Monday, 10 December 2018 00:00

እስኪ ተስፋ አበድሩኝ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(4 votes)


    አንዳንድ ቁርቋሶ፤ መንገድ መዝጋት፤ የሥራ ማቆም አድማ፤ የተቃውሞ ሰልፍ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቡድን ግጭት፤ የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ትንታኔና ዘገባ፤ የፖለቲካ ቡድኖች ሽኩቻና ክስ፤ የዜጎች መፈናቀል፤ አንዳንድ የብሔሮች ሥር የመስደድ አዝማሚያ መከተል የጀመረ መቃቃር፤ ቁጣና መቀያየም፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲደማመሩ፤ ተስፋ መቅኖ ያጣል፡፡ ‹‹ሁሉን ነገር ወደ ራሷ የምትጠራው ጠራችኝ፤ ከመሄድ በቀር ሌላ ምንም ምርጫ የለኝ›› እንዳለ ፀሐፊው፤ ተስፋ ማጣት ጉልበት እያገኘች፤ ሁሉን ነገር መጥራት እየጀመረች ነው፡፡ ግን ቅጽበት በዘላለም ላይ እንዴት ሥልጣን አገኘች?  
የተስፋ ነገር ሲነሳ፤ ሁለት ነገሮችን አስታውሳለሁ፡፡ አንደኛው የጋራችን የመሆን ዕድል አለው፡፡ ሌላኛው የኔ ብቻ መሆኑን አምናለሁ፡፡ የብቻ ከሆነው እጀምራለሁ።
ይህች አዲስ አድማስ ጋዜጣ በተወለደች ሰሞን፤ እንደ ‹‹ፎረስ ጋሙ›› ባለ ታሪክ ትረካ የሚወደው፤ የጋሞው አሰፋ ጫቦ ‹‹ቁርሳችን ሎንዶን ነው›› በሚል የጻፋት አንዲት መጣጥፍ ከተስፋ ጋር ተያይዛ በትውስታ ትመጣለች፡፡ አሁን የአሰፋን ጽሑፍ አልነካውም፡፡ ይልቅስ አሰፋ ጫቦን ከባህል አፈር ዘግኖ፤ እፍ ብሎ የሰራውን የጋሞው ህዝብ ውለታ እዘክራለሁ፡፡ በዚያ ከምድራችን ማስተዋል የጠፋ መስሎ በታየበት፤ ሽማግሌ ጠፋ ብለን በተከዝንበት፤ የክፉ ቀን አለኝታ አድርገን የምንመለከተው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ከቦታው ጠፍቶ ግራ በተጋባንበት በዚያ ሰዓት፤ ሣር ነጭተው፤ በጉልበታቸው ተንበርክከው የሽማግሌ ወግ ያሳዩን የጋሞ አባቶች፤ የአባቶቻቸው ልጆች የሆኑት የጋሞ ወጣቶች ተስፋ ሰጡን፡፡
በዚያ ድቅድቅ ጨለማ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ፤ የብርሃን ጎርፍ መስሎ፤ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ደምቆ በታየው የጋሞ አባቶች ድርጊት ተስፋችን ትንሳዔ አገኘች፡፡ ቂም፣ ፀብ እና ጥላቻ በልባቸው ውሎ ቢያድር፤ ተጨማሪ አቅም አግኝቶ ወደ አዲሱ ቀን እንዲሸጋገር የማይፈቅዱለት ጥበበኞቹ ጋሞዎች፤ ተስፋ በጠፋ ጊዜ ተስፋ ሆኑን፡፡ አባቶች ከተቀበሉኝ፤ እኔም ከእንግዲህ ጋሞ ነኝ፡፡
