Print this page
Monday, 03 December 2018 00:00

ወ/ሮ ዳግማዊት በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ተደንቀዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

አፍሪካ የወጣቶች ኦሎምፒክን እንድታዘጋጅ ጠይቀዋል


    የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ANOC ሰሞኑን በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ ላይ 23ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ ሲያካሂድ የኦዲት ሪፖርት ያቀረቡት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክን አፍሪካ እንድታዘጋጅ በመጠየቃቸው በፕሬዝዳንት ቶማስ ባች ተደነቁ፡፡ የ206 ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች፤ የ5 አህጉራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበራት፤ ስፖርተኞች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን የወከሉ ከ1300 በላይ ተሳታፊዎች ጉባኤውን ታድመውታል፡፡
በጉባኤው ቶኪዮ ለ2022 ኦሎምፒክ ያደረገችውን አጠቃላይ ዝግጅትና ቀጣይ እቅዷችን ያቀረበች ሲሆን  የጉብኝት ፕሮግራምም በማሰናዳት እንቅስቃሴዎቿን ለዓለም የኦሎምፒክ ማህበረሰብ አስተዋውቃለች።  ዓለም አቀፉን የኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር የመሰረቱትንና በፕሬዝዳንትነት ከ8 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ሼክ አህመድ በ3ኛ የስራ ዘመን ለመቀጠል የነበራቸውን ፍላጎት ጉባዔው ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በሌላ በኩል ዓመታዊው የANOC ሽልማት ስነስርዓት ለ5ኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን በተለይ በ2018 የሰሜን ኮርያ ፒዮንግቻንግ ባስተናገደችው የክረምት ኦሎምፒክ ላይ በተለያዩ ዘርፎች ኮከብ የሆኑ ስፖርተኞች ተሸላሚዎች ሲሆኑ በክረምት ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት ኢኳዶር፣ ኤርትራ፣ ኮስቮ፣ ማሌዢያ፣ ናይጀሪያና ሲንጋፖር ልዩ የምስጋና ወረቀት አግኝተዋል።  የዓለም ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር ከ5ቱ አህጉራዊ የኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበራት ጋር በመተባበር በሚያዘጋጁት ዓመታዊ የሽልማት ስነስርዓት የብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎችን የላቁ ስራዎች እና በኦሎምፒክ ሙቭመንት ውጤታማ አስተዋፅኦ በመገምገም የኖርዌይ እና የጣሊያን ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስፖርት አመራሮች ተሸልመዋል፡፡
በዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ቋሚ አባልነት ያለፉትን 5 ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት ወይዘሮ ዳግማዊት በጉባኤው ላይ የኦዲት ሪፖርት ከማቅረባቸውም በላይ አፍሪካ የዓለም ወጣቶች ኦሎምፒክን በቅርብ ዓመታት ለማዘጋጀት ተስፋ እንደምታደርግ፤ መላው የአህጉሪቱ ህዝቦች ዓለምን በታላቅ የስፖርት መድረክ ለማስተናገድ እንደሚፈልጉና እንደሚጓጉ በመግለፅ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባች በበኩላቸው ይህን የመሰለ ፍላጎት ከአፍሪካ መምጣቱን በማድነቅ በአፍሪካ ያላቸውን ተስፋ አንፀባርቀዋል፡፡
የየዲኬቲ ኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር  የሆኑት ወይዘሮ ዳግማዊት ግርማይ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከ2013 እ.ኤ.አ ጀምሮ የቦርድ አባልነት እየሰሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴን በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ከ2002-2004 እኤአ ካገለገሉ በኋላ በፕሬዚዳንትነት ከ2004-2008 እኤአ የሰሩ ሲሆን በዋና ፀሐፊነት ደግሞ ከ2009-2013 እኤአ ማገልገላቸው ይታወቃል፡፡ ከ14 ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት እቅድና አስተዳደር ማስትሬት  ዲግሪያቸውን የሰሩት ወይዘሮ ዳግማዊት በ2005 እኤአ ላይ ከስዊዘርላንዱ ሉዛን ኢንስትቲዩት  በስፖርት ተቋማት አስተዳደር ተጨማሪ የማስትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
በስፖርት አስተዳደር በኢትዮጵያ ፤ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ የኦሎምፒክ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ልምድም አላቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሴቶችና የስፖርት ኮሚሽን አባልነት ከ2010-2015 እኤአ ሲያገለግሉ ቆይተው  በዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዩ ምርጫ በተለያዩ ኮሚሽኖች መስራት የጀመሩት ከ3 ዓመት ወዲህ ሲሆን በሴቶች ለስፖርት እና በፋይናንስ ኮሚሽን አባልነትም እየሰሩ ናቸው። በ2014 እኤአ በቻይና/ናይጂንግ የተካሄደውን ሁለተኛው የወጣቶች  ኦሎምፒክ ላይ ዋና አስተባባሪ ሆነው ከ2010 እስከ 2014 እ.ኤ.አ ሰርተዋል፡፡ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ በ2024 እኤአ ላይ የሚካሄደው 33ኛው ኦሎምፒያድ በአስተባባሪነት እንዲያገለግሉ የተሾሙት    ደግሞ በ2017 እ.ኤ.አ ነው፡፡
ወይዘሮ ዳግማዊት በአፍሪካ የኦሎምፒክ እንቅስቃሴ ባላቸው ጉልህ ሚና ደግሞ የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (ANOCA) አባል ሆነው እያገለገሉ ናቸው፡፡ በአህጉራዊው የኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (ANOC) ዋና የቦርድ አባል ሲሆኑ የሴቶችና የስፖርት ኮሚሽን አባልነት ከ2006 እ.ኤ.አ ጀምሮ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በባድሜንተን ስፖርት በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አክብሮትም አትርፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባድሜንተን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን ያለፉትን 18 ዓመታት ሲያገለግሉ ከመቆየታቸውም በላይ ከ2009 እ.ኤ.አወዲህ የአፍሪካ ባድሜንተን ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ሆነው በአፍሪካ ባድሜንቲን ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የሎጀስቲክ ሰብሳቢ (ከ2002-2006 እኤአ) ለ4 ዓመታት ከመስራታቸውም በላይ እንዲሁም   ከ2013 እ.ኤ.አ ጀምሮ የዓለም የባድሜንተን ፌዴሬሽን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እየመሩ ናቸው።  በተጨማሪም የኢትዮጵያ ማርሻል አርት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለ12 ዓመታት አገልግለዋል።

Read 7598 times