Print this page
Saturday, 22 December 2018 09:08

በኳታር 22ኛው የዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  በ2022 እኤአ ላይ ኳታር የምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ  ከዛሬ በኋላ 3 ዓመት ከ10 ወራት ከ5 ሳምንታት ይቀረዋል፡፡ ኳታር የዓለም ዋንጫውን ቅድመ ዝግጅቷን በብዙ ውዝግቦች ታጅባም ቢሆን በተሳካ ሁኔታ እያከናወነች ነው። ለዓለም ዋንጫው መስተንግዶ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሆነባቸው ስምንት ስታድየሞች ግንባታቸው ከዓለም ዋንጫው 2 ዓመት ቀደም ብሎ ለመጨረስ ታቅዷል፡፡ ስታድዬሞቹ  በዘመናዊ ዲዛይኖቻቸው  በዓለም የስነህንፃ እንቅስቃሴ ላይ ተፅእኖ ያሳደሩ ሲሆን፤ በዓለም ዋንጫ ወቅት የአየር ንብረትን የሚቆጣጠሩበት ቴክኖሎጂ ተግባራዊ የሚያደርጉ በመሆናቸው ተደንቀዋል፡፡ የዓለም ዋንጫ ታሪክ ከ88 ዓመታት በላይ ካስቆጠረ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአረቡ ዓለም በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ መካሄዱም  ከፍተኛ ጉጉትና መነቃቃት ፈጥሯል፡፡  የዓለም ዋንጫ  ጨዋታዎች ከመደበኛው የፈረንጆች አመት አጋማሽ ወደ  አዲስ ዓመት ዋዜማ  መዛወራቸው ፤ በአጠቃላይ ለሙሉ የዓለም ዋንጫ ዝግጅት  ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ መደረጉ 22ኛውን ዓለም ዋንጫ ልዩ ያደርገዋል፡፡  
ፋቲማ አልኑዋሚና በራሽያ የተደረገው ዘመቻ
ከ4 ወራት ራሽያ በፊት ራሺያ 21ኛውን የፊፋ ዓለም ዋንጫ በማዘጋጀት ከፍተኛ ስኬት እንደነበራትና፤ በፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የምንግዜም ምርጥ የዓለም ዋንጫ ማስተናገዷ እንደተመሰከራላት ይታወቃል፡፡ የራሽያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለኳታሩ ገዥ አብዱል ቢን ናሲር ቢን ካሊፋ አልታሀኒ የ2022 ዓለም ዋንጫ ግዴታ እንዲወጡ ሃላፊነቱንም አስረክበዋል፡፡ የኳታር መንግስትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቀን ከ500 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በማውጣት ዝግጅቱን እንደቀጠለ ታውቋል፡፡ በራሽያው የዓለም ዋንጫ ላይ በስታድዬሞች የተሟላ አቅምና አደረጃጀት፤ በትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች መሟላት፤ በላቀ የመስተንግዶ ደረጃ የነበሩ ስኬቶች   በቀጣዩ የኳታር የ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ሆነዋል፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ወቅት የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴን የሚወክል ልዑካን በሞስኮ ከተማ ልዩ ዘመቻ ነበራቸው፡፡  በታዋቂው የሞስኮ መናፈሻ ጎርኪ ፓርክ እና በሞስኮቫ ወንዝ ዳርቻ ላይ የልዑካን ቡድኑ የኳታርን የተለያዩ ባህላዊ ትውፊቶች፣ ሙዚቃ፣ የስታዲየም ግንባታዎችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በተለያዩ አቀራረቦች ራሽያ ለገቡ የዓለም ዋንጫው እንግዶች አስተዋውቀዋል፡፡ የዓረቡ ዓለም ገጽታና አጠቃላይ ሁኔታን በሚያንፀባርቁ ክንዋኔዎች