ታዲያ ቅድም እንዳልኩት፤ ከዚህ ድንቅ ማህበረሰብ የተወለደው አሰፋ ጫቦ ‹‹ቁርሳችን ሎንዶን ነው›› በሚል ርዕስ የጻፋት ጽሑፍ ሁሌም የተስፋን ነገር ባሰብኩ ቁጥር ትዝ ትለኛለች፡፡ የሰው ልጅ በተስፋ ማጣት ላይ ሲነግስ የምናይበት ጽሑፍ ነው። ‹‹ታይታኒክ›› በተሰኘው ፊልም ውስጥ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾቹ ሁኔታ ትዝ አይላችሁም፡፡ መርከቢቱ ስትሰጥም፤ ሰው ህይወቱን ለማትረፍ እንዲያ ሲራኮት፤ ሙዚቀኞቹ ሲጫወቱ ቆዩ፡፡ አደጋው አምርሮ ሲመጣ ራሳቸውን ለማዳን እንደ ነገሩ ጥረት አደረጉ፡፡ ግን ከንቱ መፍጨርጨር መሆኑን ተረዱት፡፡ እናም መለስ ብለው ሙዚቃ መጫወታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሞት በዙሪያቸው ሲሯሯጥ እያዩ ናቁት፡፡ ሞት እንዲያ የተዋረደበት ሌላ አጋጣሚ አላስታውስም፡፡ ሞት አፍንጫውን ሲያሸት እያየ፤ ትከረት እና መናበብን የሚጠይቅ ህብረ ዝማሬ መሥራት ከቀጠለ፤ ተፈጥሮ ነባር ህጓን አፍርሳ፤ ሙዚቀኞቹን እንደ ኢየሱስ በውሃ እንዲራመዱ ማድረግ ነበረባት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ትዕይንት ሰው በመሆኔ እንድኮራ ያደርገኛል፡፡ የጋሞ ሽማግሌዎችን ድርጊት በዚህ ደረጃ የማስቀምጠው ነው፡፡ ጋሞዎች ወገኖቼ በመሆናቸው፤ ሰው በመሆን ቀረብ ያለ ኩራት ይሆነኛል፡፡ አሁን ችግሬ ተስፋ ነው፡፡ እስኪ እንደ ጋሞዎች ተስፋ አበድሩኝ!  
የተስፋ ነገር ሲነሳ የማስታውሰው እና የጋራችን የመሆን ዕድል አለው ያልኩት፤ በግሪክ ሐተታ አማልክት የተሰነደውን ነገረ-ፓንዶራን ነው --‹‹የፓንዶራን ሣጥን።›› እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ሣጥኑ የሜርኩሪ ሣጥን ወይም የኤፒሚቲየስ ሣጥን ቢባል ነበር ትክክል፡፡ የሆነ ሆኖ፤ የታሪኩ ከያኒዎች የፓንዶራ ሣጥን ብለውታል፡፡ ስለዚህ፤ ‹‹እንግዳ ሲያፍር የጋባዡን ሚስት ያጎርሳል›› ከሚያሰኝ ነገር ለመጠበቅ፤ ‹‹የፓንዶራ ሣጥን›› እያልን እንቀጥል፡፡ በእጅጉ የሚያሳስብ ችግራችንን በምሣሌ እና በትረካ ለመግለጽ የምሞክረው፤ ከችግሩ በላይ የመሆን አቅም ለማግኘት ነው፡፡
