Monday, 10 December 2018 00:00

ወርቃማ ህጎች!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ (አተአ)
Rate this item
(8 votes)

 ወርቃማው ህግ 1 - የተቸገረን (ሁሉ!) እርዳ !?
ወርቃማው ህግ የገባት አንድ ባኪ የምንላት ዝንጀሮ ነበረችን፡፡ አንድ ቀን የምትኖርበት አካባቢ በጎርፍ ተጥለቀለቀ አሉ፡፡ ሜዳዎቹም፣ ጫካዎቹም ተጥለቀለቁ፡፡ ባኪም ከአንድ ዛፍ አናት ተንጠላጥላ ወጣችና ቁጭ አለች፡፡ በዚያች ቅጽበት ከውሃ ውስጥ አንዲት አሳ ትጮህ ነበር - ‹‹አድኑኝ! ጎርፍ ወሰደኝ!›› እያለች፡፡
ዝንጀሮዋም ጩኸቱን እየሰማች ዝም ማለት አልቻለችም፡፡ በዛፉ ላይ ወደ ታች ወርዳ አሳዋን ከውሃው ውስጥ መንጥቃ አወጣቻትና ከዛፉ አናት ላይ አስቀመጠቻት፡፡ አሁን ሁሉም ሰላም ነው ስትልም አሰበችና ጋደም ብላ እንቅልፏን ትለጥጥ ጀመር። ያደረገችው በጎ ነገር የሚያስደስት እንደሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡ ግና ምን ያደርጋል፣ አሳ ያለ ውሃ እንዴት ይኖራል፡፡ ከጎርፍ የወጣችው አሳ በውሃ እጥረት ትቃትት ያዘች፡፡
በድጋሚ ‹‹አድኑኝ! እርዱኝ ወደ ውሃው መልሱኝ!›› የሚል ጩኸት ይሰማ ጀመር፡፡ ማን ሰምቶ፡፡ ዝንጀሮዋም እጅግ ተናዳባት ነበር፡፡ ምንድነው እንዲህ ያለ ነገር፣ አንዴ አውጡኝ አንዴ አውርዱኝ እያሉ መጮህ፤ አለችና ተመልሳ ተጋደመች፡፡
***
ለእረፍት ገጠር ከአያቶቼ ቤት የሄድኩ ግዜ፣ አንድ እሁድ ማለዳ መደቤ ላይ እንደተጋደምኩ፣ በጭላንጭል እያጨነቆርኩ በማለዳ የሚካሔደውን እታዘባለሁ። እማመይ (ሴት አያቴ) በጧት ተነስታ የሰንበት ቡና ታጫጭስ ነበር፡፡ ወዲያው ደግሞ ወደ በሩ ብቅ አለችና ወደ ውጪ ትጣራለች… ‹‹…. አበቡ … አበቡ … እስኪ እባክሽ ከከሰሉ ጨምሪልኝ፣ ደግሞ ወተቱን ለጌታመሳይ እለቢለት ቶሎ፡፡››
የአበቡ ድምፅ በሩቁ ይሰማኛል፡፡ ምናልባትም ከጓሮው ክምር አካባቢ እንዲህ ትላለች፤ ‹‹… እመይ ደግሞ ፊት ይሰጡታል!  አሁን እሱ ትልቅ ሰው ነው፡፡ እዚህ ቢሆን ኖሮ እንዲያውም ልጅ ወልዶ ለትምህርት ቤት ያደርስ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ይሁን ብለው ነው በጦም ወተት ይሰጠው የሚሉ! ሆሆይ! … ያቺ ድመት እንኳ አሁን አትጠጣም፡፡ ከቴም ልጁ ከተማ ሲገባ ቀበጠኮ!…›› … አበቡ ያሳደገችኝ ሰራተኛችን ናት። ምንም ብትል ከመሳቅ ውጪ አልናገርም፡፡ ኸረ እንዲያውም ጨከን ብላ አይሆንም ብትል ላልጠጣ እችላለሁ፡፡ በዚያ ላይ አባበይ ይህንን ከሰሙ አለቀልኝ።
