Saturday, 19 May 2012 11:50

በለንደን ኦሎምፒክ ስንት ወርቅ እንጠብቅ??!!

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በለንደን ከተማ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 30ኛው ኦሎምፒያድ፤ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌደሬሽን እንዲሁም ብሄራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ የሚያዘጋጀው አትሌቲክስ ፌደሬሽን ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ሰሞኑን በማራቶን የዓለም ምርጥ አስር አትሌቶችን መርጦ ይፋ አድርጓል፡፡ በማራቶን ቡድኑ ምርጫ  በኢንተርናሽናል ውድድር ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ፤ በወቅታዊ ብቃታቸውና በሚሰጠው ስልጠና የተሻለ አቋም ያሳዩና ዘንድሮ ከአንድ ማራቶን በላይ ያልሮጡ የሚሉ መስፈርቶችን በመከተል ነው ፌደሬሽኑ የማራቶን ሩዋጮችን የመረጠው፡፡ በዚህ መሰረት በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድር ኢትዮጵያን በወንዶች የሚወክሉት በዱባይ ማራቶን ከ1 እስከ 3 የወጡት  አየለ አብሽሮ” ዲኖ ሰፈርና ማርቆስ ገነቴ፤ በሮተርዳም ማራቶን 2ኛ የወጣው ጌቱ ፈለቀ እንዲሁም በዱባይ ማራቶን 5ኛ ደረጃ ያገኘው ታደሰ ቶላ ናቸው፡፡

በሴቶች ደግሞ የሮተርዳም ማራቶን አሸናፊዋ ቲኪ ገላና፤ በዱባይ ማራቶን ያሸነፈችው አሰለፈች መርጊያ፤ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ያገኙት ማሩ ዲባባና የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችው ትርፌ ፀጋዬ ተይዘዋል፡፡ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን አምስት ወርቅና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያዎች ማግኘቱዋ ሲሆን የዘንድሮው የማራቶን ቡድን በርካታ ሜዳልያዎች የማግኘት ሰፊ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

በአጭር ርቀት ለኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ሜዳልያ አዲስ ተስፋን የፈነጠቁት ሁለት አትሌቶች  ሲሆኑ በሴቶች 800 ሜትር ፋንቱ ሚጌሶ እና በተመሳሳይ ርቀት በወንዶች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው መሃመድ አማን እንደሆኑ ታውቁዋል፡፡ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር ለኢትዮጵያ የለንደን ኦሎምፒክ ቡድን ለመመረጥ የሚያበቃ ሚኒማ ለማምጣት ከ20 በላይ ምርጥ አትሌቶች የሚፎካከሩ ሲሆን በተለይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር በሆላንድ ሄንግሎ ኤፍቢኬ ጌምስ እና በአሜሪካው ዩጂን ፐሮፎንታይኔ ቴክላሲክስ በሚካሄዱ ውድድሮች ከፍተኛ ትንቅንቅ ያደርጋሉ፡፡

4 ወርቅ፤4ብር እና 4 ነሐስ - በለንደን ኦሎምፒክ

ከስምንት ዓመት በፊት በተካሄደው የአቴንስ ኦሎምፒክ የኢትዮጵያ ቡድን 7 ሜዳልያዎች ማግኘቱ ይታወሳል -  2 ወርቅ፤3 ብርና 2 ነሐስ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ ደግሞ 4 ወርቅ፤ 2 ብርና 1 ነሐስ በድምሩ 7 ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ ዘንድሮ ለንደን ላይ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 4 ወርቅ 4 ብርና 4 ነሐስ ለመውሰድ አቅዷል፡፡ ይህ እቅድ ከተሳካ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ ትልቁ ውጤት ሆኖ ሊመዘገብ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኤግዚክዩቲቭ ዲያሬክተር አቶ ታምራት በቀለ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ ቡድን በለንደን ኦሎምፒክ በሚካፈልባቸው ውድድሮች ከአራት ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ የተመዘገበውን የሜዳልያ ውጤት 50 በመቶ የማሳደግ እቅድ አለው፡፡

ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ባለፈው አንድ አመት “የአገራችን ህዳሴ በኦሎምፒክም ይደገማል” በሚል መርህ ከፍተኛ ዝግጅቶችን በስፋት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ምንጊዜም በእቅዳችን የምናስመዘግብውን ስኬት ከፍ እያደረግን ነው የምንሰራው ያሉት አቶ ታምራት፤ በዘንድሮው የኦሎምፒክ ቡድን ዝግጅት በስልጠና መሻሻል፤ በተተኪ ምርጥ አትሌቶች መብዛት፤ በባለሙያዎች ክትትል መጠናከርና በህብረተሰቡ ሰፊ ድጋፍ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በለንደን ኦሎምፒክ እንዳሰብነው 12 ሜዳልያዎች -  4 ወርቅ፤ 4 ብርና 4 ነሐስ መሰብሰብ አያዳግተንም ብለዋል፡፡ “የኢትዮጵያ አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ያስመዘገቡት ስኬት ሲታይ ከሜዳልያ ውጭ እንሆንበታለን የምንለው ውድድር አይኖርም” ሲሉም ተናግረዋል - ዳይሬክተሩ፡፡

ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አስደናቂ ብቃት እያሳየች ያለችው የአጭር ርቀት ሯጯ ፋንቱ ሚጌሶ እንዲሁም ሌላው የአጭር ርቀት ሯጭ መሃመድ አማን የሜዳልያ ድል የጠበቅንባቸው ወጣት አትሌቶች ናቸው ያሉት አቶ ታምራት፤ በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች በዓመቱ ትልልቅ ውድድሮች ያሸነፉና በፈጣን ሰዓታቸው ቀዳሚ ደረጃዎችን የያዙ አትሌቶች መኖራቸው ተስፋ ይሰጠናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ስር ስኮላርሺፕ ያገኙ ገንዘቤ ዲባባን ጨምሮ ስምንት አትሌቶች መኖራቸውን የገለፁት ዲያሬክተሩ፤ በእነሱም የሜዳልያ ተስፋ መሰነቁን ጠቅሰዋል፡፡ የኦሎምፒክ ኮሚቴው በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒያድ በአራት የስፖርት ዘርፎች ለመሳተፍ ቢያቅድም በሁለት የስፖርት አይነቶች ብቻ ነው ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶች  ማግኘት የቻለው - በአትሌቲክስ እና በዋና ስፖርት፡፡

ኮሚቴው  ለለንደን ኦሎምፒክ  ቡድኑ የዝግጅት” የጉዞ እና ሌሎች ወጭዎች መሸፈኛ የ30 ሚሊዮን ብር በጀት እንደሚበቃው አቅዶ የነበረ ቢሆንም አሁን ወደ 52 ሚሊዮን ብር አድጓል፡፡  በገቢ ማሰባሰቡ ላይ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ድጋፍ እየሰጠን ነው ያሉት አቶ ታምራት በቀለ፤ በኦሎምፒክ መድረክ የሚመዘገብ አመርቂ ውጤት የአገርን መልካም ገፅታ በመገንባት፤ የጀመርነውን የልማት ጉዞ በማጠናከርና የአገራችንን ስፖርት የመሰረተ ልማት አቅም በማስፋፋት ለተያያዝነው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ታምኖበታል ብለዋል፡፡ በተለይ በኤስኤምኤስ መልእክት- ሞባይል፤ቴሌቭዥን፤ ላፕቶፕና ሌሎች ሽልማቶችን በእጣ 2 ብር እያስከፈልን ገቢ ለማሰባሰብ ስንሰራ” ህዝቡ ምን ያህል ለኦሎምፒክ ትኩረት እንደሰጠና ስፖርቱንም ለመደገፍ ምን ያህል እንደተነሳሳ አረጋግጦልናልም ብለዋል፡፡ ለለንደን 2012 ኦሎምፒክ ጌምስ እየተደረገ ያለው ብሔራዊ ዝግጅት” በተሳካ መልኩ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ያካሄደው ግምገማ አመልክቷል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የልዑካን ቡድናችን ድጋፍ ለማሰባሰብ በተደረገው እንቅስቃሴም እስካሁን ከተለያዩ ተቋማት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ለመስጠት ቃል ተገብቷል ያለው የፅህፈት ቤቱ መግለጫ ፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለንደን 2012 ኦሎምፒክ ጌምስ የተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎችን በማሳተፍ እየተደረገ ያለውን ብሔራዊ ዝግጅት ሰሞኑን ሲገመግም፤  በአትሌቶች ስልጠና ፣ በገቢ በማሰባሰብና በኮሚዩኒኬሽን ረገድ የተከናወኑ ስራዎች በታቀደው መልኩ መቀጠላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አቶ ታምራት በቀለ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኤግዚክዩቲቭ ዳይሬክተር ግምገማውን መነሻ በማድረግ እንደተናገሩት፡፡  ባለፉት ሁለት ወራት በተለይ ገቢን በማሰባሰብ በኩል በተከናወኑት ስራዎች ከክልላዊ መንግስታት ፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም  ከዜጎች የተገኙት የገንዘብ ድጋፎች”  ህዝባችን አገራችን በኦሎምፒክ ያላት የውጤታማነት ታሪክ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳየበት እና ለጀግኖች አትሌቶቻችንም የሚሰጠውን ክብር ያመለከተ ነው ፡፡

