Monday, 03 December 2018 00:00

የዲፕሎማቲክ ሚስቶች ባዛር

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ሚስቶች ቡድን አባላት፣ በየዓመቱ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር የሚያካሂዱ ሲሆን፣ የዘንድሮው ባዛር በመጪው ሳምንት ቅዳሜ ሕዳር 29፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
የማቲሪክስ ፕሮጀክት የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ረቡዕ በሂልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በየዓመቱ በርካታ የውጭ አገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን በአንድ ጥላ ስር የሚገናኙበት ብቸኛው ትዕይንት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ለአንድ ቀን በሚቆየው በዚህ ባዛር ላይ ዘጠኝ ሺህ ያህል ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት ገልጸዋል፡፡
በባዛሩ ላይ 60 ኤምባሲዎች የየአገሮቻቸውን ምግብ፣ ባህል፣ የመታሰቢያ ዕቃዎችና የሥነ ጥበብ ቅርፆች የሚቀርቡበት ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት በተደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ባዛር 4.2 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ፣ በማትሪክስ ፕሮጀክት አማካይነት ለትርፍ ላልተቋቋሙ ድርጅቶችና ለበጎ አድራጎት ማኅበራት መከፋፈሉን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክት ማትሪክስ የሴቶችን፣ የሕፃናትና እጅግ ጎስቋላ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማሟላት የዲፕሎማቲክ ሚስቶች ያቋቋሙት ማህበር ሲሆን ከባዛሩ የሚሰበሰበው ገንዘብ መቶ ፐርሰንት ለበጎ አድራጎት ተግባር ለተቋቋሙ ድርጅቶችና ማኅበራት እንደሚሰጥ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት ከተካሄዱ ባዛሮች የተሰበሰበው ገንዘብ፤ ተጠቃሚ ከሆኑ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶችና ማኅበራት መካከል ለአብነት፡- ኔክስት ዲዛይን ኮሌጅ፣ ኢየሩሳሌም አጠቃላይ ት/ቤት፣ ክብረ የአረጋውያን ምግባረ ሰናይ ድርጅት፣ ምስጋና ቻይልድ፣ የስኳር ሕመም ላለባቸው ሰዎች ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት፣ … ጥቂቶቹ ናቸው፡፡  

Read 1835 times