተውኳቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ የአልበርት ካሙ “The Plague” ገና ስጀምረው በአይጦች ትርምስ ሲሞላ አቆምኩት፡፡ ሌላው ስሙ የማይያዝልኝ ሩሲያዊ ደራሲ፤ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው ስሙን ሲጽፉ ሳያበላሹበት አይቀርም፡፡ SOLZHENITSYN (ሶልዘኒትሳይን) ይባላል፡፡ “Cancer Ward” ይሄም መጽሐፍ ያው ነው፡፡ ተስፋ የሌለው የነቀርሳ ታማሚ፤ መጨነቅ በመፍራት ተውኩት፡፡ ሦስተኛው የብርሃኑ ዘሪሁን ሦስቱ ማዕበሎች ናቸው፡፡ ረሃብ? ወደ ጐን። አንዳንዶቹን መጻሕፍት ተራ የማስጠብቃቸው የአንድ ደራሲ ሥራዎችን አከታትዬ ላለማንበብ ነው። አንዳንድ ደራሲዎች ደግሞ አንቀጽ የሌለው ሃምሣ ስድስት ገጽ ይጽፋሉ፡፡ ለምሳሌ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሳርት እና አየርላንዳዊው ጀምስ ጆይስ፡፡ ተራራ ወጪ አይደለሁም፤ ገና ዳገት እንዳየሁ ሃሞቴ ፍስስ ይላል። አንቀፅ ያልገባበት ጽሑፍ ደረቱን የሰጠ አቀበት ነው፡፡ አዲዮስ!
ያልተነበቡ መጻሕፍት የሚቀመጡበት ጠረጴዛ የዕዳ መዝገቤ ሆኖ ይወቅሰኛል፡፡ እንደ የንታ ጥምጥም ክርክርም ያለ አመል ያላት የሳጠራ ሼልፍ፣ የድል መዝገቤ ሆና ብሥራቴን ትለፍፋለች፡፡ አንብቤ ባልገቡኝ እንደ ጉርጂፍ እና በርትራንድ ራስል ያሉት ፀሐፍያን ላይም ሥራዎቻቸውን አንብቤ በመጨረሴ ብቻ እኩራራለሁ፡፡
(ከደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ “ታለ በዕውነት ሥም” የተቀነጨበ፤ 2ኛ ዕትም)

Read 3952 times
Administrator

Latest from Administrator