Monday, 03 December 2018 00:00

አዋሽ ባንክ በግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛውን ትርፍ አስመዘገበ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 አዋሽ ባንክ ባለፈው በጀት ዓመት (2017/18) ባደረገው እንቅስቃሴ፣በባንኩና በግል ባንኮች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ባንኩ የዛሬ ሳምንት በሒልተን ሆቴል ባካሄደው የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ መደበኛና 15 ድንገተኛ ጉባኤ፣ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታቦር ዋሚ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ያለፈው በጀት ዓመት ለአገራችንም ሆነ ለግል ባንኮች ፈታኝ ጊዜ ቢሆንም ባንኩ ተግዳራቶችን በመቋቋምና ወደ መልካም አጋጣሚ በመለወጥ በሁሉም የሥራ ዘርፎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡንና ከታክስ በፊት ያልተጣራ 1.96 ቢሊዮን ብር ማትረፉን ገልፀዋል፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩ አጋጥሞት ከነበሩት ተግዳራቶች ዋና ዋናዎቹ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የብድር ጣሪያ መቀመጡና ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲደረግ መወሰኑ እንደነበር ጠቅሰው የተመዘገበው ውጤት ከአስር ዓመት ስትራቴጂ አኳያ እጅግ የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ያስመዘገበው 1.96 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ650 ሚሊዮን ብር ወይም የ49 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን አቶ ታቦር ጠቅሰው፣ ይህ ትርፍ ለአዋሽ ባንክም ሆነ በአገሪቷ ባሉ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛው ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላላ የባንኩ ተቀማጭ ሂሳብ ኤልሲ ማርጂንን ጨምሮ 13 ቢሊዮን ብር ወይም 40 በመቶ ዕድገት በማሳየት በዓመቱ መጨረሻ 45.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ በዓመቱ የተሰጠው 31.3 ቢሊዮን ብር ብድር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታይ የ8.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ38 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን፣ የባንኩ ጠቅላላ ገቢም አምና ከነበረበት 3.76 ቢሊዮን ብር 1.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ44 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 5.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የቦርድ ሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ወጪም 1 ቢሊዮን ብር ወይም 41 በመቶ ዕድገት በማሳየት 3.4 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው፣ ለወጪዎቹ ማደግ የወለድ ምጣኔ መጨመር፣ የሠራተኞች ደሞዝና ጥቅማጥቅም ዕድገት፣ የዕቃዎች መናርና የባንኩ የሥራ ዘርፎች መስፋት እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡
ለደንበኞች የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በኤቲኤም፣ በፓስ ማሽኖች፣ በሞባይልና በኢንተርኔት ባንኪንግ በመታገዝ የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው አዋሽ ባንክ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 50 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት ጠቅላላ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 366 ማድረሱን፣ ለወደፊት ደግሞ ዘመናዊ Contact Center እና Customer Relation Management አገልግሎቶችን ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል - የቦርድ ሰብሳቢው፡፡  
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ከ3 ዓመት በፊት ከነበረበት 25 ቢሊዮን ብር ከእጥፍ በላይ መጨመር 55 ቢሊዮን ብር መድረሱን የባንኩ ጠቅላላ ካፒታል መጠባበቂያዎችን ጨምሮ 65 ቢሊዮን ብር መሆኑን የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 2.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ባለአክሲዮኖች በሚቀጥሉት ሦስት ዓመት የባንኩን የተከፈለ ካፒታል 6 ቢሊዮን ለማድረስ በተስማሙት መሠረት በሚቀጥሉት ዓመታት የተከፈለ ካፒታሉ ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚያሳይ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመውጣት አኳያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ዘንድሮም ለበጐ አድጎት ሥራዎች 30 ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ የዲሬክተሮች ቦርድ መወሰኑን አቶ ታቦር ዋሚ ገልፀዋል፡፡

Read 4193 times