Saturday, 15 December 2018 14:50

የክፍለ ዘመኑ የኢህአዴግ አስቀያሚ ታሪክ??!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(31 votes)

“ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ” – (ለገዢው ፓርቲ የተመረጠ አገራዊ ተረት!)
                     

    ስድስተኛ ፎቅ ላይ ወደ ሚገኘው ቢሮዬ ለመውጣት፣ ቆሜ  ሊፍት እየጠበቅሁ ነበር። እንደኔው ሊፍት የሚጠብቁ ሁለት ወንዶች፣ አጠገቤ ቆመው፣ ጮክ ብለው ያወራሉ - እጃቸውን እያወራጩ፡፡ ከቆምኩበት ስንዝር ሳልነቃነቅ፣ የወሬያቸው ርዕሰ ጉዳይ፣ ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡ አጀንዳውን አውቀዋለሁ፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ አሳዛኝና አሳፋሪ የኢህአዴግ የቅሌት ታሪክ ነው፡፡ የግፍ ታሪክ! ከሰብአዊነት የተፋታ የጭካኔ ታሪክ!!
አዎ፤ አጠገቤ የቆሙት ግለሰቦች የሚያወሩት፣ ሰሞኑን በመንግስት ቴሌቪዥን ስለተላለፈው፣ በእስረኞች ላይ የተፈጸመ እጅግ አሰቃቂ  የግፍ ታሪክ ነው፡፡ ወዲያው ሊፍቱ መጣና አብረውኝ ገቡ፡፡ ወሬያቸውን ግን አላቋረጡም፡፡ ቁጣ ጨምረውበት ቀጥለዋል፡፡  
ከሁለቱ አንደኛው ወደኔ እያየ፤ “አየኸው ይሄን ህዝብ! ይሄን እየሰማ ዝም ብሎ ተጋድሟል” አለኝ። (የሸገርን ህዝብ ማለቱ መሰለኝ!)
 “ህዝቡማ  ጨዋ ነዋ!” ሳላውቀው ነው ከአፌ ያመለጠኝ፡፡  
“ጨዋ?! ልፍስፍስ ነው እንጂ!!” አለ ሰውዬው፤ በቁጣ ገንፍሎ፡፡
 (እኔን ይሁን ህዝቡን አላወቅሁም፡፡)
“ምን እንዲያደርግ ነው የፈለጉት? እንዲጋደል?!-- አገር እኮ ይፈርሳል!” አልኩኝ፤ በቅጤ ሳላስብ፡፡
“አገር ይፈርሳል ነው ያልከው!? ለምን ፍርስርስ አይልም!!” አምባርቆብኝ ከሊፍቱ ወጣ፡፡
 (እግዜር ነው ያወጣኝ!!)
ግን ይሄ ሁሉ ክፋት፣ ይሄ ሁሉ አውሬነት፣ይሄ ሁሉ ጭካኔ፣ ይሄ ሁሉ መሰይጠን --- ከየት መጣ?! ኢትዮጵያውያውያንን ከሚመራ ፓርቲ፣ ዲሞክራሲን አስፋፋለሁ፣ አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ አሰልፋለሁ፣ ህዝቡን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድህነት አረንቋ አወጣለሁ -- እያለ ሲደሰኩር ከኖረ መንግስት ነው፡፡ ፈጽሞ የማይታመን እኮ ነው!! (ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ! ነው ያለው- የአገሬ ሰው!) በጥልቀት መጠናት ያለብን ህዝቦች ነን!!
ሊፍት ውስጥ ሊጣላኝ የዳዳው ሰውዬ -- ጉዳይ  ቀኑን ሙሉ ሲያሳስበኝ  ዋለ፡፡ በቴሌቪዥን የተላለፈው ዘግናኝ የግፍ ታሪክ (መቼ ገና ታሪክ ሆነ?) በብዙዎች ልብ ውስጥ ጥላቻን፣ በቀልን፣ ቁጣን፣ አውሬነትን፣--- ወዘተ ሊፈጥር እንደሚችል  እያሰብኩ፣ በስጋት ተውጬ  ዋልኩላችሁ፡፡ ምናልባት ዶክመንታሪው በባለሙያዎችና በአገር ሽማግሌዎች አስተያየትና  ምክር ቢታጀብ ጥሩ ነበር - ሌጣውን ከሚቀርብ፡፡ (ጭንቀት የወለደው ሃሳብ ነው!)
ጠ/ሚኒስትሩ ያወጡትን መግለጫ ማታ ስሰማ ግን  እፎይ አልኩ፡፡ “ግፍ ሰርቶ መደበቅ፣ ዘርፎ መንደላቀቅ አይቻልም” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤” ግፈኞች የግፋቸውን ዋጋ በህግ እንዲያገኙ ከእነሱ የተሻልን መሆናችንን በተግባር ማሳየትአለብን” ብለዋል፡፡ “…ቂምና በቀልን ልናስብ  አይገባም፤ፍርድና ፍትህን እንጂ” ሲሉም አሳስበዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ “ግፈኞቹ ትግርኛ ተናጋሪም ይሁኑ ኦሮምኛ አሊያም ሲዳማ፤ የበቀሉበትን ብሔረሰብ ፈጽሞ አይወክሉም፤ ወንጀለኛ ራሱን ችሎ ወንጀለኛ ነው!!” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ”ለአንድ ገጽ ብለን መጽሐፍ የምንቀድ ሞኞች አይደለንም” ብለዋል፡፡ ዛሬም “አንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ነው” የሚሉ የቀድሞ ባለሥልጣናትና ጭፍን የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ግርም ይሉኛል። በቴሌቪዥን የታየውና የተሰማው ግፍና በደል እንኳን አይሰማቸውም፡፡ “አንድ ብሄርን ለማጥቃት የታለመ እርምጃ ነው” በሚለው ትርክታቸው ተጨፍነዋል፡፡ ያሳዝናል!! (እኒህም የኢህአዴግ ፍሬዎች ናቸው!)