‹‹…አይ እንግዲህ በጧት አትጀምሪኝ፤ ልጄን በሚፈልገው መልኩ እንጂ በዚህ ዕድሜው የሚበላውና የሚጠጣውን እኔ እየመረጥኩ አደለም የምሰጠው። ከተማ ሲኖር የሚበላውን እኛ እየሰጠነው መሰለሽ! ይልቅ ቶሎ ቡሬን እለቢ…››
እያጉተመተመች ስትናገር ይሰማኛል፡፡ ‹‹…እመይ እኔኮ ሚገርመኝ፣ የቡሬ ወተት ጦም የሌለው ሆኖ ነወይ! ያለሱ አይጠጣም እንዴ፤ ይልቅ ይቀስቅሱልኝ ጥጃዋን እንዳጣባ ያግዘኝ…››
‹‹ተይው ባክሽ አሁን ይተኛበት፡፡ ሊያርፍ መጥቶ አንችን ጣለበት፤ እስከዛሬ ማን ያግዝሽ ነበር!…››
‹‹ይሁን ግዴለም፤  ግን እመይ ጌትዬንስ ለዚያች መጎጥ አንድረውም፤ ምነውቴ!…››
‹‹ኸረ በህግ አምላክ! … የፃድቁ ያለህ! ደሞ ይህን ወሬ ከየት አመጣሽ!…››
‹‹እንግዲህ አገሬው የሚያወራው ነው … የጋሽ አየለን ልጅ ሊያገባት ነው ተብሏል! ደግሞኮ እርሷ እምቢ አለች ይላሉ፡፡ የኔን ጌታመሳይ አግኝታ ነው፡፡ ድንቄም እቴ፤ የሰው ልክ አለማወቅ፡፡ የኛ ልጅ ቅብርር ያለ ጌታ ነውኮ!….››
እማመይ ቀስ እያለች ትስቃለች፡፡ ‹‹..በይ ዝም በይ። ወሬና ሳቅ አይደበቅ! ይላሉ፡፡ ሆሆይ…››
የምሰማው ነገር እየገረመኝ እኔ ራሴ ሳቄ መጣ። ማናት የጋሽ አየለ ልጅ፡፡ ደግሞ ማነው ሊድረኝ ያሰበው፡፡ አያቴ መቼም አያርፍምኮ! በራሱ ካመነበት የሚያደርገው ነገር ብዙ ነው፤ የማንንም ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ የጋሽ አየለ ልጅ ትንሷ ‹አይናለም› መሆን አለባት መቼም፡፡ ያቺ ቆንጆ ልጅ፡፡ በውነት የገጠር ልጅ ከመሆኗ ውጪ (በአለባበሷና በአነጋገሯ ከከተሜዎቹ ስለምትለይ!) የአዲስ አበባ ልጆች ከእርሷ ጋር አይወዳደሩም! ታስከነዳቸዋለች፡፡ ደግሞ ቀላል ቆንጆ ናት! ግን መቼም እኔ አልጠየኩ፡፡ ላግባ አላልኩ፡፡ ዳሩኝ አላልኩ፡፡ በዚያ ላይ አያቴ መክሊትን (እጮኛዬን) ታውቃታለች፡፡ እንደምትወዳትም አውቃለሁ፡፡ አባባ ግን ከወራት በፊት ‹ለምንድነው እንዲህ ሳታገባ ብቻህን የምታባትተው!› ብሎ እንደጠየቀኝ አስታወስኩ፡፡
እመይ … ቀስ ብላ ወደ ቤት ተመለሰችና ከሰሉ ላይ ጭሳ ጭሷን ጣል አድርጋ ስራዋን ቀጠለች፡፡ የእድሜ ጣመን ያዛለው ሰውነቷ ለስንፍና ፊት አይሰጥም እንጂ ደካክማለች፡፡ አሁንም ልክ እንደ ድሮው በለሊት ተነስታ ስራዋን እስከ ውድቅት ትቀጥላለች፡፡ የመድሃኒያለም ያለህ! ምን ያለው ብርታት ነው ግን!