እንደምታስታሱት፤ በ9/11 በአሜሪካ የተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ካስከተላቸው የተለያዩ ተፅዕኖዎች መካከል አንዱ የቀልድ መጥፋት ነው፡፡ የተለያዩ ሚዲያዎች ማንም ሳያዛቸው የቀልድንና የሳቅ ዝግጅቶችን ለተወሰነ ጊዜ ዘግተው ነበር፡፡ ከዚያ ዘግናኝ እና አስደንጋጭ ክስተት ማግስት፤ በአሜሪካውያን ዘንድ የታየው ቀልድ የመስማት እና የመናገር ጉልበት ማጣት ወይም ቀልድን እንደ ነውር ነገር የማየት ልዩ የስሜት መሳሳት (ስሱነት)፤ በሽብር ጥቃቱ የተፈጠረውን ትራጄዲያዊ ድባብ ይበልጥ እንዲጠናከር ያደረገ ተጨማሪ ነገር ሆኖ ነበር፡፡ እንዲያውም አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ‹‹የ9/11 ክስተት አንዳንድ የቀልድ ዓይነቶች ከአሜሪካ ህብረተሰብ ዘንድ ጨርሶ እንዲጠፉ ምክንያት የሆነ ክስተት ነው›› እስከማለት ደርሰው ነበር። ለወትሮው፤ በአሜሪካ (የእሳት ቃጠሎን የመሰሉ) ከባድ አደጋዎች ሲከሰቱ፤ ወዲያው በርካታ ቀልዶች ይፈለፈላሉ፡፡ ሆኖም በ9/11 ያ የተለመደ የአሜሪካውያን ባህርይ አልታየም፡፡
ችግሩን የተረዱት የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ሩዶልፍ ጊዩሊያኒ (Rudolph Giuliani)፤ ‹‹ሰዎች መሣቅ ጀምሩ›› የሚል ግልጽ ትእዛዝ አስተላለፉ። ከንቲባው በአደባባይ ንግግር በሚያደርጉበት አንድ አጋጣሚ ‹‹እኔ ዛሬ ከመሐላችሁ የተገኘሁት፤ የመሣቅ ፈቃድ ልሰጣችሁ ነው፡፡ ትዕዛዜን በማክበር ካልሣቃችሁ፤ ሁላችሁንም እስር ቤት እከታችኋለሁ›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ እኔም የፓንዶራን ታሪክ ማሄጂያ አድርጊያለሁ፡፡ ናትናኤል ሃውተርን የተረከውን እኔ አሳጥሬ ሳቀርበው እንዲህ ነው፤
ገና በፍጥረት ማለዳ፤ ይህች የምንኖርባት ምድር በአፍላዋ ሳለች፤ አንድ ኤፒሚቲየስ የሚሉት ልጅ ይኖርባት ነበር፡፡ ኤፒሜቲየስ አባትም ሆነ እናት አልነበረውም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሲኖር ሳለ፤ እንደ እርሱው አባትም ሆነ እናት ያልነበራት አንዲት ልጅ፤ ውሃ አጣጭ፣ አጋር እና አጫዋች ትሆነው ዘንድ ከሩቅ ሐገር ተላከችለት፡፡ ስሟም ፓንዶራ ይባል ነበር፡፡ ፓንዶራ ገና ወደ ኤፒሜቲየስ ጎጆ እንደ ገባች ቀድሞ ከዓይኗ የገባው፤ አንድ በጣም ትልቅ የሆነ የእንጨት ሣጥን ነው፡፡ ገና ሳትቀመጥ፤ ‹‹በዚያ ሣጥን ያስቀመጥከው ነገር ምንድነው፤ ኤፒሜቲየስ?›› አለችው፡፡
