Monday, 03 December 2018 00:00

4ሺ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሳተፉበት የICT ውድድር ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አሸናፊዎች ለዓለማቀፍ ውድድር እንዲመረጡ ዕድል ይሰጣል - ሁአዌ

    በዓለም በሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ግዙፉና ታዋቂው የቻይና የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁአዌይ፤ በሰሜን አፍሪካና በተቀረው የዓለም አገሮች መካከል የሚካሄድ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ውድድር በመጪዎቹ ወራት እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡
ሁአዌይ፣ ከቻይና ኤምባሲና ከትምህርት ሚ/ር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሦስተኛው የአይሲቲ ውድድር መጀመሩን ለማስታወቅ ባለፈው ማክሰኞ በትምህርት ሚ/ር የስብሰባ አዳራሽ በተደረገው ሥነ-ሥርዓት፤ በኢትዮጵያ የሁአዌ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ቲበር ዞሁ፤ ለሦስተኛ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ውድድር፣ በኢትዮጵያ የአይሲቲ ትምህርት ከሚሰጡ 20 ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 4000 ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ ገልፀዋል፡፡
የውድድሩ ዓላማ የኢትዮጵያን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማሳደግና ለማስፋፋት መሆኑን የጠቀሱት ሚ/ር ቲበር ዞሁ፤ይህ ከመንግሥት፣ ከትምህርትና ከኢንዱስትሪ የተዋቀረ ሐሳብ፣ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች እውነተኛ የሕይወት ልምድ እንዲያገኙ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር (ልውውጥ) ለማካሄድ፣ የተሻለ ሥርዓተ ትምህርት ለመቅረጽና ተማሪዎችን ለወደፊት የቅጥር ዕድሎች ለማዘጋጀት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ልዩ ውድድር ለተማሪዎች የተለየ የትምህርት ልምድ ከመስጠቱም ባሻገር፣ በአገራቸው ተወዳድረው፣ ለዓለም አቀፍ ውድድር እንዲመረጡ ዕድል ይሰጣል ያሉት ሚ/ር ዞሁ፤ መጀመሪያ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ 4000 ተማሪዎች ይወዳደራሉ፡፡ እያንዳንዱ የትምህርት ተቋም የአይሲቲ ፈተናዎችን በማካሄድ፣ 20 ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ይመርጣል፡፡
እነዚህ የተመረጡ አሸናፊዎች የሁአዌይ ተወካዮች በተገኙበት ይፈተኑና ብልጫ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተመርጠው፣ ለመጨረሻው አገር አቀፍ ውድድር ያልፋሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 3 አሸናፊዎች በፈተና ተመርጠው ይሸለማሉ ብለዋል፡፡
ሁአዌይ ለአሸናፊ ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለትምህርት ተቋማት ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን 1ኛ እና 2ኛ የወጡት ተማሪዎች የሁአዌይ ሜት 10 ሞዴል ተንቀሳቃሽ ስልክና ሰርቲፊኬት፣ 3ኛ ለሚወጣው ደግሞ የሁአዌይ ዋይ 7 ሞዴል ተንቀሳቃሽ ስልክና ሰርቲፊኬት ይሸለማሉ፡፡
ከተሸላሚዎቹ መካከል ሦስት ተማሪዎችና አንድ መምህር ተመርጠው በአፍሪካ አህጉር ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆነው ተማሪ፤ በቻይና ሸንዘን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድር የመሳተፍ ዕድል ያገኛል ተብሏል፡፡

Read 2581 times