Monday, 03 December 2018 00:00

ሕብረት ኢንሹራንስ ከ120 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ አገኘ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 ሕብረት ኢንሹራንስ አ.ማ ሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ሕብረት ኢንሹራንስ ባለፈው ማክሰኞ በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው 24ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ግርማ ዋቄ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከሰተው አለመረጋጋት፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና በአጠቃላይ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖውን ቢያሳርፍም ኩባንያው ተፅዕኖውን ተቋቁሞ እቅዱን ለማሳካት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት አመርቂ ውጤት  ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ባደረገው የሥራ እንቅስቃሴ፣ግብር ከመቀነሱ በፊት ያገኘው ትርፍ 132 ሚሊዮን 274 ሺህ 489 ብር መሆኑን ጠቅሰው፣ የተገኘው ትርፍ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው ጋር ሲነፃፀር 95 ከመቶ ዕድገት ማሳየቱን፣ በዓመቱ የተመዘገበው 120 ሚሊዮን 825 ሺህ 114 ብር የተጣራ ትርፍ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው ጋር ሲተያይ፣ 26 በመቶ ብልጫ እንዳለው የቦርድ ሰብሳቢው አመልክተዋል፡፡
ኢንሹራንስ ኩባንያው የሰበሰበው አጠቃላይ የአረቦን ገቢ 473 ሚሊዮን 622 ሺህ 068 ብር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 473 ሚሊዮን 787 ሺህ ብር ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፍ፣ 35 ሚሊዮን 837 ሺህ ደግሞ ከሕይወት ነክ የመድን ዘርፍ የተገኘ መሆኑን፣ 13 በመቶ ሕይወት ነክ ካልሆነ ዘርፍ፣ 20 በመቶ ደግሞ ከሕይወት ነክ የተገኘ መሆኑን፣ ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘው 13 በመቶ የአረቦን ገቢ ዕድገት በኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ከተመዘገበው 11 በመቶ አማካይ የአረቦን ገቢ ጋር ሲተያይ መጠነኛ ብልጫ ያለው በመሆኑ የተገኘው ውጤት አርኪ ነው ብለዋል፡፡
የኩባንያው የተከፈለ ካፒታል 250 ሚሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት የቦርድ ሰብሳቢው፤ በዚህ ዓመት ሙሉ በሙሉ ከተከፈለ አክሲዮን ላይ 43 በመቶ የትርፍ ክፍያ ለባለ አክሲዮኖች እንዲከፈል የዳይሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ወደ ኅብረተሰቡ ቀረብ በማለት ተደራሽነቱን ለማስፋት ኩባንያው ባደረገው እንቅስቃሴ፤ የቅርንጫፎችና የአገናኝ ቢሮዎች ቁጥር 32 በመቶ በመጨመር 41 መድረሳቸውን፣ የኩባንያው የሠራተኞች ቁጥር በበጀት ዓመቱ 47 ሠራተኞች ተጨምረው፣ 359 መድረሳቸውን፤ ከዚህ ወስጥ 323 ወይም 90 ከመቶ ቋሚ፣ 36 ሠራተኞች ደግሞ የኮንትራት ተቀጣሪዎች መሆናቸውን አቶ ግርማ ዋቄ ገልፀዋል፡፡

Read 2468 times