ኤፒሜቲየስ፤ ‹‹ለሰው የሚነገር ነገር አይደለም። ምስጢር ነው፡፡ እባክሽ ስለዚህ ነገር ዳግም ጥያቄ እንዳታነሽብኝ፡፡ ሣጥኑ ከእኔ ዘንድ የተቀመጠው በብርቱ በአደራ ነው፡፡ አደራዬን አክብሬ በጥንቃቄ ከመያዝ በቀር፤ እኔም በውስጡ ምን እንዳለ አላውቅም›› ሲል መለሰላት፡፡
‹‹እሺ፤ ግን ማነው ለአንተ የሰጠህ?›› አለች ፓንዶራ፤ ‹‹ከየትስ ነው የመጣው?››
‹‹እርሱም ምስጢር ነው›› ብሎ መለሰላት ኤፒሜቲየስ፡፡
‹‹ምን ዓይነት ዕረፍት የሚነሳ ነገር ነው›› አለች ፓንዶራ፤ ለምቦጯን እንደ መጣል አድርጋ፡፡ ‹‹ይህን ሣጥን ከዚህ ቤት አውጥቶ የሚጥልልኝ ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር›› አለች፡፡ እናም የብስጭት ስሜት ያደረባት መሰለች፡፡
‹‹አንቺ ደግሞ፤ በቃ እርሺው›› አላት ኤፒሜቲየስ፡፡ ‹‹ይልቅ ተነሺ፤ ወጣ ብለን ከልጆቹ ጋር እንጫወት፡፡››
ኤፒሜቲየስ እና ፓንዶራ በምድር መኖር ከጀመሩ ሺህ ዓመታት አሳልፈዋል፡፡ ግን ሁሉም ከልጅነት ዕድሜአቸው አልወጡም፡፡ ችግር፣ ጭንቀት እና አደጋ የሚባሉ ነገሮች የሚታዩበት ዓለም ስላልነበረ፤ ልጆቹ የእናት እና የአባት እንክብካቤ እና ጥበቃ አያሻቸውም። የሚበላው እና የሚጠጣው ነገር የተትረፈረፈ ነበር። ማንኛውም ልጅ የሚበላውን ነገር ከዛፍ ላይ ተንዠርግጎ ያገኘዋል፡፡ ለራት ቀጥፎ የበላው ነገር፤ ጧት ለቁርስ ሲነሳ እንደገና በቅሎ - በስሎ ያገኘዋል፡፡ ባይገርማችሁ፤ ጸብ፣ ጭቅጭቅ እና ጭንቀት የሚባል ነገር አይታወቅም፡፡ ልጆቹ አንድም ቀን አልቅሰው አያውቁም፡፡ እኒያ ትናንሽ ክንፎች ያሏቸው፤ መከራ ወይም ችግር የሚባሉ አስቀያሚ ፍጥረቶች ገና በምድር አይታዩም፡፡ ምናልባት፤ በልጆቹ ዘንድ የሚታወቅ የመጨረሻ ክፉ ሊባል የሚችል አንድ ብቸኛ ነገር ቢኖር፤ ፓንዶራ እንቆቅልሽ በሆነው በዚያ ሣጥን ያለውን ምስጢር ማወቅ ባለመቻሏ የተፈጠረባት የሚጎረብጥ ስሜት ነው፡፡
እንዲያውም መጀመሪያ ላይ ያ ጎርባጭ ስሜት የችግር ጥላ እንጂ ችግር ለመባል የሚበቃ ነገር አልነበረም፡፡ ግን ዕለት በዕለት ጥንካሬው እያደገ ይሄድ ነበር፡፡ ‹‹ይኸ ሣጥን ከየት ይሆን የመጣው›› ትላለች ፓንዶራ ዘወትር፡፡ ‹‹በውስጡስ የተቀመጠው ምን ነገር ይሆን?››
