Saturday, 24 November 2018 12:48

በውበት ላይ የሚያተኩረው “ዝግዛግ” ሆቴልና ስፓ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)


ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ለትምህርት አሜሪካ በሄደች ጊዜ የሚያውቋት ሰዎች፤ “አሜሪካ መጥተሽ ወደፊት ጥሩ የሚያበላሽን ነገር ትማሪያለሽ እንጂ እንዴት ስለ ጸጉር ትማሪያለሽ?” ብለዋት ነበር፤ አልተቀበለቻቸውም እንጂ፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ትወደው ለነበረው፣ ለዛሬው ማንነቷና ለኑሮዋ መሰረት ለሆነው ኮስሞቶሎጂ (ሥነ-ውበት) ትኩረት ሰጥታ ተምራ፣ በጥሩ ውጤት መመረቋን ትናገራለች - የዛሬ ሳምንት የተመረቀው “ዝግዛግ” ሆቴልና ስፓ መስራችና ባለቤት ወ/ሮ ኮንስታንቲና አማኑኤል፡፡
“ዝግዛግ” የሚለው ቃል ወ/ሮ ኮንስታንቲና የተማረችበት ት/ቤት መጠሪያ ሲሆን ት/ቤቱ የሚሰጠውን ትምህርት በጣም ትወደው ስለነበር፣ ድርጅቷንም በዚሁ ስም መሰየሟን  ገልጻለች። ኮስሞቶሎጂ፤ አጠቃላይ ስለ ሰውነት ክፍሎች (የቆዳ፣ ፀጉር፣ ፊት፣ ጥፍር--) ውበትና እንክብካቤ የሚያስተምር የትምህርት ዘርፍ እንደሆነ የጠቆመችው ወ/ሮ ኮንስታንቲና፤ እስከ ዛሬ ድረስ ትምህርቱን በተከታተለችበት አሜሪካም ሆነ በአገሯ ውስጥ ከዚህ ዘርፍ ውጭ ሰርታ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡  
ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በ1969 ዓ.ም ተወልዳ፣በመድኃኒዓለም ት/ቤትና በአሜሪካን ሚሽን መማሯን ያወሳችው ወ/ሮ ኮንስታንቲና፤ ከ16 ዓመት በፊት ወደ አገሯ ተመልሳ፣ግሎባል ሆቴል አካባቢ “ዝግዛግ” ስፓና የፀጉር ውበት ቤት ከፍታ ሥራ መጀመሯን ትገልጻለች፡፡
ቦሌ መስቀል ፍላወር አካባቢ፣ ከግርግር ነፃና ምቹ በሆነ ስፍራ፣ በ300 ካ.ሜ ቦታ ላይ፣ 40 ሚሊዮን ያህል ብር ወጭ ተደርጎ የተሰራው ባለ 6 ፎቁ “ዝግዛግ” ሆቴልና ስፓ፤ 15 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለ72 ቋሚ ሰራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ  ታውቋል፡፡
ግንባታው 6 ዓመት የፈጀው “ዝግዛግ” ሆቴልና ስፓ፤ በመዲናዋ ብቸኛው በውበትና የጤና እንክብካቤ ላይ የሚያተኩር፣ ለእንግዶች ምቹ የመዝናኛ ስፍራና በርካታ ጥቅል አገልግሎቶች (ፓኬጆች) ያለው፣ የሆቴሉ ዲዛይን ለዚሁ አገልግሎት ታስቦና ታልሞ  የተሰራ፣ ክፍሎቹ የተቀቡት ቀለም የሚያምሩ አረንጓዴና ቢጫ ሲሆኑ አረንጓዴው የአኗኗር ዘይቤን (ላይፍ ስታይል)፣ ቢጫው ደግሞ ሰዎች ግልጽ (ኦፕን) እንዲሆኑ የሚያደርግ መልካም ቀለም መሆኑን የሆቴሉ አማካሪ ወ/ሪት ነዒማ አህመድ አብራርታለች። ሆቴሉ፤ አንድ ወለል ስፓ፣ አንድ ወለል፣ ፀጉር ቤት፣ ሦስት ወለሎች መኝታ ክፍሎች፣ አንድ ፔንት ሐውስ (አፓርትመንት) አሉት፡፡