 የፓርቲዎች ነገር!
በቅርቡ 80 የሚደርሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በወቅቱም ከተነሱት ጉዳዮች መካከል  ፓርቲዎች  በመዋሃድ ቁጥራቸውን ወደ 4 እና 5 እንዲያወርዱ የቀረበው ሃሳብ (ጥያቄ) ይገኝበታል፡፡ (የምርጫ መስፈርት  ማድረግ ነበር!) ችግሩ ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች፤ ሥልጣን በጋራ ሳይሆን በግላቸው ነው የሚመኙት። (እንደ ፓርቲ ሊቀመንበር!) እናም የመዋሃድ ነገር የሚታሰብ አይመስለኝም። አንዳንዶቹ የምርጫ  መስፈርት ነው ቢባሉ እንኳን በጄ አይሉም፡፡ ምርጫው ቢቀርባቸው ይሻላቸዋል። (በውህደት ፓርቲያቸውን ከሚያጡ!) ለነገሩ በምርጫ ቢወዳደሩም እንደማያሸንፉ ያውቁታል፡፡ (ከህዝቡ ጋር የት ተዋውቀው!) ለእነሱ ፖለቲካ ቢዝነስ ነው፡፡ (“የፖለቲካ ሸቃጮች” ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ!) አንዳንዶቹ ደግሞ የሊቀ መንበርነት ሱስ ተጠናውቷቸዋል!! በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ሊቀ መንበር ሳይሆኑ መኖር አይችሉም፡፡ (ምክትል ሊቀመንበርነትን እንኳን አይቀበሉም!) በውህደት የሚፈጠረውን ፓርቲ በሊቀ መንበርነት የሚመሩ ከሆነ ግን ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ (ማስተማመኛ ከተሰጣቸው ነዋ!)
ባይገርማችሁ እንዲህ ያሉት ፖለቲከኞች--- ፓርቲ የግል ንብረታቸው ነው የሚመስላቸው። (ለዚህ እኮ ነው በተጣሉ ቁጥር የፓርቲውን ማህተም ይዘው የሚጠፉት!) እኔ የምለው-- የፖለቲካ ፓርቲ ንብረትነቱ የማነው? (ኢህአዴግ እኮ---”መሬት የመንግስትና የህዝብ ነው” እያለ ሲፎግረን ኖሯል!) ያውም በሊዝ እየቸበቸበ!! ኢቴቪም፤ የህዝብና የመንግስት መሆኑ ተነግሮናል። (የማን አገር ህዝብ?!)
እናላችሁ--- አንዳንድ ፓርቲዎች (ጠ/ሚኒስትሩ እንደመከሩት)፤ ከሌሎች ጋር ተዋህደው፣ የ”መዋጥ” ዕጣ ፈንታ እንዲገጥማቸው  አይፈልጉም፡፡ (“ምን ልታዘዝ” በተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ ላይ “ፓርቲዬ ተዋጠብኝ” የሚለው የ”ልጥ” ፓርቲ ሊቀመንበር ትዝ ይላችኋል?!) አያችሁ--- መዋጥ ማለት፤ ለስንት ዓመት የመሩትን ፓርቲ ማጣት ማለት ነው። መዋጥ ማለት፤ለዓመታት ከገነኑበት  የፓርቲ ሊቀመንበርነት መገርሰስም ሊሆን ይችላል፡፡ (የሰይጣን ጆሮ አይስማው?!)
እኔ በበኩሌ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንኳን ለቀጣዩ ምርጫ ቀርቶ፣ ከ20 ዓመት በኋላም፣ ከ80 ወደ አራት ይቀነበባሉ ብዬ አልጠብቅም (“ዲቫይን ኢንተርቬንሽን” ካልተጨመረበት በቀር!) እናም ለምን ፓርቲዎቹን እስከዛው ደረስ በድንቃ ድንቅ ታሪኮች መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ) ላይ አናስመዘግባቸውም? መቼም 80 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሉት አገር እምብዛም አይኖርም። የበሰለ ፖለቲከኛና የበሰለ የፖለቲካ ባህል የላትም በምትባል አገር ውስጥ  80 ፓርቲዎች ምን ይሰሩልናል? (ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችንንማ ሰሞኑን አየነው!)

Read 6020 times