‹‹አንቺ ዘላለም ስለዚህ ሣጥን ነው የምታወሪው?›› አለ ኤፒሜቲየስ፤ ‹‹ስለ ሌላ ነገር ብታወሪ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነይ፤ ወጣ ብለን የበሰለ ሾላ ለቅመን፤ ራታችንን ከዛፉ ሥር ቁጭ ብለን እንብላ፡፡ ቀምሰሽው የማታውቂው፤ ውሃ የሞላው እና በጣም ጣፋጭ የሆነ የወይን ፍሬ የት እንዳለ አሳይሻለሁ፡፡››
‹‹አንተ ደግሞ ዘላለም ስለ ሾላ እና ወይን ነው የምታወራው›› በማለት ጮኸች ፓንዶራ፤ እንደ መቆጣት ብላ፡፡
‹‹በቃ እሺ፤ እየሮጥን ሄደን ከልጆቹ ጋር በመጫወት ደስ የሚል ጊዜ እናሳልፍ፡፡››
‹‹እኔ መዝለል እና መፈንጨት ስልችት ብሎኛል›። ይህን አስቀያሚ ሣጥን! ዘወትር ስለእርሱ ነው የማስበው፡፡ ኤፒሜቲየስ፤ በውስጡ ምን እንዳለ ልትነግረኝ ይገባል!››
‹‹ሺህ ጊዜ ነገርኩሽ፤ አላውቅም›› ብሎ መለሰላት፤ ትንሽ ስሜቱ ጎሾ፡፡
‹‹ለማወቅ ከፈለግህ መክፈት ትችላለህ›› አለችው ፓንዶራ፤ አግድም እያየችው፡፡
ኤፒሜቲየስ በእምነት የተሰጠውን ሣጥን የመክፈት ሐሳብ መነሳቱ ብቻ እጅግ የዘገነነው መሰለ፤ እንዲህ ያለ ሐሳብ ዳግም እንዳታነሳበት እየተመኘ፡፡ እርሷም አያይዛ ‹‹እሺ፤ ቢያንስ  ከአንተ ዘንድ እንዴት እንደ መጣ ንገረኝ›› አለችው፡፡
‹‹በቃ፤ ከበር ተቀምጦ አገኘሁት›› አለ ኤፒሜቲየስ፤ ‹‹አንቺ ከእኔ ዘንድ ከመምጣትሽ ትንሽ ቀደም ብሎ፤ ፊቱ በፈገግታ ፀዳል የደመቀ እና ጠቢብነቱ  በግልጽ የሚታይ አንድ ሰው አምጥቶ ከደጅ አስቀመጠው። ሣጥንኑን ከደጄ ሲያስቀምጥ፤ ሣቁን መቆጣጠር አቅቶት ነበር፡፡ አሮጌ ካባ ደርቦ፤ ከአናቱ ክንፍ ያለው እና በከፊል ከላባ የተሰራ የሚመስል ባርኔጣም አድርጎ ነበር፡፡››
‹‹በእጁ ምን ዓይነት በትር ይዞ ነበር?›› ፓንዶራ ጠየቀች፡፡
‹‹ኧረ፤ የያዘው ዱላ አይተሸው የማታውቂው ግራ አጋቢ ዱላ ነው›› አለ ኤፒሜቲየስ፤ ‹‹ሁለት እባቦች ከላይ እስከ ታች የተጠመጠሙበት ይመስላል፡፡ ዱላውን በመፈልፈል የሰሯቸውን እባቦች መጀመሪያ ስታያቸው፤ በዱላው ላይ በእውን ያሉ ህያው እባቦች እንጂ፤ ፈጽሞ እንጨት ተፈልፍሎ የተቀረፁ አይመስልሽም፡፡››
‹‹አወቅኩት›› አለች ፓንዶራ፤ በሐሳብ እንደተዋጠች፤ ‹‹በቃ ሜርኩሪ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር እንደዚያ ያለ በትር የሚይዝ የለም፡፡ እኔንም ሣጥኑንም ወደዚህ ያመጠው እርሱ ነው፡፡ ርግጠኛ ነኝ፤ ይህን ሣጥን ያመጣው ለእኔ ነው፡፡ ምናልባት በሣጥኑ ለእኔ እና ለአንተ የታሰቡ መጫወቻ አሻንጉሊቶች እና የምንለብሳቸው ቆንጆ ቆንጆ ልብሶች ተቀምጠው ይሆናል፡፡››