ጥቅልል ካልኩበት መደቤ ላይ የጧት እንቅልፍ እያንጎላጀኝ ቢሆንም፣ ፊቴ ፈገግታ እንደሞላው የተጠቀለልኩበትን ብልኮ በቀስታ ገልጬ ብርሃን በሚፈሩ አይኖች አስተውላለሁ፡፡ አባበይ ከቤተ ክርስቲያን መመለሻ ሰዓታቸው ስለደረሰ (እንዲያውም ረፍዷል!) ቁርሱ ሁሉ ተዘገጃጅቷል፡፡ አሻግሬ በበሩ ወደ ውጪ በትንሽ በትንሹ ብን ብን የሚለውን ዝናብ እከታተላለሁ፤ ቀስ ብዬ ጋቢዬን በላዬ ላይ ጠቀለልኩና ተነስቼ እየተጎተትኩ ወጣሁ፡፡ ማለዳው እጅግ ያምራል፣ ካፊያ ነገር ያለ ቢመስልም ቀኑ ግን ብሩህ ነበር፡፡
የአጥሩን በር ከፍቼ ወደ ሜዳው ወጣሁ፡፡ ማዶ ላይ ከፊት ለፊታችን የተገተረው ተራራ በማለዳው በእሳት የተያያዘ ይመስል በእንፋሎት ጭስ ተሞልቷል። በተራራው መቀነት ላይ እንደ ባልቴት ንቅሳት የሚታየው የእግረኛ መንገድ ላይ ነጭ የለበሱና ከቤተ ክርስቲያን የሚመለሱ የሰፈራችን አባወራዎችና እማወራዎች ይታዩበታል፣ አልፎ አልፎ በማለዳ የሚጓዙ እግረኞች ይዞሩታል፣ እንስሳት የሚነዱ የሰፈሩ ሰራተኞችና እረኞች በየማለዳው ይንከላወሱበታል። ደግሞ (አሁንም በዚህ ዘመን፣ አለም ሰልጥኖ ስንት በሚራቀቅበት ወቅት!) እንስራ ያዘሉ ባልቴቶችና ልጃገረዶች ሸክሙን በወገባቸውና በዳሌያቸው ላይ እያጫወቱ በየዕለቱ፣ ማልደውና አረፋፍደው ሳይመላለሱበት አይውሉም፡፡
ተራራው ላይ ከተጠቀጠቀው ጢሻ ውስጥ የሚሰማኝ የእንስሳት ጩኸት፣ የከተማ ግርግር ሲሰለቸኝ በልቡናዬ የማስበው ውብ ዜማዬ ነው፡፡ ባሻገር የሚያስካካውን የቆቆች ድምፅ መቼም ልረሳው የምችለው አይደለም፡፡ (ሳንባዬን በንጹህ አየር ሞልቼ አይኔን እንደጨፈንኩ ቆምኩ!) …. አውቃለሁ ደግሞ ከዚያ … ከማዶ ከተራራው መሃል ቀበሮዎች አሉ፣  ከዚያ ከጠፍጣፎቹ አለቶች አናት ዝንጀሮዎች፣ ደግሞ ከስር ከበሃ ድንጋዮቹ ውስጥ ጅቦች፣ በዚያ ባሻገር በርቀት ላይ ጃርቶችና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩበት፣ በስሩ ካለው ጫካ ውስጥ ሰስና አጋዘኖች፣ ደግሞ ከምንጩ አካባቢ … (በድጋሚ ሳንባዬን በአየር ሞላሁና በረጅሙ ተነፈስኩ …. ይህ የማወራው ገጠር ላልኖረ ሰው እንዴት ሊገባው ይችላል!) … ደግሞ ከትዝታዎቼ አንዷን ሳብ አድርጌ አያለሁ! … አቤት! ... አያቴኮ በራሱ ሀሳብ ብቻ ነው የሚመራው! አንድ ጊዜ እንዲህ አደረገኝ ፡፡
***
አንድ ጊዜ ገና በአስራዎቹ ዕድሜ እያለሁ … አያቴ ወደ ገበያ ይዞኝ ሄደ፡፡ በዚያን ወቅት እኩያዎቼ በራሳቸው ገበያ ደርሰው የሚመጡ ቢሆንም እኔ መሄድ አይፈቀድልኝም ነበር፡፡ የ11 ክፍል ተማሪ እያለሁ አስተማሪዬ ከሴቶች ጋር እያወራሁ እንደዳስቸገርኩት ነገረውና አባበይ ተናደደብኝ፡፡ ምዬ ተገዝቼ ብናገርም አልሰማኝም፤ ከዚያም … ‹‹ለዚህ ለዚህማ ከመንደር አትውልም ወይ!…›› … ብሎ ድብን አድርጎ ገረፈኝ፡፡ እየማልኩ ባስረዳውም አላመነኝም፡፡
ስለዚህ በሚቀጥለው የገበያ ቀን ለመጀመሪያ ግዜ አብሬው ገበያ ወሰደኝ፡፡ የሚገርም አጋጣሚ ነበር … ሰውንም፣ እንሰሳውንም፣ አቧራውንም፣ ዝንቡንም፣ ትንኙንም … እንደ አዲስ በመገረም ሳስተውል ዋልኩ (ሁሉም ቀድሞ የማውቃቸው ነገሮች አልመሰሉኝም ነበር!)… ስራችንን ጨርሰን አመሻሽ ላይ ወደ ቤታችን መመለስ ስንጀምር ከከተማው አንድ ስርቻ ይዞኝ ሄደ። ከዚያም ጭፈራና ሁካታ ወደ ሞላበት ቤት ገባን። ሰው ቤቱን ሞልቶ ይጯጯሃል … (…እኔ በቀያችን ከገበያና ከንግስ በዓል ውጪ እንዲህ ሰው የበዛበት ቦታ አይቼ አላውቅም ነበር፡፡) …. በቤቱ ውስጥ ጠርሙስና ብርጭቆዎች ይዘው ወዲያ ወዲህ እያሉ ስራውን ከሚያቀላጥፉት ውጪ ዝም ብለው የቆሙ ኮበሌዎች በጣም ብዙ ናቸው፡፡  ሙዚቃው ከቤቱ የሚወጣ አይመስልም፣ እዚህም እዚያም የሰከሩ ሰዎች፣ ደግሞ ሴቶችን የሚጎተትቱና ወደ ጓሮ የሚሰወሩ፣ ደግሞ የሚሰዳደቡና ለጠብ የሚጋበዙ፣ ደግሞ ከቴፑ በላይ ድምፃችን ይሰማ እያሉ የሚጮኹ፣ ደግሞ … ምን ዓይነት አገር ነው! (ምን ዓይነት ነገርስ ነው!) … ፔፕሲዬን እያጣጣምኩ ተቁለጨለጭኩ፡፡ (በወቅቱ ጥቁር ለስላሳ ነበር የምለው!)