ወደ “ዝግዛግ” ሆቴልና ስፓ አገልግሎት ፈልጎ ለሚመጣ ሰው ሁሉ የእግር እንክብካቤ (ትሪትመንት) ይሰጣል፡፡ ሰውነት ውስጥ ያሉትን መርዛም ኬሚካሎች የተለያዩ የተፈጥሮ ቅባቶች በመጠቀም (የደም ግፊት፣ የስኳርና የወገብ ህመም…) ላለባቸው ሰዎች ለ45 ደቂቃ ያክማል፡፡ “ፊታቸው ላይ ማዲያት፣ ጥቋቁር ነገሮች፣ ሰንበር፣ … ላለባቸው ሴቶች የፊት ውበት ከመስጠታችንም በላይ፣ እቤታቸው ሄደው በቀላሉ ሊያገኙት በሚችሉት ነገር ምን ማድረግ፣ ምን ዓይነት ምርቶች መጠቀም እንዳለባቸው እንመክራቸዋለን። ሙሉ አካል ሳይሆን አንድ የተወሰነ ቦታ (ወገብ፣ ትከሻ፣…) ላይ ሙቀት በመስጠት እናክማለን” በማለት ወ/ሪት ነዒማ አስረድታለች፡፡
ሆቴሉ ጭስ አልባ የወለባ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ የአገልግሎቱ ፈላጊ በልዩ ትዕዛዝና ዲዛይን በተሰራው ሳጥን መሰል ዘመናዊ መቀመጫ ውስጥ ሆኖ፣ አንገቱ ወደ ውጭ በማውጣት፣ ወለባውን ይጠቀማል፡፡
ሆቴሉ፣ የተለያዩ እንግዶች የሚያርፉባቸው ክፍሎችም አሉት፡- ስታንዳርድ፣ ሲንግል፣ ቲዊን፣ ስዊትና ፋሚሊ ክፍሎች አስፈላጊ የመገልገያ ዕቃዎች (ቲቪ፣ ካዝና፣ ፍሪጅ፣ ስልክ፣ ጠረጴዛና ወንበር፣ መታጠቢያና መጸዳጃ…) የተሟሉላቸው ናቸው፡፡ አምስት ሆነው በቡድንና በቤተሰብ ለሚመጡ አገልግሎት ፈላጊዎች አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ሁለት ፎቅ አፓርትመንቶች አሉት፣ አፓርትመንቶቹ ሰፊ መኖሪያ ቤትና ሁለት መኝታ ክፍሎች አላቸው፡፡ እንግዳው አብስሎ መመገብ ቢፈልግ፣ ሙሉ የኪችን ዕቃዎች  ... የተሟላላቸው ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የ24 ሰዓት ስፓ፣ የሴቶችና የወንዶች የውበት ሳሎን፣ ባርና ሬስቶራንት፣ የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ፣ ፒዜሪያና ካፌ እንዲሁም በሆቴሉ ለሚያርፉ እንግዶች የላውንደሪና የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ሆቴሉ፤ በርካታ በጥቅል የሚሰጡ አገልግሎቶችም አሉት፡፡ ነፃ የሙሉ ቀን ጥቅል አገልግሎት፡- ስቲም፣ ሳውና፣ ሞሮኮ ባዝ፣ የ60 ደቂቃ የስዊድን ማሳጅ፣ የእግር ማሳጅ፣ የፀጉር ሳሎን (የሴትና የወንድ) የፊት ውበት እንዲሁም ምሳና መዝናኛ መጠጥ ያካትታል፡፡ ለሙሽሮች የሚሰጡ አገልግሎቶች ደግሞ ስቲም፣ ሳውና ሞሮኮ ባዝ፣ ማሳጅና የፊት ውበት የሚሰጥ ሲሆን ሻምፓኝ ወይም ወይን ይቀርብላቸዋል፡፡
ለተለያዩ ዝግጅቶች ለምሳሌ ለልደት፣ ለእናቶች ቀን፣ ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚሰጡ ጥቅል አገልግሎቶች፡- ለጥንዶች ስቲም፣ ሳውና፣ ማሳጅና፣ ሞሮኮ ባዝ ይሰጣል፡፡ ለሁለቱ እራትና ወይንም ይቀርብላቸዋል፡፡ አምስት ሆነው ለሚሄዱ፤ በቡድን ስፓ ክፍል ውስጥ ስቲም፣ ሳውና፣ ማሳጅና ሞሮኮ ባዝ፣ የሴቶችና የወንድ የፀጉር ውበት አገልግሎት እንዲሁም የለስላሳ መጠጥ ግብዣ ይደረግላቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፀጉርና የስፓ ጥቅል አገልግሎት በተናጠል እንዲሁም ሁለቱ አገልግሎቶች በጥምረት ይሰጣሉ፡፡ የውበት ሳሎን ጥቅል አገልግሎት፡- ፀጉር፣ ፊትና እግር ማስዋብ፤ የስፓ ጥቅል አገልግሎት፡- 60 ደቂቃ የስዊድን ማሳጅ፣ ስቲምና ሳውና፣ ልዩ ሳውና በከበረ ድንጋይ … ያካትታል፡፡Read 2194 times