በገቢ ማሰባሰብ እንቅስቃሴው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ወገኖች በድምሩ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ለመስጠት ቃል መገባቱን የጠቀሱት አቶ ታምራት፤ ቁጥሩ በሚቀጥለው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ መጠን እንደሚያድግ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ሀገራችንን በለንደን ኦሎምፒክ የሚወክሉ አትሌቶችን ለማዘጋጀት በተዘረጋው የስልጠና ፕሮግራም አልፈው ሚኒማ አሟልተው የተመረጡ የማራቶን ተወዳዳሪዎች ከሰሞኑ ይፋ መደረግ ተጀምሯል፡፡  አቶ ታምራት አትሌቶቹ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ተጠቃለው ወደተዘጋጀላቸው ሆቴል እንደሚገቡና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴም ለዝግጅቱ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ሁሉ በማሟላት ሀላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

ባለፈው ረቡዕ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለለንደን 2012 ኦሎምፒክ ገቢ ማሰባሰቢያ እያካሄደ ባለው የSMS ሎተሪ ተካፍለው ላሸነፉ ዕድለኞች ያዘጋጀውን የሽልማት ፕሮግራም ታዋቂ አትሌቶች በተገኙበት አካሂዷል፡፡ በአዲስ አበባ ዋቢ ሸበሌ በተከናወነው 3ኛው ዙር የሽልማት ፕሮግራም ላይ ለ40 ዕድለኞች የቴሌቭዥን ፣ የላፕቶፕ እና የሞባይል ስልኮች ሽልማቶች የተሰጠ ሲሆን ሽልማቱንም ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ፣ አትሌት ገ/እግዚአብሔር ገ/ማርያምና  ሌሎችም ዕንግዶች አበርክተዋል ፡፡ የሽልማት ፕሮግራሙ ለአዲስ አበባ እና አካባቢዋ የ SMS ሎተሪ ዕድለኞች ብቻ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታምራት፤ የክልል አሸናፊዎች በየአካባቢያቸው ሽልማቱን ሊቀበሉ የሚችሉበትን ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንደሚያመቻችም አክለው ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  የለንደን ኦሎምፒክን ምክንያት በማድረግ ባዘጋጀው የSMS ሎተሪ ዕጣ እስካሁን ከ 170 ባላይ ዕድለኞች የልዩ ልዩ ሽልማት አሸናፊ ሲሆኑ በቀጣይም የመኖሪያ ቤትና ሌሎች ክፍተኛ ዕጣዎች መዘጋጀታቸውን መረዳት ተችሏል፡፡ በሰኔ ወር መጨረሻ ትልልቅ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ኩባንያዎች፤የመንግስት ተቋማት እና ባላሀብቶችን በማሰባሰብ የሚደረግ የእራት ግብዣ በኦሎምፒክ ኮሚቴው የሚዘጋጅ ሲሆን የገቢ ማሰባሰቡ ማጠቃለያ ሆኖ በዚህ ግዜ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ያቀደውን 52 ሚሊዮን ብር ወይም ከዚያም በላይ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡

በምናሰባስበው ገቢ ለንደን ኦሎምፒክን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የስፖርት ልማት ስራዎችንም ለማከናወን አቅደናል  የሚሉት  አቶ ታምራት በቀለ፤ ወደፊት ስፖርቱ በራሱ አቅም እንዲተዳደር ስለምንፈልግ ለዚህ የሚያግዙንን መሰረተልማቶች ለመጀመር እንደመነሻ ልንጠቀምበት አስበናል ብለዋል፡፡ ንፋስ ስልክ አካባቢ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ላይ የአዲስ አበባ መስተዳድር 120ሺ ካሬ ሜትር እንደሰጠ የገለፁት ዲያሬክተሩ በዚህ ቦታ የኦሎምፒክ ኮምፕሌክስ ለመገንባት እቅድ መኖሩን፤ ቢሾፉቱ ላይ አንድ የስፖርት ማእከል ለመስራት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለመደጎም መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ለኦሎምፒኩ ከ70 በላይ የልዑካን ቡድን ይዞ ለመሄድ መታሰቡን የገለፁት አቶ ታምራት፤ በለንደን አፍሪካን ሃውስ በተባለ ስፍራ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ጋር  በመተባበር በኪራይ በሚገኘው 25 ካሬ ሜትር ቦታ የአገራችንን መልካም ገፅታና የኢንቨስትመንት ምቹነት ለማስተዋወቅ መድረክ አለን ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች በአፍሪካ ሃውስ በየቀኑ ስለአገራቸው  በኦሎምፒኩ ለሚገኙ የተለያዩ አገራት ስፖርተኞችና ህዝቦች፤ ለዲያስፖራዎች፤ ለሚጎበኙን ሁሉ ኢትዮጵያ ባላት ጥሬ ሃብት፤ በሰው ሃይል ብዛት እና በኢንቨስትመንት ምፁነቷ ያሉ መልእክቶችን በማስተላለፍ እንደሚሰሩም  ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪ በለንደን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋርም በመቀናጀት የሚያዘጋጃቸው ሁለት ትልልቅ የግብዣ መድረኮች የሚኖሩት የኦሎምፒክ ኮሚቴው አትሌቶች በየትምህርት ቤቱ እና በዩኒቨርስቲዎች በመገኘት በሚሰጡት መግለጫ ሰፊ ተግባራትን ለማከናወን አቅዷል፡፡

በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፏችን የቀድሞ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ጀግኖች በስፋት አብረው እየሰሩ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ታምራት በቀለ ሰሞኑን በሴኤሜስ ለተዘጋጀው ሎተሪ ላሸነፉት አትሌት ምሩፅ ይፍጠር እንዲሸልም መደረጉን ጠቅሰው በተለይ ኃይሌ ገብረስላሴ የኦሎምፒክ ቡድኑን አትሌቶች በአንድነትና በብሄራዊ መንፈስ እንዲሰሩ በግሉ ጥረት በማድረግ አርዓያ ሆኗል ብለዋል፡፡

 

የሄንግሎ ፍጥጫ

በሆላንድ ሄንግሎ ከሳምንት በኋላ የሚደረገው የ10ሺ ሜትር ውድድር ላይ 1ኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚወስዱት በቀጥታ ለኦሎምፒክ ያልፋሉ ያሉት የአትሌቶች ተወካይ ጆስ ሄርማንስ ናቸው የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ሶስተኛውን አትሌት ለመምረጥ እና ተጠባባቂውን ለመያዝ ሰፊ አማራጭ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡  ሄንግሎ ኃይሌና ቀነኒሳ የ5ሺ 10ሺ ሜትር የሰበሩባት ከተማ ናት፡፡ ኃይሌ በ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር  “ሚር ሄንግሎ” ተብሎ በተወደሰባት የሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊወዳደር አስቧል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በበኩሉ በ10ሺ ሄንግሎ ላይ ባይሮጥም በኦሎምፒክ ቡድኑ ሊያዝ የሚችለውን ሶስተኛ ኮታ ያለተቀናቃኝ ሊወስድ ይችላል እየተባለም ነው፡፡  በሆላንድ ሄንግሎ የ10ሺ ሚኒማ ለማግኘት ኢማና መርጋ፤ ስለሺ ስህንና ገብረ እግዚአብሄር ገብረማርያም ተሳታፊ ናቸው፡፡ኃይሌ ገብረስላሴና በበርሊን የማራቶን  ሪኮርዱን  የነጠቀው ኬንያዊ ፓትሪክ ማኩ  በማንችስተር የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መገናኘታቸው ትኩረት ሳበ፡፡

