Print this page
Saturday, 15 December 2018 14:53

“የየት አገር ሰው ነው?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


      “--ፍቅርና ጓደኝነት የስሜትና የልብ ጉዳይ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ጉዳይ መሆኑን አላየች! እናማ…ጓደኝነት ኢንቨስትመንት ሆኗል… ካልጠቀመህ ምን ያደርግልሀል!... የባንከ ደብተር አለው?... ሰባት ዲጂት ዲፖዚት አለው? ስንት ገንዘብ አለው? ስንት ቤቶች አሏት? ከባለስልጣናት እነማንን ያውቃል? --”
    
     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ዘንድሮ ‘ነግ በእኔ’ን የመሰለች ለዘመኑና ለእኛ በልክ የተሰፋች አባባል የለችም፡፡
እንደ ወንዝ ድንጋይ አሳ እንደላሰው
ሙልጭልጭ እያለ አስቸገረኝ ሰው
በሀሰት ሲደልለኝ ፈገግታው ጥሩ ነው
ዛሬ ከእኔ ጋራ ነገ ከሌላው ነው
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡ ለዘንድሮ በልክ የተሰፋች ስንኝ ትመስላለች፡፡ የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ወዳጅነት፣ ጓደኝነት፣ ጉርብትና የመሳሰሉት ህብረተሰባችንን አስተሳስረው የኖሩ እሴቶች አሁን ፈተና ገጥሟቸዋል፡፡ ለዚህ አንድ መቶ አንድ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ አልለቅ ያለንና የተለያዩ ክፍሎች፣ ለግል ፍላጎታቸውና ለቡድን ጥቅማቸው እያባባሱት ያለው የዘር ፖለቲካ ከዋነኞቹ መሀል ነው፡፡
እናላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በአንድ በኩል በሀሳቦች፣ አመለካከቶችና ድርጊቶች ሁሉ ቀዳሚው መመዘኛ ዘር መሆኑ እንዲቀር እየተለፋም… ላስነጠሰንም፣ ላደናቀፈንም … ሁሉንም ነገር ከዘር ጋር የምናያይዝ ደግሞ ሞልተናል፡፡ እናማ… በዚህ የተነሳ ለስንት ዘመን ጥብቅ ሆነው የኖሩ ትስስሮች፣ ነፋስ እየገባባቸው ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚቹ ከተማችን ውስጥ ባለፉት ወራት ፖለቲካችን፣ የተለያዩ ሀሳቦች ያሏቸው ጓደኛሞች፤ “ዓይንህ ለአፈር!” “ዝምቤን እንኳን እሽ አንዳትይ!” አይነት ነገር እየተባባሉ መለያየታቸውን ሰምተናል፡፡ ጋሼ ትረምፕ አገር ያሉ ወገኖቻችንም ትዳራቸው በራሱ የሚያቃቅር እንከን ሳይኖረው በዘር ፖለቲካ ምክንያት ሰማንያቸውን የሚቀዱ እንዳሉ ሰምተናል፡፡ የምር ያሳዝናል፡፡ ስለ አንድነትና ስለ አብሮ መኖር ---  እነሱ መካሪዎች፣ እኛ ምክር ተቀባዮች ሆነን፣ የሌሎች ሀገራት ምሳሌዎች ይነገረን መጀመሩ የምር ያሳዝናል፡፡
እናላችሁ…በተለያዩ መልኮች የሚገለጹት የአብሮ መኖር እሴቶቻችን ፈተና ገጥሟቸዋል። ይህኛውም፣ ያኛውም እየተነሳ፣ በዚህ ህዝብ እጣ ፈንታ፣ ይግባኝ የሌለው ፍርድ አስተላላፊ አይነት በሆነበት ዘመን እየተሸረሸሩ ያሉ የወዳጅነትና የጉርብትና እሴቶቻችን የምር ሊያሳስቡን ይገባል፡፡