የታጀበውን ዘመቻ ያዘጋጀው በኳታር የዓለም ዋንጫውን ዝግጅት በበላይነት የሚያንቀሳቀሰው ሱፕሪም ኮሚቴ Supreme Committee for Delivery and Legacy (SC)  ነበር፡፡ ሱፕሪም ኮሚቴው ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ ውድድሩን ባስተናገዱ የራሽያ ከተሞች በተለይ በሞስኮና ሴንት ፒተርስበርግ  በመዘዋወር ከዓለም እግር ኳስ ማህበረሰብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት ሰርቷል፡፡ በሞስኮ ከተማ በሚገኙት የማክሲም ጎርኪ ፓርክ እና  የሞስኮቫ ወንዝ ዳርቻ ላይ የተዘጋጁትን ኤግዚብሽኖች ጎብኝቻለሁ ኳታራዊያን ለዓለም ዋንጫው መስተንግዶ ከፍ ያለ ትኩረት መስጠታቸውንም ተገንዝቢያለሁ፡፡ በተለይ በሞስኮቫ ወንዝ ዳርቻ ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው ኤግዚብሽን ለዓለም ዋንጫ ማስተዋወቂያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በተሰናዳ ተንሳፋፊ የመልቲሚዲያ ሙዚዬም የኳታር ዝግጅትን እንደተመለከትኩት በጣም አስደናቂ ነበር፡፡ በኳታር የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ሱፕሪም ኮሚቴ የቀረቡትን ዝግጅቶች እና ትርኢቶች በራሽያ የነበሩ የተለያዩ አገሮች ደጋፊዎች፣ ቱሪስቶችን የማረኩ ሲሆኑ ከ30ሺ በላይ ጎብኝዎች በቀጥታ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተወስቷል።   በሞስኮቫ ወንዝ ዳርቻ ላይ በተዘጋጀው ልዩ የመልቲሚዲያ ትርዒት ስለስታዲየሞች ግንባታና ከዓለም ዋንጫው በኋላ ስለሚኖራቸው አገልግሎት፣ ስለትራንስፖርትና ተመልካቾች መስተንግዶ ላይ ገለፃዎች ተደርገዋል፡፡  
አውደ ርእዩን በጎበኘሁበት ወቅት የፊፋን ዋና ጸሐፊ ሴኔጋላዊቷ ፋትማ ሳምባን ጨምሮ የተለያዩ አንጋፋ የቀድሞ የእግር ኳስ ተጨዋቾች፣ አሠልጣኞች እንዲሁም ባለሥልጣናት ከጎብኝዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡
በጉብኝታችን ወቅት ካነጋገርናቸው የኳታር ዓለም ዋንጫ ሱፕሪም ኮሚቴ አባላት መካከል የኮሚኒውኬሽን ዲያሬክተሯ ፋቲማ አልኑዋሚ ዋንኛዋ ናቸው፡፡ ኳታር በዓለም ዋንጫ መስተንግዶዋ ስኬታማ እንደምትሆን በልበሙሉነት የሚናገሩት ፋቲማ አልኑዋሚ ፤ ራሽያ ላይ በነበራቸው እንቅስቃሴ ኳታርን ለዓለም ዋንጫው ታዳሚዎች በቅርበት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል፡፡ ‹‹በዐውደ ርዕዩ የኳታርን መሰናዶ በምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የኳታርን ባህል ከወዲሁ በማስተዋወቅ ጠርተናል፡፡ የዓለም ሚዲያዎች ይህን ጥረት ሊደግፉት እና ሊያበረታቱት ይገባል፤›› ብለዋል። ለመጀመርያ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ላይ በአረቡ ዓለም ላይ ሰፍኖ የቆየውን አሉታዊ አመለካከት እንዲቀየር ጠንክረን እየሰራን ነው›› በማለት የሚሉት አልኑዋሚ ተናግረዋል፡፡ “በኳታር የበርካታ አገራት ዜጎች የሚሠሩ  መሆናቸው፤ እንግሊዝኛ ቋንቋ በጥራት መነገሩና በዓለም ዋንጫ አዘጋጁ ኮሚቴ የተለያዩ አገራት ባለሙያዎች የሚሰሩ መሆናቸው ስኬታማ ያደርገናል” ብለዋል፡፡
እስከ 200 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ዓለም ዋንጫን ለማስተናገድ
