Tuesday, 04 December 2018 11:56

ማደግ ከፈለግን፣ እንከባበር!

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(2 votes)

ከሁለት ወራት በፊት በቡራዩ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተጎዱ ወገኖች ቴዲ አፍሮ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተከትሎ፣ በማኅበራዊው ሚዲያ ላይ የደረሰበትን ትችትና ዘለፋ አስመልክቶ የተሰማኝን ቅሬታ በፌስቡክ ገጼ ላይ አሥፍሬ ነበር፡፡ በጊዜው በጽሑፌ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤ “ዘፋኝና ዘፈን አገር አያቀናም፣ አገር የምትበለጽገው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቻ ነው” የሚል ይገኝበት ነበር፡፡ ለዚህ አስተያየት፤ “ሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቻ?” የሚል ጥያቄ-አዘል ምላሽ ስሰጥ፣ “አዎ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ብቻ!” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ነበር የተሰጠኝ፡፡
ከአስተያየት ሰጪው ጋር በሐሳብ ለመግባባት ሞክረን ስላልቻልን፣ ላለመስማማት ተስማምተን ነገሩ በዚሁ ቆመ፤ ከዚህ በኋላ ግን፣ አስተያየት ሰጪውን ልጠይቃቸው ይገባኝ የነበረ፣ ግን የዘነጋሁትን ጥያቄ አስታወስኩ፤ “ብቻውን አገር ያቀና ሙያ አለ?” የሚል፡፡ ምን ያደርጋል? ጊዜው ካለፈ በኋላ ሆነና ሳልጠይቃቸው በመቅረቴ ቆጨኝ፡፡ ቢሆንም፣ ይህ ርዕስ የማይሞት አጀንዳ በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ ላይ አቋሜን ለማቅረብ ወደድኩ፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ፣ በርካታ ውብ እሴቶች ያሏት አገር ብትሆንም፣ በዚያው ልክ ደግሞ በቁጥር የበዙ ድክመቶችና ከእነዚህ ድክመቶች የሚመነጩ ችግሮችን የተሸከመች ናት፡፡ ከእነዚህ ድክመቶች መካከል አንደኛው የአስተሳሰብ ድክመት ነው፡፡ የእኛ የኢትዮጵያዊያን የአስተሳሰብ ድክመት መገለጫዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለዛሬው ሐሳቤ መነሻ የሆነው፣ የአስተሳሰብ ድክመታችን መነሻ፣ ሙያን መሠረት ያደረገ መናናቅ ነው፡፡
በአገራችን በፊውዳላዊውም ሆነ ከዚያ በፊትም በነበሩት ሥርዓቶች፣ ሰዎች በሙያቸው የተነሳ መናቃቸውና መገለላቸው የተለመደ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቆዳ ሰሪውን “ፋቂ፣” ነጋዴውን “መጫኛ ነካሽ፣    “ ልብስ ሰፊውን “ክር በጣሽ፣” ሸክላ ሠሪውን “ቡዳ፣”… እያሉ መናቅ የማኅበረሰቡ ወግና ዐቢይ መገለጫ የነበረባቸው ዘመናት ሩቅ አልነበሩም፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ የማኅበረሰቡ ክፍሎች፣ ጋብቻ እስከ መከልከል፣ በአገር መቀመጫ እስከ ማጣትና አልፎ ተርፎም እስከ መገደል ድረስ መከራ ተቀብለዋል፡፡
ይህንን አግላይ አስተሳሰብ ለመቀየር ተራማጅ አስተሳሰብ የነበራቸው የአገራችን መሪዎች፣ በየሥልጣን ዘመናቸው ሙከራ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ እንደ ምሳሌም፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ጥር 17 ቀን 1900 ዓ.ም. ባስነገሩት አዋጅ፤ “ሠራተኛን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ” የሚል ጠንካራ ኃይለ-ቃል ብለዋል፡፡
ዘመናት አልፈው፣ “ኋላ-ቀር” እና “ጎታች” የተባለው ሥርዓት ፣ “አብዮታዊና ተራማጅ” በተባለው ሥርዓት ሲተካ፣ ሙያን መሠረት ያደረገ፣ የንቀትና የማግለል አስተሳሰብን ለመቀየር የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህም አንፃራዊ ለውጥ ታይቷል፡፡ ይሁንና በመንግሥት ደረጃ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ ተቋማዊውን አግላይነት ቢቀንሱም፣ ማኅበረሰባዊውን አግላይነት ሙሉ በሙሉ አጥፍተዋል ማለት አያስደፍርም፡፡ “ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መከተል ጀምረናል” በተባለበት በአሁኑ ጊዜ፣ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ነገር ቢታይም፣ አሁንም ማኅበረሰባዊው አመለካከት ሙሉ በሙሉ አልተቀየረም፡፡ በተለይ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ላይ ይህ በጣም ጎልቶ ይታያል፡፡