በቀደመው ጊዜ ጓደኛሞች ሆኑ አብሮ አደጎች፣ ሁለትም ይሁኑ አስራ ሁለት የሚያስተሳስሯቸው ጠንካራ ክሮች ነበሩ፡፡ አብረው ከመብላትና ከመጠጣት ባለፈ በደስታም ሆነ በሀዘን ጊዜ የይሉኝታ ሳይሆን የልብ መረዳዳቶች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ደስታም፣ ሀዘንም እንደ ፍጥርጥሩ ያውጣው ተብለው የሚተዉ ሳይሆን፣ የጋራ ተደርገው ይወሰዱ ነበርና ነው፡፡ ጓደኝነቱም፣ አብሮ አደግነቱም የሕይወት አካል ነበሩና፡፡ ወሬና መተቻቸት አንኳን ቢኖር… አለ አይደል… ግፋ ቢል “አከሌ አረንጓዴ የሆነውን ነገር ሁሉ እየቃመ በዓለም የመጀመሪያው የፍየሎች ሪቮሉሽን በአገራችን እንዳይጀመር…” አይነት  “እሱ በሳምንት ሰባት ቀን ሹክክ እያለ ጣልያን ሰፈር የሚሄደው… ጭንቅላቱ ላይ ቆጣሪ ተገጥሞለታል እንዴ!” አይነት መበሻሸቅ ይኖር ይሆናል እንጂ “እንዲህ እኮ የሚያደርገው የዚህ አካባቢ ሰው ስለሆነ ነው፣” ብሎ ነገር አልነበረም፡፡ ከራሱ መንደር አስር ኪሎ ሜትር አንኳን ሄዶ የማያውቀውን፤ ሦስት ሺ ኪሎ ሜትር ወስደን… “የዚህ አካባቢ ሰው ስለሆነ እኮ ነው…” ብለን የሌለበት  ህብረተሰብ ውስጥ እንዶለዋለን፡፡
በነገራችን ላይ አንድ ትንሽ ግራ የሚያጋባ ነገር አለ…በመፈክር ነገሮች ላይ አልፎ፣ አልፎ የምናየው፡፡ “ማንም ሰው ብሔሩን አልመረጠም!” የሚል አይነት ነገር--- ትንሸ  ግራ አያጋባም? አለ አይደል… ልክ እኮ “መምረጥ ብችል ኖሮ፣ የሌላ ብሔር አባል (ወይም “የእናንተ ብሔር አባል) እሆን ነበር” ማለት ይመስላል፡፡ ብቻ የሆነ የማይመች ትርጉም ይሰጣል፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“መኪና ምን ያደርጋል፣ ትርፉ መጋጨት ነው..” የሚል ወዳጅ ደስ አይላችሁም! ቢያንስ ሞራላችሁን ጠብቆላችኋላ! አለበለዛ… “አንተ መኪና ገዛህ ማለት አኔ የሮናልዶን አውሮፕላን በጨረታ አሸንፌ ገዛሁ ማለት ነው…” ቢላችሁ ሞራላችሁ ያለ ቪዛ አገር ጥሎ ይጠፋ ነበር፡፡ አይጠልዙትማ! ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አዚህ ኢሚግሬሽን አካባቢ የሚሰለፈው ሰው እኮ ብዙ፣ በጣም ብዙ እየሆነ ነው፡፡ ደግሞም አብዛኞቹ ከክልሎች አካባቢ የመጡና ምናልባትም በአስራዎቹ አጋማሽ ወይም ሀያዎቹ መዳረሻ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ወጣቶቿ ጀርባቸውን የማያዞሩባት አገር ያድርግልንማ!
በነገራችን ላይ አንዳንድ ጊዜ ሰዋችን አርሴና ማንቼን አብይ አጀንዳ ቢያደርግ “ታዲያ ምን ያድርግ! ግራ የሚያጋቡ ነገሮች በዙበት እኮ!” አይደለም በማያውቁትና ባዳ በሚባሉ ሰዎች አካባቢ… አለ አይደል… ለስንት ዘመናት አብረውት በኖሩት ጓደኞች አንኳን የሚናገራቸውና የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ፣ ከትውልድ ስፍራውና ከ‘አፍ መፍቻ ቋንቋው’ ጋር እየተመዘነ መተንፈስ ሲያቅተው ምን ያድርግ! አሁን እኮ አይደለም በእለታዊ አንቅስቃሴዎቻችን፣ የቴሌቪዥን ጠያቂዎችና ተጠያቂዎችን የምንመዝነው በአስተሳሰብ ምጥቀታቸው ወይም በሙያ ከፍታቸው ሳይሆን በዘር ድልደላ እየሆነ ነው፡፡ ለእኛ ደስ የሚሉን ነገሮች ከሰማን “ኢሮ!” ብላን እናጨበጭባለን፤ ደስ ካላለን ደግሞ አንዱን ወገን የሆነ የዘር ኩሬ ውስጥ ወርውረን “ድሮስ ቢሆን…” ነገር እንላለን፡፡
እናላችሁ…
እኔን ለቸገረኝ ለበላሁ ሽምብራ
ጓደኛዬ ጠላኝ አንደባላጋራ
የሚሏት ነገር አለች፡፡ ነገርዬዋ የ‘ኢኮኖሚ’ ጉዳይ፣ ወይም “አኔ ከቺሰታ ጋር አልገጥምም፣” አይነት ነች እንጂ… “እሱ አኮ ቸግሮት ሽምብራ የሚበላው የእንትን አካባቢ ሰው ሰለሆነ ነው፣” የሚለው አልነበረም፡፡ አናማ...ከፍ ብለን የጠቀስናትን ስንኝ ለመነካካት ያህል…
እኔን ለቸገረኝ ለበላሁ ሽምብራ
በዘሬ አሳበበ አንደባላጋራ፡፡
ፎቅና መርሴዲስ ሰሜት አይሰጡኝም
እኔን ፍቅር አንጂ ሀብት አያሞኘኝም
ብላ ነበር ብዙነሽ…ዘንድሮ ጉዳችንን አላየች፡፡ ፍቅርና ጓደኝነት የስሜትና የልብ ጉዳይ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ጉዳይ መሆኑን አላየች!
