Monday, 03 December 2018 00:00

አትሌት ሰለሞን ባረጋ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • በዓመቱ አዲስ አትሌትና ምርጥ ፎቶ ዘርፎች አትሌት ሰለሞን ባረጋ በእጩነት ይወዳደራል
  • የ5ሺ ሜትር ሪከርድን መስበር ይፈልጋል


    የ18 ዓመቱ አትሌት ሰለሞን ባረጋ  በ2018 የአይኤኤኤፍ የአትሌቲክስ አዋርድ ላይ በሁለት  የሽልማት ዘርፎች ለውድድር የቀረበ ሲሆን በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ለመስበር እንደሚፈልግ ታውቋል፡፡ አትሌት ሰለሞን በውድድር ዘመኑ በ5ሺ ሜትር ዳይመንድ ሊግን በማሸነፉ፤ በ5000 ሜትር ከ13 ዓመታት በኋላ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገቡ እና በሀ20 ሪከርድ በመያዙ፤ በ3ሺ ሜትር በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ በመጎናፀፉ እና በ5ሺ ሜትር በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4ኛ ደረጃ በማግኘቱ በአይኤኤኤፍ ከሀ20 በታች ኮከብ ለሆኑ አትሌቶች በሚሸለመው ‹‹አዲስ ኮከብ አትሌት›› rising star award ከሚፎካከሩ አምስት አትሌቶች አንዱ ሆኗል፡፡ ከአትሌት ሰለሞን ባረጋ ጋር በእጩነት የሚፎካከሩት የኩባው ስሉስ ዘላይ ጆርዳን ዲያዝ ፤ የስዊድኑ ምርኩዝ ዘላይ አርማንድ ዱንላንቲስ፤ የኖርዌይ መካከለኛ ርቀት ሯጭ ጃኮብ ኢንግሪብስተን  እንዲሁም የኬንያው ረጅም ርቀት ሯጭ ሮኒከስ ኪፕሮቶ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በስፔን በተካሄደ  የክሮስ ኤልጎይቤር አገር አቋራጭ ውድድር አሸንፎ ሲገባ ደስታውን የገለፀበት አስደናቂ የድል ፎቶው ደግሞ በ2018 የአይኤኤኤፍ የአትሌቲክስ አዋርድ የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ዘርፍ መታጨቱም ታውቋል፡፡ ዘንድሮ በአይኤኤኤፍ ዓመታዊ  የሽልማት ስነስርዓት  ለመጀመርያ ጊዜ የዓመቱ ምርጥ የአትሌቲክስ ፎቶግራፍ በይፋ የሚሸለም ሲሆን፤  በአይኤኤኤፍ  ውድድሮች ላይ እውቅና አግኝተው የሚሰሩ ፎቶግራፈሮች ያቀረቧቸው ከ70 በላይ ምርጥ ፎቶዎች ተወዳድረውበታል፡፡  የአይኤኤኤፍ የአትሌቲክስ አዋርድ በሞናኮ በሚደረገው ከሳምንት በኋላ ሲሆን  አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ2018 የዓለም አዲስ ኮከብ አትሌት እና የዓመቱ ምርጥ ፎቶ ሽልማቶችን እንደሚያሸንፍ ተጠብቋል፡፡ ሽልማት ስነስርዓት ላይ በሚቀርብ ኤግዚብሽን አሸናፊው ፎቶ ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በእጩነት የቀረበበትን ፎቶ ያነሳው የፎቶራነርስ ባልደረባ ፍሊክስ ሳንቼዝ ይባላል፡፡ ፎቶው ሰለሞን  በ2018 የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግን በ5ሺ ሜትር ማሸነፉን አስመልክቶ አትሌት ሰለሞን ባረጋ ከአይኤኤኤኤፍ ድረገፅ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ  በውድድር ዘመኑ በልምምዱ ድግግሞሽ እና ጫና ላይ ጠንክሮ መስራቱንና ከአሰልጣኞቹ ከሚያገኘው ምክር ባሻገር በራሱ ጥረት ብዙ መልፋቱን ገልፆ ሙሉ ብቃቱን ለመመለስ መቻሉን ተናግሯል፡፡
በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናና በአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ባስመዘገባቸው ውጤቶች አለመደሰቱን ሲገልፅም አሰልጣኞቹ የሰጡት ምክር በቂ ሞራል ስለገነባለት በዳይመንድ ሊግ ላይ አተኩሮ በመስራት ስኬታማ ሊሆን መብቃቱን አብራርቷል፡፡ በ2018 ዳይመንድ ሊግ ላይ  በአሜሪካ ዩጂን በ2 ማይል ፤በቼክ ኦስትራቫ በ3ሺ ሜትር፤ በስዊድን ስቶክሆልም በ5ሺ ሜትር ካሸነፈ በኋላ በዳይመንድ ሊጉ ፍፃሜ የመጨረሻ ውድድሩን በቤልጅዬም ብራሰልስ አድርጓል፡፡
 በብራሰልስም በ5ሺ ሜትር ውድድሩ 12፡43.02 የሆነ በምንግዜም ፈጣን ሰዓት ላይ በአራተኛ ደረጃ እንዲሁም በሀ20 የዓለም ሪከርድ አስመዝግቦ የዳይመንድ ሊጉ ተሸላሚ ሊሆን በቅቷል፡፡ ከ2018 በፊት በ5ሺ ሜትር የነበረው የግሉ ፈጣን ሰዓት 12፡55 እንደነበር ለአይኤኤፍ የተናገረው አትሌት ሰለሞን ሰዓቱን ወደ 12፡43 ማውረድ ከቻለ በኋላ ቀጣይ እቅዱ የዓለም ሪከርድን ማሻሻል መሆኑን ገልጿል፡፡ በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ከ14 ዓመታት በፊት በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ 12፡37.55 በሆነ ጊዜ እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡


------      በረጅም ርቀት ሩጫ በተለይም በ5ሺ ሜትር ተወዳዳሪነት የሚታወቀው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ18 ዓ መቱ በዓለም
አትሌቲክስ ያገኘው ትኩረት የሚያስደንቅ ነው፡፡ በዓለም አትሌቲክስ በፕሮፌሽናል አትሌትነት በቆየባቸው ያለፉት 3
ዓመታት 12 ውድድሮችን አሸንፏል፡፡ የሩጫ ዘመኑ ዋና ዋና ውጤቶችና ምርጥ ሰዓቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
• በ2016 በዓለም ሀ20 አትሌቲክስ ሻምፒዮና በፖላንድ ባይድጎስዝ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ
• በ2017 በአፍሪካ ሀ20 የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በትሌምቼን አልጄርያ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ
• በ2017 በዓለም ሀ18 አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ ናይሮቢ በ3ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ
• በ2017 እኤአ ላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በእንግሊዝ ለንደን በ5ሺ ሜትር 5ኛ ደረጃ
• በ2017 በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አሸናፊ
• በ2018 በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በእንግሊዝ በርሚንግሃም በ3ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ
• በ2018 በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በናይጄርያ አሳባ በ5ኺ ሜትር 4ኛ ደረጃ
• በ2018 በአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር ሻምፒዮን ለመሆን ሲበቃ ያስመዘገበው 12፡43.02 የሆነ
ጊዜ በምንግዜም ምርጥ ሰዓቶች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠበት ነው፡፡
ምርጥ ሰዓቶቹ - በትራክ
3000 ሜ. – 7:37.54 (ኦስትራቫ 2018)
5000 ሜ. – 12:43.02 (ብራሰልስ 2018) (የዓለም U20 Record)
2 ማይልስ - 8:20.01 (ዩጂን 2018)
በቤት ውስጥ አትሌቲክስ
3000 ሜ.– 7:36.64 (ሊዬቪን 2018)

Read 2463 times