አያቴ አንዷን ልጅ መሳይ ጠራትና አነጋገራት (…በኋላ ስሰማ የቀያችን ልጅ ናት ሲሉ ሰማሁ፣ ወጣቱ ሁሉ ከገበያ መልስ መጀመሪያ እርሷ ዘንድ ይሄዳል ይላሉ!) … በመቀጠል አየት አደረገኝና ወደ ጆሮዬ ጎንበስ ብሎ ‹‹አብረሃት ሂድ!›› አለኝ፡፡ እየተጠራጠርኩ ተከተልኳት፤ በተደቋቆሱት ቤቶች ስር ወደ ውስጥ ከአንዷ ጎጆ ዘልቅንና በሩን ከኋላዬ ዘጋች። ትንሽ ከተቁለጨለጭችብኝ በኋላ በትዕዛዝ መልክ … ‹‹ልብስህን አውልቀዋ! … ›› አለችኝ (ግራ ገባኝ!)
‹‹…አባትህ አለማምጂው ብለውኝ ነውኮ! … ወይኔ! እኔ እንዲያው ስንቱን ገበሬ ሳለማምድና ሳሰለጥን ልኑር! … በተለይ ከዚያ አገር የምትመጡ ቆምጨዎች! …›› ከላይ የለበሰቻትን ሹራብ ጎትታ አወጣችና ስትጥላት እንኮይ የመሰሉ ጡቶች ከፊቴ ተንጠለጠሉ፡፡ ደነገጥኩ … አይቼ አላውቅም ነበር፡፡
‹‹…ደግሞ ከሴት ጋር መተኛት ምን ልምድ ያስፈልገዋል፤ እያንዳንዱ ያገርህ ገበሬ በጨለማ እየዳበሰ አይደል እንዴ የሚያገኘው፡፡ ልክ ፍትፍት እንደ መጉረስ ማለት ነውኮ፡፡ መብራት ቢጠፋም እጅህ አፍህን አያጣውም…›› ረጅም ሳቅ … ‹‹..በልቶሎ አውልቀዋ፤ ደግሞ አንተ ትንሽ የምትሻል ትመስላለህ፤ ልብስህም ንፁህ ነው!፤ እንዲያው በሞቴ የከንፈር ወዳጅ የለህምና ነው!…›› … ለደቂቃዎች ደነዘዝኩ፡፡ ለመጀመሪያ ግዜ ባየሁት ነገር የደነገጥኩና የደም ስሮቼ ሁሉ የተገታተሩ ቢሆንም በመቀጠል ያደረግሁት አስደንጋጭ ነገር ነበር፡፡ ገፍትሬ ከእንጨት አልጋው ላይ ፈነቸርኳትና በሩን ታግዬ ከፍቼ ወጣሁ፣ ከዚያም … በሩጫ ድቁስቁሱን ሰፈር አቋርጩ የአገሬን መንገድ እስካገኝ ሮጥኩ፡፡ ከገበያተኞች ጋር አብሬ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ፤ አያቴ የሰራኝ ስራ ግን … (ተቀየምኩት!)