ሁልጊዜ ለክፋት ሃሳቡ እያደላ
ተንኮልን የሚወድ ፍቅርን የሚጠላ
ደግ ለዋለለት ክፉ የመለሰ
ይሙት በህሊናው እንደተወቀሰ
ብለዋል ከበደ ሚካኤል…በዘመናቸው፡፡
በዚህ ዘመን ይቺን ስንኝ ለመጠቀም መጀመሪያ ህሊና የሚባለው ነገር ስለመኖሩ መግባባት አያስፈልግም ብላችሁ ነው! ግን ይሄ በራሱ ችግር አለው፡፡ አንዱን ሰው “ለምን ህሊና እንደሌለው ሰው ትሆናለህ!” ብትሉት፣ እውነተኛውን ምክንያት ከመመርመር ይልቅ “እንዲህ ያለኝ በዘሬ የተነሳ ነው‹” ሊላችሁ ይችላል፡፡ “እና ‘እኛ’ ህሊና የለንም ማለት ነው!” ብሎ የነገሩን ወርድና ስፋት ሊለጥጥባችሁ ይችላል፡፡ በሆነ ባልሆነው ሁለት ሰዎች በተጋጩና ቡጢ በተሰነዛዘሩ ቁጥር ድፍን ዩኒቨርሲቲዎች የሚተረማመሱት በዚህ አይነት አስተሳሰብ የተነሳ ነው፡፡
ዘንድሮ ሰዉ ‘ጓደኛ’ መሆኑ ቀርቶ፣ ‘ሰው’ መሆኑ ቀርቶ፣ አብሮ ሻይ ምናምን የሚባባል መሆኑ ቀርቶ… “የእንትን አካባቢ ሰው ሆኗል። አንድ ሰሞን… በብዛት ይሰሙ የነበሩት… ‘ተለጣፊ፣’  ‘ተቸካይ፣’ ‘ጥገኛ፣’ ‘ተንበርካኪ፣’ የሚሏቸው ነገሮች፣ መደበኛ ስሞቻችንን ስፍራ አስለቅቀው በፍርድ ቤት ያላስለወጥናቸው መጠሪያዎችችን ሆነው ነበር፡፡ ደግሞላችሁ… በተለያዩ መልኮች የሚመጡ  በ‘ኛ’ ፊደል የሚያልቁ መጠሪያዎች አሁንም አልለቀቁንም፤ የምር እኮ የስድቦችና የዘለፋዎች ‘ጥልቅ ተሀድሶም’ ያካሄድን ነው የሚመስለው፡፡
ፎቅና መርሴዲስ ስሜት አይሰጡኝም
እኔን ፍቅር አንጂ ሀብት አያሞኘኝም
ብላ ነበር ብዙነሽ…ዘንድሮ ጉዳያችንን አላየች። ፍቅርና ጓደኝነት የስሜትና የልብ ጉዳይ ሳይሆን የኢንቨስትመንት ጉዳይ መሆኑን አላየች! እናማ…ጓደኝነት ኢንቨስትመንት ሆኗል… ካልጠቀመህ ምን ያደርግልሀል!... የባንከ ደብተር አለው?... ሰባት ዲጂት ዲፖዚት አለው? ስንት ገንዘብ አለው? ስንት ቤቶች አሏት? ከባለስልጣናት እነማንን ያውቃል? እና ደግሞ.. የጥያቄዎች ሁሉ አናት… “የየት አገር ሰው ነው?” ሆኗል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2048 times