በ2022 እኤአ የሚካሄደውን 22 የዓለም ዋንጫውን ለማስተናገድ ከ9 ዓመታት በፊት ኳታርን ጨምሮ 11 አገራት አመልክተው ነበር፡፡ በፊፋ ኮንግረስ የአዘጋጅ አገር ምርጫው ከመከናወኑ በፊት በመጀመርያው ምዕራፍ ከፉክክር የወጣችው የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ አገር ሜክሲኮ ነበረች፡፡ ከዚያም በኋላ ኢንዶኔዥያ በቂ የመንግስት ድጋፍ ባለማግኘቷ ማመልከቻዋን ሰረዘች፡፡ በፊፋ ኮንግረስ በተካሄደው የአዘጋጅ አገር ምርጫ እስከመጨረሻው ዙር ከኳታር ጋር ለዓለም ዋንጫ መስተንግዶው የተፎካካሩት አውስትራሊያ፤ ጃፓን ደቡብ ኮርያ እና አሜሪካ ነበሩ፡፡ 22 አባላት ያሉት የፊፋ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከአመልካች አገራት መካከል አወዳድሮ የ22ኛውን የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ መርጦ በይፋ ያስታወቀው በ2010 እኤአ ላይ ነበር፡፡
በአራት ዙር  በተከናወነው የምርጫ ሂደት ኳታር በመጀመርያው ዙር 11 በሁለተኛው 10 በሶስተኛው 11 እንዲሁም በ4ኛው ዙር 14 ነጥብ በማግኘት ለአዘጋጅነቱ ተመርጣለች ፡፡ እስከ 4 ዙር የቅርብ ተፎካካሪዋ የነበረችው በ8 ነጥብ አሜሪካ ስትሆን ደቡብ ኮርያ በመጀመርያው ዙር፤ ጃፓን በሶስተኛው ዙር እንዲሁም አውስትራሊያ በሁለተኛው ዙር ከውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡
ኳታር የዓለም ዋንጫውን መስተንግዶ ካገኘች በኋላ ባለፉት ስምንት ዓመታት ለመስተንግዶው እያደረገች ባለው ዝግጅት በመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና በተለያዩ ሁኔታዎች እስከ 200 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ታደርጋለች፡፡
ስምንቱ ስታድዬሞች
ከ10 ዓመታት በፊት ኳታር  ዓለም ዋንጫውን በ8 ከተሞች የሚገኙ  12 ስታድዬሞችን  በአዲስ ግንባታና እድሳት ለማዘጋጀት ያቀረበችው እቅድ ነበራት፡፡  በፊፋ ኮንግረስ ከስምንት ዓመታት በፊት ለመስተንግዶው ስትመረጥ የስታድዬሞቹን ብዛት ስምንት ብቻ ለማድረግ ወስናለች፡፡
በአዲስ መልክ የምትገነባቸውን አምስት ስታድዬሞችን በመጀመርያ ያስተዋወቀችው በ2010 እኤአ ላይ ነበር፡፡  ሰሞኑን ደግሞ የ22ኛውን የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደውን ግዙፉን የሉሳሊ አይከን ስታድዬም ዲዛይን አስተዋውቃለች፡፡ 88ሺ ተመልካቾችን የሚያስተናግደው ሉሳሊ አይከን ስታድዬም ከዋና ከተማዋ ዶሃ 15 ኪሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሉሳሊ ማሪና ከተማ የሚገነባ ነው። ጥንታዊውን የሩቅ ምስራቅ ባህላዊ እደጥበብ በሚያንፀባርቅ ልዩ የስነህንፃ ዲዛይን የሚሠራ ነው፡፡
የሉሳሊ አይከን ስቱድዮ ዲዛይን ይፋ በሆነበት ወቅት አዘጋጅ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ የ22ኛው የዓለም ዋንጫ አስተናጋጅ የሆኑት ሁሉም ስታድዬሞች የአረቡን ዓለም በተለይ የመካከለኛው ምስራቅን ታሪካዊና ባህላዊ ትውፊቶች የሚያንፀባርቁ መሆናቸውንና ዓለም ዋንጫን በአገሪቱ ባህል ሆኖ እንዲቀር አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ገልፀዋል፡፡  የፊፋ ዋና ፀሃፊ የሆኑት ሴኔጋላዊቷ ፋቲማ ሳሙራ በበኩላቸው ኳታር በ ዘመናዊ የስታድዬም መሰረተልማቶችና ልዩ ዲዛይኖች ለዓለም ዋንጫው የላቀ ደረጃ መፍጠሯን አድንቀዋል፡፡