‹‹ይሆን ይሆናል›› አለ ኤፒሜቲየስ፤ ‹‹ሆኖም ሜርኩሪ ተመልሶ መጥቶ ክፈቱት ካላለ፤ ማናችንም ይህን ሣጥን የመክፈት መብት የለንም›› አለ ፊቱን ወዲያ መልሶ፡፡ ከዚያም ፓንዶራ ከመጣች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻውን ከቤት ወጣ፡፡ ፓንዶራ ሣጥኑን በመደነቅ ተመለከተችው፡፡ ከመጣች ጀምሮ ‹ይህ አስቀያሚ ሣጥን› እያለች ስትጠራው የነበረችው ዕቃ፤ በየትኛውም ቤት ቢቀመጥ፤ ለቤቱ ውበት የሚያጎናጽፍ ምርጥ ዕቃ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ አሰበች፡፡
ስለ ሣጥኑ ብዙ ስታስብ ቆይታ፤ ብዙ የስሜት እና የሐሳብ ግብግብ ስታደርግ ቆይታ፤ ኤፒሜቲየስ ቢመጣ ምን ይለኛል እያለች ስታወጣ እና ስታወርድ ቆይታ፤ ‹‹ከፍቼ ትንሽ ሰረቅ አድርጌ አይቼ መልሼ እዘጋዋለሁ›› በሚል ለመክፈት ወሰነች፡፡ እናም ከቁልፉ ጋር ትግል ጀመረች፡፡ ለየት ያለ ቁልፍ ነው፡፡
ኤፒሜቲየስ ውጭ ሲጫወት ሳለ ከዚህ ቀደም ተሰምቶት የማያውቀው የመጨነቅ ስሜት ተሰማው። ይህን የተመለከቱት ሌሎች ልጆችም ግራ ገባቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ጎጆው ለመመለስ ወስኖ ጉዞ ጀመረ። ለፓንዶራ ለመስጠት አስቦ ከመስኩ የሊሊ፣ የጽጌረዳ እና የብርቱካን አበቦች ቀጥፎ ወደ ቤት ሲያመራ፤ እየተሳበ ወደ ፀሐይ የሚወጣ ጥቁር ደመና ተመለከተ። ጥቁሩ ደመና ሰማዩን መላው፡፡ ልክ ከጎጆው በር ሲደርስ፤ ፓንዶራ እጇን በሣጥኑ መቆለፊያ አድርጋ ነበር፡፡ ይህን የተመለከተው ኤፒሜቲየስ ድንገት ካስደነገጥኳት ሳታስበው ሣጥኑን ትከፍተው ይሆናል ብሎ በስጋት ሲያደባ ሳለ፤ እርሱም እንደ ፓንዶራ በውስጡ ያለውን ነገር የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረበት፡፡
በመጨረሻ ፓንዶራ ሣጥኑን ስትከፍተው፤ ጎጆዋ በድቅድቅ ጨለማ ተዋጠች፡፡ የነጎድጓድ ድምጽም ተሰማ፡፡ ፓንዶራ ግራ ተጋብታ እየተቅበጠበጠች ክዳኑን ክፍት ስታደርገው፤ ክንፍ ያላቸው ህልቆ መሳፍርት ፍጥረታት እየበረሩ እና ከእርሷ ጋር እየተጋጩ እና እየተሻሹ ከሣጥኑ መውጣት ያዙ፡፡ በዚያች ቅጽበት፤ ኤፒሜቲየስ ‹‹ወይኔ፤ ተነደፍኩ ወይኔ ተነደፍኩ›› እያለ መጮኽ ጀመረ፡፡ አስቀያሚ ክንፍ ያላቸው እኒያ ፍጥረታት ፓንዶራንም ሊነድፏት ከግንባሯ ሲያፍፉ፤ ኤፒሜቲየስ ደርሶ አራገፈላት፡፡ እንዲያ እየታመሱ በሩጫ በመሄድ፤ በር እና መስኮቱን ሲከፍቱ፤ ግር ብለው ወደ ውጪ ወጡ፡፡ እነዚያ አስቀያሚ ፍጡራን በምድር ላይ ተሰራጭተው የሚገኙ ዓይነታቸው የበዛ እና ለቁጥር የሚያታክቱ መከራዎች እና ችግሮች ናቸው፡፡ ቁጣ፣ ንዴት፣ ግዴለሽነት፣ ሐዘን እና ጭንቀት ወዘተ ነበሩ፡፡ ሜርኩሪ እንዳላቸው ሣጥኑን ባይከፍቱት ኖሮ ይህ ሁሉ ችግር ባላገኛቸው ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ ያ የደስታ እና የይባቤ ምድር ተበላሸ፡፡
ሁለቱም ክፉኛ ተነድፈዋል፡፡ ኤፒሜቲየስ በጣም አዝኖ ለፓንዶራ ጀርባውን ሰጥቷት ሲቀመጥ፤ ፓንዶራ ሳግ እየተናነቃት ከመሬት ተዘርፍጣ፤ ጭንቅላቷን ሣጥኑ ክዳን ላይ አድርጋ ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ ሳለች ከውስጥ በኩል ደፍ- ደፍ የሚል ድምጽ ስትሰማ፤ ድንገት ብንን ብላ፤ ‹‹ደግሞ አንተ ማነህ?›› አለች፤ ‹‹ከዚህ ከፉ ሣጥን ውስጥ ያለኸው ማን ነህ?›› ስትል፤ ‹‹አንድ ድምፁ ያማረ ፍጥረት፤ ‹‹ክዳኑን እንሺው፤ ያኔ ታይኛለሽ›› አላት፡፡ አሁን ፓንዶራ እምቢ አለች። ግን በተናገረ ቁጥር  ድምፁ ያባብላታል፡፡ ‹‹አሁን ጅል አልምሰልህ፤ እነዚያ አስቀያሚ እህት ወንድሞች ያደረሱብኝ ነገር ይበቃኛል›› በማለት እምቢ አለችው። እርሱም መልሶ፤ ‹‹እኔ የእነሱ ዓይነት አይደለሁም፡፡ ከከፈትሽው ራስሽ ታረጋግጫለሽ፤ እኔ የነሱ ወንድም አይደለሁም›› አላት፡፡ ድምፁ የሚያማልል በመሆኑ እምቢታዋ ሊፀና አልቻለም፡፡ ስለዚህ ፓንዶራ እና ኤፒሜቲየስ ተመካክረው፤ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› በሚል ስሜት ተጋግዘው ሣጥኑን ከፈቱት፡፡ ከሣጥኑ እንደ ፀሐይ ብርሃን የደመቀ ፀዳል ያላት አንዲት እንግዳ ፍጥረት በክፍሉ ውስጥ እየበረረች፤ በመከራ የተነደፈውን የኤፒሚቲየስን ግንባር ስታሽለት ህመሙ ታገሰለት፡፡ ፓንዶራንም ስትስማት እፎይታ ተሰማት፡፡
‹‹ተመስገን፤ አንቺ ውብ ፍጥረት ማን ትሰኛለሽ?››› አለች ፓንዶራ፡፡
‹‹እኔ ተስፋ እሰኛለሁ›› በማለት አብረቅራቂዋ ፍጥረት መለሰች፡፡ ‹‹እኔ እኒያ የመከራ መንጋዎች ከሣጥን በወጡ ጊዜ፤ ሰዎችን በማጽናናት ለማገዝ በሣጥኑ እንድገባ የተደረኩ ነኝ›› አለች፡፡