ማታ ሲመጣ እየሳቀ ነበር … እኔ በጣም ተቀይሜዋለሁ፤ እየሳቀ እንዲህ አለኝ … ‹‹….ጌታ! … አስተማሪህ ሴት ለምዷል ብሎ ሲከስህ ተጠራጥሬህ ነበር፡፡ በርግጥ ልጄን እኔ አውቅሃለሁ፡፡ ግና መቼስ አስተማሪ አስተማሪ ነው፡፡ እና ከዚያ ቤት ያስገባሁህ ልፈትንህ ነበር፡፡ በሃሰት ስለከሰስኩህ ይቅርታ አድርግልኝ…›› (… ድንቄም ፈተና፣ ለንቦጬን ጣልኩ… ደግሞ በኋላ ሲነግረኝ … ከልጅቱ ጋር ተመካክረው ኖሯል! በጉርምስና ድፍረት አንቄ ብይዛት ኖሮ ግን…!)
አንገቴን ቀልሼ ዝም አልኩት፡፡ እናም ለቀናት አኮረፍኩት፡፡ በርግጥ ፈተናውን አለፍኩ ማለት ነዋ! ብወድቅስ! ምን ሊፈጠር ነበር ….  አያቴን ከዚያ ወዲህ አላምነውም፡፡  
***
እናም በመጨረሻ አበቡ የዕድሞውን በር ከፍታ ብቅ አለችና እንዲህ አለች፤ ‹‹…አንተ ጌታ! … በብርድ ምን ይገትርሃል፡፡ በል ቶሎ ግባ አባበይ ደርሰዋል፡፡ ደግሞ ሳይመጡ ወተትህን ጠጣ … አንዴ ክርህን በጥሰህ ጥለህ … ሆሆይ መቅበጥ!…››
‹‹…አቤ እንዲያውም አንቺ ከምትቀየሚ ወተቱን ትቼዋለሁ አልጠጣም!…›› አልኩ ጋቢዬን እየሰበሰብኩ።
‹‹…ኸረግኝ…አላማረብህም ላንተ አደል በጧት የተለፋው!…በል ቶሎ ና ግባና ጠጣ፡፡ አንድ ጊዜ ጀምረሃል ጨርስና ትጠመቃለህ!››
ልብሴን እያስተካከልኩና እየሳቅኩ ተጠጋኋት፤ ወዲያው ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መመለሻ ቀኔ መድረሱን አስብና ልቤን ስልብ የሚያደርግ ስስት ይሰማኛል፤ አዝናለሁ፡፡  ነጠቅ ነጠቅ በሚያደርግ እርምጃ ከአጠገቧ ደረስኩና በስራ እንደ ሞረድ የሻከሩ አሳዳጊ መዳፎቿን አንስቼ ሳምኳቸው፡፡
‹‹አይይይ …. እንደው ይህንን ልጅ ምናባቴ ላድርገው!›› እያለች መዳፏን ነጠቀችኝና እንባዋን ከአይኖቿ መጠራረግ ስትጀምር፣ እድሞውን ዘልቄ በፍጥነት ወደ ቤት ገባሁ፡፡ እውን አሁን ደግሞ አባባ ልዳርህ እያሉ ሊያጨናንቁኝ ባልሆነ እያልኩ በልቤ እያሰላሰልኩ፣ በኩባያ ላይ የተቀዳውን ትኩስ የታለበ ወተት ማጣጣም ጀመርኩ፡፡
***
ወርቃማው ህግ 2 - የምትረዳውን ለይ! (የምታደርገው … ሊደረግልህ የምትፈልገውን ብቻ ነው!)
ኪባ የምትባል ሌላ ዝንጀሮም ነበረች፡፡ እንዲሁ ከሌላኛው ዛፍ ነበረች፡፡ እናም የሌላውን አሳ እሪታ ስትሰማ አሰላሰለች፡፡ ‹‹ይህንን አሳ ከውሃው በማውጣት ማዳን ይኖርብኛልን! እኔስ በአሳው ቦታ ብሆን ኖሮ፣ ከውሃው እንዲያወጡኝ እፈልግ ነበርን!›› ስትል ጠየቀች፡፡
እናም ‹‹አይደረግም! ከውሃው እንዲያወጡኝ አልፈልግም!›› ስትል ወሰነች፡፡ እናም አሳው በውሃው ውስጥ ቁልቁል ሲምዘገዘግ ከዛፉ አናት ቁጭ ብላ አየችው፡፡ ጭካኔ አይደለም፡፡ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢሰቃይም በህይወት የመኖር ዕድሉ ግን ሰፊ ነው ስትል ወሰነች፡፡ ይህ የብልህ ውሳኔ ነው ስትልም አሰበች፡፡

Read 3167 times