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የአል ዋክራህ ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ14 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ የስታድዬሙ ዲዛይን በኳታር የወደብ ከተማ ማሪታይም ያለውን “ደሃው” በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ባህላዊ የጀልባ መጓጓዣን የሚያንፀባርቅ ሲሆን ተነቃቃይ ዙርያ ገብ ጥላፎቅ ይኖረዋል፡፡
አልዋክራህ ስታድዬም
60ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የአል ባያት ስታድዬም ከዶሃ ከተማ 27 ማይሎች ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከምድብ አንስቶ እስከ ግማሽ ፍፃሜ የሚደረጉ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው ይህ ዘመናዊ ስታድዬም በዲዛይኑ ባህላዊውን የአረቡ ዓለም ድንኳን “ባያት አልሻራርን” የሚመስል ሲሆን የዓረቡን ዓለም እንግዳ ተቀባይነት እንዲያንፀባርቅ ታስቦ ተሠርቷል፡፡
አልባያት ስታድዬም
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የአል ራያን ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ14 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ የስታድዬሙ ዲዛይን የኳታርን የቆየ የንግድ ታሪክ እና የአራዊት መናኘርያነት የሚያመለክት ገፅታ የሚላበስ ነው፡፡ ስታድዬሙ ለኳታር በርሃማ ክልል ባለው ቀረቤታ የአካባቢውን የንግድ መናሐርያዎችን የሚመሳሰልስነህንፃዎች ሲኖሩት የኳታርን ባህል የሚያንፀባርቅ ገፅታ ዙርያውን የሚኖረውና በበረሃ ክልል የሚገኙ አሸዋማ ኮረብታዎች በዙርያው የሚያጅቡት ይሆናል፡፡ አል ራያን ስታድዬም ከምድብ እስከ ሩብ ፍፃሜ የሚደረጉ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል፡፡
አልራያን ስታድዬም
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የኤዱኬሽን ሲቲ ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ7 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ ስታድዬሙ በኳታር ፋውንዴሽን ክልል ውስጥ እየተገነባ ሲሆን በከተማው በርካታ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርስቲዎች መኖራቸው ልዩ ያደርገዋል፡፡ ስታድዬሙ እስከ ሩብ ፍፃሜ ድረስ ጨዋታዎችን እንደሚያስተናግድ የሚጠበቅ ሲሆን ከዓለም ዋንጫው በኋላ የኳታር ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ሜዳ ሆኖ አገልግሎቱን ይቀጥላል፡፡ የዳይመንድ ቅርፅ የሚኖረው ስታድዬሙ የበርሃው ዳይመንድ በሚል ስያሜ እየተጠራ ሲሆን ገፅታው ቀን ቀን እንዲያንፀባርቅ ማታ ማታ ደግሞ ፍንትው ብሎ እንዲበራ ይደረጋል፡፡
ኤዱኬሽን ሲቲ ስታድዬም
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የአል ቱማማ ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ8 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ ስታድዬሙ በኳታራዊ የስነህንፃ ባለሙያ  መሰራቱ ልዩ ሲያደርገው ዲዛይኑ በኳታር ወንዶች ባህላዊ ልብስ ጋሂፋያ ተምሳሌትነት ገፅታውን ያገኘና ዙርያውን በአረንጓዴ መናፈሻዎችእና ፓርኮች የሚከበብ ይሆናል፡፡
