Monday, 03 December 2018 00:00

ከተስማሙ ዘጠኝ ቂጣ ለባልና ሚስት ይበቃል

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልዑል በአንድ ጫካ ውስጥ አደን ሲያድን ውሎ እየተመለሰ ሳለ አንድ ባላገር ያገኛል፡፡ ባላገሩ የልዑሉን ማንነት አያውቅም፡፡ ስለዚህም እንዲሁ በአዘቦት ሰላምታ፡-
“እንዴት ዋልክ ወዳጄ?” አለ
ልዑሉም፤
“ደህና እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ አንተስ ደህና ውለሃል?”
“ደህና፡፡ ከየት እየመጣህ ነው?”
“ከአደን”
“ቀናህ?”
“ዛሬ እንኳን እንደትላንትና አደለም”
ልዑሉ፤ ባላገሩ እንዳላወቀው ገብቶታልና፤
“ለመሆኑ ንጉሥ ማለት ምን ማለት ነው? ታውቃለህ?”
“አላውቅም”
“አየህ፤ ንጉሥ ማለት በፈረስ ሲሄድ ሰዎች ሁሉ ቆመው የሚያሳልፉት፣ እጅ የሚነሱት፣ አንዳንዴም ያለፈበትን መሬት ሳይቀር የሚስሙለት ሰው ነው፡፡ አሁን ና ፈረሴ ላይ ተፈናጠጥና ወደ ከተማ አብረን እንዝለቅ” አለው፡፡ ባላገሩ ተፈናጠጠና አብረው መጓዝ ቀጠሉ፡፡ ወደ ከተማ እየተጠጉ ሲመጡ፣ ሰው ሁሉ በያለበት ይቆም ጀመር፡፡ ግማሹ እጅ ይነሳል፡፡ ግማሹ ይንበረከካል፡፡ ዕልል የሚሉ ሴቶች ሁሉ ታዩ፡፡
ልዑሉ፤
“እሺ ወዳጄ፣ አሁን ንጉሡ ማን እንደሆነ ገባህ?”
“አዎን”
“ማን ይመስልሃል?”
“እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነን ማለት ነዋ!”
***
ሰዎች የሚያስቡት በገባቸው መጠን ነው፡፡ በቀናነት የሚያስቡ ሰዎች ልክ አላቸው፡፡ ንፅህና አላቸው፡፡ የአዕምሮ ልኬት አላቸው፡፡ ሁሌ ካፍንጫችን ስር ብቻ ማሰብ፣ እንደ መንጋ መነዳትን ያስከትላል፡፡ ስለ ሜቴክ ሲነግሩን፣ እሱን ብቻ ልናስብ ከሆነ፣ በዚያው ታቅበን እንቀራለን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የወንጀል ደሀ ሆና አታውቅም፡፡ የምላስም ደሀ አይደለችም። የሥራ እንጂ!
ጥንት በነበረው የትግል ሂደት ውስጥ…
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ከንግግር በፊት የአርምሞ ፀጥታ
ዛሬም ያገሬ ሰው ጊዜያዊ ዝምታ
 ነገ ግን ይነቃል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያሸንፋል አንጠራጠርም”
… እንል ነበር፡፡
ብለናል ግን የሀገራችን ሰው ከዝምታው ሳይነቃ ዘመን አልፏል፡፡ ጊዜው አልደረሰም ማለት ነው፡፡ አሁን መሆን ያለበት፣ አግባብ ያላቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ መጠየቅ ነው። ከጥያቄዎቹ አንዱና ዋነኛው “አንድ ምርጫ ብቻ ነው ማሰብ ያለብን?” የሚለው ነው፡፡ የ1966 አብዮት ወደ 1969 ሲያድግ በጠባቡ “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም” ብለን የጀመርነውን፤ “ደም በደም ነው የሚጠራው” ብለን ደመደምነው፡፡ ዋጋ ከፈልንበት፡፡ የ1993 የምርጫ ሂደት አንድ ዙር ልናልፈው ስንችል፤ “ዕውር ነገ አይንህ ይበራልሃል” ሲባል፣ “ዛሬን እንዴት አድሬ?” አለ የተባለው ሆነና፣ በስድስት ወር አገር እንለውጣለን ብለን ሁሉንም አፋረሰነውና ዋጋ ከፈልን። አሁንም የያዝነው ለውጥም ሆነ መጪው ምርጫ የመጨረሻው ነው ብለን አናስብ። ከምርጫው በኋላ ሌላ ምርጫ ይኖራል ብለን እናስብ፡፡ እንዘጋጅ፡፡ ይኖራል ያልነው ላይኖር፣ አይኖርም ያልነው ሊኖር ሁኔታዎች ሊያስገድዱት፤ የተፈጥሮም፣ የሶሻልም፣ ምናልባትም የሶሻል ሳይንስ ህግ ነው! ምክንያቱም ለመኖር አለመኖርን መቃወም ተፈጥሯዊ ነውና -Living is resisting death ይባላልና በፈረንጅ አፍ!  
ዞሮ ዞሮ ያለንን አዎንታዊ መንፈስ ለማጠንከር፣ በቅን ልቦና ለውጥን ማመን ያስፈልገናል። ስለ ምንም ስለ ማንም ብለን ሳይሆን፣ የሀገርና የህዝብ ነገር ስለሚቆረቁረን ነው፡፡ “ከተስማማን ዘጠኝ ቂጣ ለባልና ሚስት ይበቃል” ስንል፤ ከተስማሙ ላይ አስምረን ነው፡፡ አለዚያማ ቂጣው ለጎረቤትስ ይበቃ አልነበር? ጥናቱን ይስጠን!

Read 7778 times