Tuesday, 04 December 2018 00:00

እናት ባንክ ከታክስ በፊት 216 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

እናት ባንክ አ.ማ ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው የሥራ እንቅስቃሴ፤ ከታክስ በፊት ያልተጣራ 216 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ባለፈው ሳምንት በሚሌኒየም አዳራሽ ባደረገው የባለአክሲዮኖች 5ኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀ መንበር ወ/ሮ ሐና ጥላሁን ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፤ ባንኩ፣ ውጤማና ትርፋማ መሆኑ የባንኩን ቀጣይ ዕድገትና ብሩህ ተስፋ አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ በወዲያኛው ዓመት ከነበረበት 1.2 ቢሊዮን ብር፣ ወደ 4.97 ቢሊዮን ብር ማደጉን፣ የአስቀማጭ ደበኞች ቁጥር ከ70 ሺህ በላይ መሆኑንና ከዚህ ውስጥ 56 በመቶ ወይም 39,200 ደንበኞች ሴቶች መሆናቸውን፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 6.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህ ውጤት ባንኩ በህዝቡ ዘንድ ያገኘውን ተአማኒነትና ተቀባይነት ያመለክታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባንኩ ያገኘው ጠቅላላ ገቢ 751 ሚሊዮን ብር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ገቢ ጋር ሲተያይ የ230 ሚሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱን፣ የባንኩ ጠቅላላ ወጪ 534 ሚሊዮን ብር መሆኑን፣ በዓመቱ ከታክስ በፊት የተገኘው የ216 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ70 ሚሊዮን ብር ጭማሪና በአንድ አክሲዮን የተገኘው 18.4 በመቶ መሆኑ የተገኘውን ዕድገት ያመለክታል ብለዋል፡፡
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 671 ሚሊዮን ብር መድረሱን፣ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ15 ሺህ በላይ መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ የሴቶች ቁጥር 65 በመቶ እንደሆነና በካፒታልም ረገድ 60 በመቶ መድረሱን የጠቀሱት ወ/ሮ ሐና፤ ይህም ባንኩ የሴቶችን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት ይዞት የተነሳውን ትልቅ ራዕይ ከግብ ለማድረስ ሴቶች ከባንኩ ጎን በመሰለፍ፣ እያደረጉ ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
ደንበኞች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ጋር የሚፈጽሟቸውን ክፍያዎች በባንኩ የመረጃ መረብ በኩል እንዲያልፍ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ እየተገባደደ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት ተግባራዊ በማድረግ የደንበኞችን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብ እርካታቸውን ከፍ እናደርጋለን ብለዋል፡፡
የባንኩን ተደራሽነት ለማስፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 6 አዳዲስ ቅርንጫፎች በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል ከተሞች በመክፈት፣ የቅርንጫፎችን ቁጥር 40 ማድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
የሴቶችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሳደግ የብድር መያዣ ማቅረብ የማይችሉ ሴቶች ማሟላት ያሉባቸውን መስፈርቶች በማዘጋጀት፣ ለአምስት ሴቶች ብድር መስጠቱን የጠቀሱት ሊቀመንበሯ፣ ተበዳሪዎችም የወሰዱትን ብድር በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከመክፈል አልፈው ለ81 ግለሰቦች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንና ንብረት ማፍራታቸውን ተናግረዋል፡፡

Read 2498 times