ሁለቱም ከአጠገባቸው እንዳትርቅባቸው ለመኗት። ‹‹እናንተ በምድር እስካላችሁ ድረስ እኔ አብሬአችሁ ለዘላለም እኖራለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሌለሁ መስሎ ሊሰማችሁ ይችላል፡፡ የሌለሁ መሆኔ በርትቶ በተሰማችሁ ጊዜ፤ የክንፎቼን የብርሃን ፍንጣቂዎች ሲያንፀባርቁ ታያላችሁ፡፡ ፈልጉኝ ታገኙኝማላችሁ፤ ቃል ኪዳኔን እመኑ፤ ለዘላለም ከእናንተ አልለይም›› አለች ተስፋ፡፡
 ሁለቱም እናምንሻለን አሏት፡፡
ከዚያ ወዲህ፤ የተለያየ መከራ መጥቶ በአናታቸው እየዞረ ሲያንዣብብባቸው፤ ሁለቱም ተስፋን በትዕግስት ይጠብቋታል፡፡ የቀስተ ደመና ህብረ ቀለም ያለው ውብ ክንፍ የታደለችው ያች ፍጥረት፤ መከራ በጎበኛቸው ጊዜ እየመጣች ትፈውሳቸዋለች፡፡ ታጽናናቸዋለች፡፡
እንግዲህ አሰፋ ጫቦ፤ በ‹‹ቁርሳችን ሎንዶን ነው›› ጽሁፉ የገለጻት፤ የእርሱ ዘመዶች የሆኑት የጋሞ ሽማግሌዎች፤ በደም በሥጋ አግዝፈው ያሳዩን፤ በፓንዶራ ታሪክ አሁን የተመለከትናት፤ ጠፋች ብለን የተጨነቅንላት፤ አባቶቻችን አጽንተው ያቆዩዋት፤ ሆሜር የጠቀሳት፤ ሄሮዱቱስ የዘከራት፤ ነቢዩ መሐመድ ያወሷት፤ የአረብ ባለቅኔዎች ያከበሯት የኢትዮጵያዊነት ወግ ጋሞጎፋ ጨንቻ ግድም ብቅ ብላ አረጋግታ አጽናናችን፡፡
ከጓዳ እና ከአደባባይ የሽማግሌ ድምጽ ሲጠፋ፤ የፍቅር ድምፁ ሲከፋ፤ የእምነት ሚዛኑ ሲደፋ፤ ‹‹እንኳን ሰው ግንድ ያድናል›› ይባል በነበረበት ሐገር፤ ቤተ ክርስቲያን እና መስጊድ ገብቶ ከአጥቂ መዳን እንደማይቻል አይተን፤ ተስፋ በቆረጥንበት ጊዜ፤ የተስፋ ፀሐይ ካልተገመተ አቅጣጫ ደምቃ ስትወጣ አየን፡፡ ዋርካ ሣይሆን እርጥብ ሣር መከታ ሆኖ አየን፡፡
እንደ ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ፤
‹‹ይኖር ይሆን ወይ አርማ፣ ይኖር ይሆን ወይ ባንዲራ፤
ሰውን የመሰለ ቀለም ያለው፣ ሰውን የመሰለ አሻራ›› ስንል ነበር፡፡
እንደ ታላቁ የኪነ ጥበብ ሰው፤ እንደ ዮፍታሔ ንገሤ፤
‹‹አይኔ ሰው እራበው፤ ዓይኔ ሰው እራበው፤    
“የሰው ያለህ የሰው፣  የሰው ያለህ የሰው” እያልን ሳለ ከጋሞዎች መንደር ምላሽ አገኘን፡፡ ይህ ተዐምር የሆነው፤ በትንሣዔ እንድናምን ነው፡፡ ግን በሐገራችን የፓንዶራን ሣጥን የከፈተው ማነው? ብዙዎቻችን ሌሎች ይመስሉናል፡፡ ግን ሁላችንም ተካፍለናል፡፡
 እኔስ አዘንኩ ለዚህ አምባ እኔስ አዘንኩ ለዚህ ዘመን፤
ለሚፎክት ለሚሰቃይ፣ በመጻጉአን ደረመን፤ ይላል ደበበ በ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ››
እስኪ ተስፋ አበድሩኝ ጎበዝ?!

Read 5191 times