በለንደን ኦሎምፒክ አለመሳተፋቸውን ያረጋገጡት ሁለቱ አትሌቶች የማንችስተሩን ፉክክር  በማራቶን ሪኮርድ ታሪካቸው አማካኝነት ወሳኝ አጋጣሚ አድርገውታል፡፡ ኃይሌ ለለንደን ኦሎምፒክ ያልደረሰው 18 የኢትዮጵያ አትሌቶች ለኦሎምፒክ በሚያበቃ  ሚኒማ ከእሱ የተሻለ ፈጣን ሰዓት አስመዝግበው ለአራቱ የማራቶን አትሌቶች ኮታ በመፎካከራቸው ነው፡፡  የ26 ዓመቱ ፓትሪክ ማኩ ደግሞ በኬንያ የኦሎምፒክ ቡድን ከጉዳት ጋር በተያያዘ አስተማማኝ አይደለም ተብሎ ሳይመረጥ ቀርቷል፡፡ ኃይሌ የማንችስተር የ10 ኪሎ ሜትር ውድድርን በተከታታይ ለ4ኛ ዓመት ለማሸነፍ የሚወዳደር ሲሆን ማኩ ከማራቶን ሪከርዱ በኋላ ያገኘው አዲስ ምእራፍ መሆኑን በመግለጽ ተሳትፎው እንዳጓጓው ተናግሯል፡፡

በ10ሺ ሜትር የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው ኃይሌ በ39 ዓመቱ  ሩጫ ገና አልበቃኝም ማለቱን የዘገቡት የእንግሊዞቹ ዘ ጋርድያንና ዴይሊ ቴሌግራፍ ናቸው፡፡ ኃይሌ በለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን የመሳተፍ ፍላጎቱ የተበላሸበት ከ2 ወር በፊት ነበር፡፡ በጃፓን ቶክዮ ማራቶን በአረተኛ ደረጃ ያስመዘገበው 2 ሰዓት ከ08 ደቂቃ ከ17 ሰኮንዶች የሆነው ሰዓት ለሚኒማው የበቃ ነበር፡፡ ከ2 ሰዓት  ከ 04 ደቂቃ ያላቸው ከ18 በላይ አትሌቶች መኖራቸው የመመረጥ እድሉን አጥብቦታል፡፡

በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ያለው ኃይሌን ከለንደን ኦሎምፒክ አልቀረም ለማለት ይቻላል፡፡ በአገር ውስጥ ብሄራዊ የኦሎምፒክ ቡድኑን በማስተባበር  እየሰራ ነው፡፡ ከአገር ውጭ ደግሞ የቅርብ ጓደኞቹ ከሆኑት የኦሎምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ሃላፊዎች እንደአምባሳደር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡  የኦሎምፒክ ተሳትፎ ያመለጠው ኃይሌ ለዓለም አቀፍ ውድደሮችም እጁን አልሰጠም፡፡  ከ2 ሳምንት በፊት የዓለም የማራቶን ሪኮርድ በሴቶች ካስመዘገበችው እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ጋር በቪዬና ግማሽ ማራቶንም ተሳትፎ ነበር፡፡ በወቅቱ ለፓውላ ራድክሊፍ 7ደቂቃ 52 ሰኮንዶች አቫንስ ሰጥቶ ልዩውን ውድድር ያደረገው ኃይሌ ሊያሸንፋት ችሏል፡፡ ሁለቱ ምርጥ አትሌቶች ብዙ የጋራ ነገር አላቸው፡፡ በሁለቱም ፆታዎች የማራቶን ሪኮርድ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት በቦስተን በተደረገ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በታዳጊዎች ውድድር የመጀመርያ ዓለም አቀፍ ሜዳልያቸውን ያገኙ ናቸው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ሁለቱም በማራቶን ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ በለንደን ማራቶን መሳተፍ መጀመራቸውም ይታወሳል፡፡