በመግቢያዬ ላይ ያነሳሁት የራሴ ገጠመኝ፣ ምናልባት ቀላሉ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ የባሱ አግላይ አስተያየቶችን ባለፉት ዓመታት ሰምቻለሁ፣ አንብቤያለሁ፡፡ አልፎ ተርፎም፣ ሃይማኖታዊ ካባ የደረቡ   ማግለያዎችንም በብዛት ተመልክቻለሁ፡፡ ወደ እነዚህ አስተያየቶችና ወደ ክርክሩ በዚህ ጽሑፍ ለመግባት አልፈልግም፤ ራሱን የቻለ ትልቅ ርዕስ ነውና፡፡ በእነዚህ ሐሳቦች መነሻነት ግን፣ “ሙያን ማበላለጥ አገር አያቀናም፣ አያበለጽግም” የሚለውን ሐሳቤን ለማካፈል እፈልጋለሁ፡፡
በዓለም ላይ፣ በየትኛውም አገር፣ አንድ ሙያ ብቻውን አገር አቅንቶና ገንብቶ አያውቅም፤ የግድ የሌላ ሙያ ድጋፍና ትብብር ያስፈልገዋል። የፌስቡኩን አስተያየት ብንወስድ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች፣ ሥራቸውን በንቃት ለማከናወን ሙዚቃን ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሙያዎች፣ ባለብዙ መስመር የፕሮግራም ኮዶችን ለመፃፍ ረዥም ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፣ ሥራው የሐሳብ (concept) ስለሆነ አዕምሮ በእጅጉ ይወጠራል፡፡ ይህንን የአዕምሮ ውጥረት ለማቃለል፣ ባለሙያዎቹ በሥራቸው ላይ ሆነው፣ ሙዚቃ በጆሮ ማዳመጫ እያዳመጡ፣ የሚሠሩበት ጊዜና ሁኔታ ብዙ ነው፡፡ በዋና ዋናዎቹ የዓለማችን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሚሠሩ ባለሙያዎችን በሥራ ቦታቸው ላይ ሆነው ስናያቸው፣ ይህንን በሚገባ እንመለከታለን። ሙዚቃው የባለሙያዎቹን አዕምሮ ባያረጋጋው፣ ዛሬ የምንደነቅባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማግኘት ቀላል አይሆንልንም ነበር፡፡ ይህ የቴክኖሎጂና የሙዚቃ ቁርኝት ምሳሌ፤ “ዘፋኝና ዘፈን አገር አያቀናም” የሚለውን ክርክር ውድቅ የሚያደርግ  ይመስለኛል፡፡
የሙያዎች የእርስ በርስ መደጋገፍ፣ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ እያንዳንዳችን የተቸረን  የየራሳችን ስጦታና መክሊት አለን፡፡ ፈጣሪ ለሁላችንም መክሊታችንን ሲሰጠን ያለምክንያት አይደለም፡፡  ሁላችንም በራሳችን ሙሉና ፍጹም አለመሆናችን ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም፣ የአንዳችን ችሎታና ሙያ ለሌላችን አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉ አናጢ፣ ሁሉ ግንበኛ፣ ሁሉ ጠራቢ፣ ሁሉ ለሳኝ፣… ቢሆን ቤት አይገነባም፡፡ ሁሉ ሐኪም፣ ሁሉ ነርስ፣ ሁሉ መርፌ ወጊ፣… ቢሆን ሕመምተኛ አይድንም፡፡ ሁሉ መሐንዲስ፣ ሁሉ ወታደር፣ ሁሉ መምህር፣… ቢሆንም አገር አትቀናም፣ አትበለጽግም፡፡ የእያንዳንዳችን ዕውቀት፣ ችሎታና ተሰጥኦ ድምር ውጤት ናት አገራችን። አንዳችን በምንሠራው ላይ ሌላችን የራሳችንን ጡብ እያስቀመጥን ነው፤ “ኢትዮጵያ” የምትባለውን ታላቅ አገር የገነባነው፣ የምንገነባውም፡፡
ታዲያ ለምንድን ነው የአንዳችንን ሙያ ሌላችን መናቃችን? ብቻችንን ለማንኖርባት ምድር፣ ተከባብሮ መኖር እንደምን ተሳነን? ሌላ ሰውና ሌላ ሙያ እንደሚያስፈልገን ለምን መረዳት አቃተን? ልብስ ሰፊው፣ ልብሳችንን ካልሰፋ ዕርቃናችንን ወደ ሥራችን መሄድ እንደማንችል፣ ጫማ ሠሪው ጫማ ባይሠራልን በባዶ እግራችን ወደየትም መንቀሳቀስ እንደሚሳነን ለምን እንረሳለን? እነዚህን ሰዎች ንቀን የት ልንደርስ ይሆን?
ተናንቀን አገር አንገነባም፤ እንኳን ተናንቀን፣ “ተከባብረን ኖረናል” ባልንባቸው ዘመናት እንኳን ኢትዮጵያ ከድህነት አልወጣችም፡፡ ዛሬ “አድገዋል” የሚባሉትና እኛም በባሌም፣ በቦሌም ልንገባባቸው መከራ የምናይባቸው አገራት የበለጸጉት፤ ለእያንዳንዱ ሙያ ተገቢውን ክብርና ዕውቅና ስለሰጡ ነው፣ መስጠት ብቻም ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ ሙያ መደጋገፍ፣ ለልማት አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተው ነው፡፡ ስለዚህ፣ ማደግ ከፈለግን እንከባበር!

Read 4967 times