አልቱማማ ስታድዬም
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የራስ አቡ አበዋድ ስታድዬም  ከዶሃ ከተማ በ8 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሚሆን የግንባታ ስራ በ998 ኮንቴነሮች ተገጣጥሞ የሚሰራው ስታድዬሙ ከዓለም ዋንጫ ሙ በሙሉ የሚፈርስ ነው፡፡
80ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የሉሳሊ አይከን ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ10 ማይሎች ርቀት ይገኛል፡፡
ራስ አቡ አበዋድ ስታድዬም
40ሺ ተመልካች የሚያስተናግደው የከሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድዬም ከዶሃ ከተማ በ8 ማይሎች ርቀት የሚገኝ ነው፡፡ ይህን ስታድዬም ከሌሎች የተለየ የሚያደርገው በአዲስ መልክ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ሲሆን ከ1976 እኤአ ጀምሮ የኳታር ብሄራዊ ቡድን ሜዳ ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡
ከሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድዬም
ኳታር የዓለም ዋንጫውን አዘጋጅነት በይፋ ከተረከበች 8 ዓመታት ያስቆጠረች ሲሆን እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሚሆንባቸውን ስምንት ስታድዬሞች 21ኛው የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ አዘጋጅታ ትጨርሳለች። የመጨረሻ ሆኖ ግንባታው የሚያልቀው የሉሳሊ አይከን ስታድዬም ሲሆን ከሁሉም አስቀድሞ የተጠናቀቀው የመጀመርያ ስታድዬም ሁለገብ እድሳት የተደረገለት የከሊፋ ኢንተርናሽናል ስታድዬም ነው፡፡
በአልክሆር ከተማ የሚገኙት የአልሞክራህ እና የአልባየት ስታድዬሞች ግንባታ በ2019 እኤአ መጨረሻ ላይ እንደሚያበቃ የሚጠበቅ ሲሆን ሌሎቹ ስታድዬሞች እስከ 2020 ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ይጠናቀቃል፡፡ የኳታር መንግስት ከዓለም ዋንጫው በኋላ ለአንዳንዶቹ ስታድዬሞች ያሉትን ተነቃቃይ ጣሪያዎች እንዲሁም ከ17000 በላይ የስታድዬም መቀመጫዎች በእርዳታ ለተለያዩ አገራት ለማበርከት ወስኗል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ የምትገኘው ኳታር 11,581 ስኴር ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት ያሉት ስትሆን ይህም ከተሞቿ በቅርብ ርቀት እንዲገናኙ አድርጓቸዋል፡፡ በዓለም ዋንጫው ወቅት ከስታዲዬም ስታዲዬም ለመጓዝ ቢያንስ  የአምስት ደቂቃ ቢበዛ ረዥም ርቀት የሚወስደው  ሁለት ሰዓት ይሆናል፡፡ የስታዲየሞቹ በቅርብ ርቀት ላይ መገኘት ተመልካቹ እንደፍላጎቱ ተንቀሳቅሶ ጨዋታን እንዲመለከት ያስችለዋል ተብሏል፡፡ ሌላው ስታድዬሞቹን ልዩ የሚያደርጋቸው የአካባቢውን ሙቀት በውስጣቸው ወደ 20 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይንም ወደ 36 ዲግሪ ፋራናይት በሚያወርዱበት የግንባታ ቴክኖሎጂ በመሰራታቸው ነው፡፡
ከስታዲየሞቹ ባሻገር የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችም እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

Read 7301 times