የዩጂን ትንቅንቅ

ከ2 ሳምንት በኋላ በአሜሪካዋ ኤራጎን በሚደረገውና ከ2012 የዳይመንድ ሊግ 14 ውድድሮች አንዱን በሚያስተናግደው የዩጂን ፕሮፈንታይኔ ክላሲክ ውድድር ላይ ትኩረት የሳበው በ5ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለና ሞፋራህ መገናኘታቸው ነው፡፡በለንደን ኦሎምፒክ ለወርቅ ሜዳልያ ድል ከተጠበቁ 10 የዓለም ምርጥ ኦሎምፒያኖች የኢትዮጵያን ከፍተኛ የኦሎምፒክ ውጤት የያዘው ቀነኒሳ በቀለ አንዱ መሆኑን ከሳምንት በፊት የዘገበው ሂንዱስታን ታይምስ ነው፡፡

የጃማይካው ዩስያን ቦልት፤ የአሜሪካዎቹ ማይክል ፊሊፕስና አሊሰን ፊሊክስ፤  የኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ በዘገባው በለንደን ለአገራቸው እርግጠኛ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያ እንደሚወስዱ ከተገመቱት ይገኙበታል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሎምፒክ በ10ሺና በ5ሺ ድርብ የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበውና የሁለቱን  ርቀቶች የፍጥነት ክብረወሰኖች ለረጅም ግዜ ይዞ በመቆየት አዲስ ሪከርድ ዘንድሮ የያዘው ቀነኒሳ ለ 2 ዓመት በጉዳት ርቆ ቢቆይም ለኢትዮጵያ እርግጠኛ የወርቅ ሜዳልያ ድል በመጠበቅ ባለፈው ሁለት ወር ስሙ በዓለም ሚዲያዎች ተነስቷል፡፡

ቀነኒሳ በለንደን ኦሎምፒክ የሚቀርበው በ5ሺ እና በ10 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎቹ ታጅቦ ሲሆን በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ታሪክ ትልቁን ውጤት ያስመዘገበበትን ክብር በተሻለ ሊያሳድግ እድል ኖሮት ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ በ10ሺ እና በ5ሺ ሚኒማ ያላስመዘገበ ሲሆን በዩጂን የ5ሺ ሚኒማውን ለማምጣት ተስፋ ያደርጋል፡፡

በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ለለንደን ኦሎምፒክ ሚኒማ ለማምጣት በዚሁ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ከመሆናቸውም በላይ በ800ሜ እና በ1500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የሚወዳደሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ይኖራሉ፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዩጂን በሚደረገው ውድድር በተለይ ለኦሎምፒክ ቡድን የሚመርጣቸውን የ10ሺ ሜትር አትሌቶች ለመለየት አቅዷል፡፡ በዩጂን ፕሮፎንታይኔ ክላሲክስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር ከ43 በላይ የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያዎችን የሰበሰቡ 17 አትሌቶች መሳተፋቸው ደማቅ ፉክክር እንዲጠበቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች እርስ በእርሳቸው ለኦሎምፒክ ሚኒማ ከባድ ትንቅንቅ ያደርጉበታል በሚባለው በዚህ ውድድር የአሜሪካና የእንግሊዝ አትሌቶችም በተቀናቃኝነት ተደምረውበታል፡፡ በዩጂን በ800 ሜትር አስቀድመው ሚኒማ ያመጡት ፋንቱ ሚጌሶና መሃመድ አማን  ይሮጣሉ፡፡ ሚኒማቸውን ለማግኘት በ1500 ሜትር ትዝታ ቦጋለ እና ብርቱካን ፈይሳ፤ በ10ሺ ሜትር ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ ፤ ሱሌ ኡትራ፤ ውዴ አያሌው፤ በላይነሽ ኦልጅራ፤ ትእግስት ኪሮስ ፤አበበች አፈወርቅ፤ ወርቅነሽ ኪዳኔ ፤ አሃዛ ኪሮስና አበሩ ከበደ ይሳተፋሉ፡፡

 

 

Read 1467 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 12:48