Sunday, 25 November 2018 00:00

ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ “አሁንም እሳትና አበባ ከፊታችንአለ”

በሐገራችን ጎላ ብለው ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ ሰፊ የጸጥታ መደፈርስ ችግር ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች የምንመለከተው የጸጥታ መደፍረስ በጣም ያሳስበናል፡፡ ይህ ችግር አጠቃላይ ስርዓቱን ለቀውስ የሚዳርግ ችግር እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በቅርቡ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው ነገር አስጊ መሆኑን መንግስት ገልጧል፡፡ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር እንደ ገለጹት፤ ዩኒቨርስቲዎችን ማዕከል አድርጎ ሁከት የመቀስቀስ የተቀናጀ እንቅስቃሴ መኖሩን አመልክተዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የተወሰዱት የለውጥ እርምጃዎች ኢትዮጵያ ምን ያህል መለወጥ እንደፈለገች ሲያመለክቱ፤ ሁከቱ ደግሞ ሐገሪቱ ገና ብዙ መለወጥ እንደሚቀራት ያሳየናል። አንዱ የስርዓቱን ጥንካሬ ሲገልጽ፤ ሌላው ብዙ መሠረታዊ ድክመቶች መኖራቸውን ይናገራል። አንዱ የስርዓቱ ተስፋ፤ ሌላው ለስርዓቱ ዳፋ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሁንም እሣት እና አበባ ከፊታችን አለ። አሳሳቢው እሣቱ ነው፡፡ ይህ እሣት ህገ መንግስቱን አመድ ሊያደርገው ዙሪያ - ዙሪያውን ይንቀለቀላል፡፡ ይህ በእጅጉ ያሳስባል፡፡
ህገ መንግስቱን የሁከት እሣት ከበላው በባዶ እጅ እንቀራለን፡፡ ግራ እንጋባለን፡፡ በመታፈር የኖረችውን ኢትዮጵያ እናዋርዳታለን፡፡ የጠላቶቻችን መጫወቻ እንሆናለን፡፡ ሰላም እናጣለን፡፡ ሐገር እናፈርሳለን፡፡ እርስ በእርስ እንተላለቃለን፡፡ ዛሬ የዓለም ህዝብ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያገኙትን መልካም ዕድል ያስቀጥሉታል ወይስ ተመልሰው ከመጥፎ አዙሪታቸው ጥለው ያበላሹታል?›› ብሎ በአንክሮ ይመለከተናል፡፡ ከቀውስ ወጥተው የልማት ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ ወይስ ተሰናክለው ይቀራሉ? እያለ በትዝብት ያስተውለናል፡፡ ዓለም ‹‹ኢትዮጵያውያን የተስፋ አበባቸውን ረግጠው፤ ህገ መንግስታቸውን በአመጽ እሣት አቃጥለው፤ በሐገራቸው ሁከት አንግሰው ወደ ተለመደ ትርምሳቸው ይገቡ ይሆን?›› እያለ ሲያየን ይውላል፡፡
ኢትዮጵያውያን እርምጃቸውን በእጃቸው በያዙት ህገ መንግስት እየለኩ ካልተራመዱ የምንፈራው ይደርሳል፡፡ ሆኖም በቃል ኪዳን ሰነዳቸው (በህገ መንግስታቸው) ያሰፈሩትን ነገር ተከትለው ለመራመድ ከቻሉ፣ እያደር መንገዳቸው ይቃናል፡፡ አሁን የያዝነውን ህገ መንግስት፣ የአንድ ቡድን ህገ መንግስት አድርገን በመመልከት መሳሳት የለብንም፡፡ ህገ መንግስቱ የእኛ ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት፤ አሟልተው የማይቀበሉትን ወገኖች እንኳን በልበ ሰፊነት የሚቀበል ህገ መንግስት ነው። ይህ ህገ መንግስት የደጋፊዎቹ ብቻ ሳይሆን፤ የተቃዋሚዎቹም ነው፡፡ ህገ መንግስቱ መለወጥ አለበት ብለው የሚያስቡ ሰዎች ህገ መንግስት ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውን መንገዳቸው ሁሉ በህገ መንግስቱ በኩል መሆን አለበት፡፡ ይህ  ህገ መንግስት የተቃዋሚዎቹም የደጋፊዎቹም ነው፡፡ ስለሆነም፤ አሁን ጸንቶ ያለውን ስርዓት የሚቃወሙ ወይም እንዲለወጥ የሚፈልጉ ሰዎች ጭምር ይህን ህገ መንግስት መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ህገ መንግስት የሰው ህይወት ሳይጠፋ፤ ንብረትና ሐብት ለውድመት ሳይዳረግ በሰላማዊ ጎዳና ዓላማን ማሳካት የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡
ህገ መንግስቱ የሰላማችን ካስማ ነው፡፡ ከፋም - ለማም ልማት ማምጣት ያስቻለ ሰነድ ነው፡፡ የሰላማችንና ሁሉንም አርኪ ከሆነ ደረጃ ያልደረሰው ልማታችን ምንጭ እርሱ ነው፡፡ አንዳንዶች፤ የልማቱ ምንጭ ‹‹ትክክለኛ ፖሊሲ፣ ምቹ ዓለማዊ ሁኔታ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ያልተማከለ አስተዳደር›› ወዘተ ሊሉ ይችላሉ። ጉዳዩን ከዚህ አኳያ ለማየት የጀመረ ሰው፤ ከተጠቀሱት ነገሮች በተጨማሪ ብዙ ዝርዝር ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ነገሩ ያለ ሐተታ በአንድ ቃል ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ይህ ቃል ዘወትር ከዓለም ህዝቦች አንደበት የማይጠፋ፤ የደፈረሰ ህሊናን የሚያጠራ፤ የሁሉም በጎ ነገሮች ምንጭ የሆነ ክቡር ቃል ነው፡፡ ለፍጥረታት ሁሉ አለኝታና መከታ የሆነ የሦስት ሆሄያት ስሪት ነው። ይህ ንዑድ -ክቡር ቃል ‹‹ሰላም›› ነው፡፡ ሁሉንም አርኪ ከመሆን ደረጃ ያልደረሰው ልማታችን ምስጢር ‹‹ሰላም›› ነው፡፡ በእኔ እምነት የሰላሙ ምንጭ ደግሞ ህገ መንግስታችን ነው፡፡
ትናንት እንደ ጠላት የሸሸን፤ ዛሬ ደግሞ በጸጋው የሚባርከን፣ ነገንም በተስፋ አሻግሮ እያሳየ በፍቅር የሚያሳድረን ሰላም ነው፡፡ በእጅ ያለ ወርቅን ከመዳብ የመቁጠር መጥፎ ሰብኣዊ ዝንጋኤ፤ ሁልጊዜ የሰላምና የጤንነትን ዋጋ አሳንሶ ያሳያል፡፡ አረቦች፤ ‹‹ጤንነት ስውር ዘውድ ናት›› ይላሉ፡፡ የጦርነትን ገፈት ለምዕተ ዓመታት እስኪያንገሸግሻቸው የተጋቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ፤ ‹‹ሰላም ስውር ዘውድ ናት›› ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹ሰላም ስውር ዙፋን ናት፡፡›› የሰው ልጆችን ሁሉ የክብር በትረ ሙሴ አስጨብጣ የምታነግስ ሰላም ናት፡፡ ይሁንና፤ ነገሩ ‹‹ሰው ካልሄደ ወይም ካልሞተ አይመሰገንም›› እንዲሉ ሆኖ፤ አንዳንዴ የሰላም ዋጋ የሚታወቀን፤ ከእኛ ርቃ በሄደች ወይም በሞተች ጊዜ ነው፡፡ ‹‹ሰላም ካልሄደች ወይም ካልሞተች አትመሰገንም፡፡›› ዋጋዋ አይታወቅም፡፡
አበው፤ ‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› ይላሉ፡፡ እኔም ‹‹ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› እያልኩ ነው፡፡ እውነተኛ የሰው ልጆች ገንዘቦች፡- ሰላም እና ጤንነት ናቸው፡፡ በዚሁ አገባብ ‹‹ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› የመባሉ ምስጢር ‹‹ሰላም ካለ በሰማይ መንገድ አለ›› በሚል አንድምታ መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡ አሁን በእጃችን የያዝነው ሰላም ዋጋው ዝቅ ብሎ ታይቶናል፡፡ አሁን የሰላም ዋጋ ብቻ ሳይሆን የሰላሙ ምንጭ ምን እንደሆነ ጠፍቶብናል፡፡ የሰላማችን ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡ የልማታችን ምንጩ ሰላም ነው። ስለዚህ የልማታችን ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡ የሰላማችን ምንጭ ህገ መንግስቱ ነው፡፡  
ስለዚህ ህገ መንግስቱ ከመካከላችን ሲጠፋ፤ እኛንም ይዞ ይጠፋል፡፡ አሁን ይህ እውነት ተሰውሮብናል፡፡ አሁን የቆምነው በህገ መንግስቱ መሠረት ነው፡፡ ብንጣላም ብንዋደድም እስካሁን አንድ አድርጎ በሰላም ያኖረን ህገ መንግስቱ ነው። በፖለቲካ ስሌት ከታሰበ፣ አሁን ያለን የጋራ ነገር ህገ መንግስት ብቻ ነው፡፡ በዚህች ሐገር ምንም ዓይነት ጥያቄ ወይም ቅሬታ አለኝ የሚል ዜጋ፤ ጥያቄው ሊመለስና ቅሬታው ሊቀረፍ የሚችለው የጸና ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ተጨባጭ የሐገራችን ሁኔታ የጸና ስርዓት ሊገኝ የሚችለው በህገ መንግስቱ ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም ይህን ነገር መነሻ አድርገን መውሰድ አለብን፡፡
ይህ ህገ መንግስት፤ ቀደም ሲል ሐገሪቱን የጦርነት አውድማ ሊያደርጓት የሚችሉ የታጠቁ ኃይሎችን ወደ ሰላም ጠረጴዛ በመጥራት ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ የብሔር ጥያቄ ያነሱ ኃይሎችን ፍላጎት በማክበርና የመረጋጋትን መንፈስ በመፍጠር፤ የመገንጥል ጥያቄ ላነሱ ወገኖች የሚያረካ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የመጠቀም (የመዳኘት እና የመማር) እንዲሁም ባህልና ታሪካቸውን የማሳደግ መብት አጎናጽፎአቸዋል፡፡ በዚህ ዓይነት በወቅቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት አርግቧል።
ኢህአዴግ የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች መብት እንዲከበር ሲያደርግና ለዚህ የተመቸ የፖለቲካ ስርዓት እንዲፈጠር ሲያደርግ፤ በቀላል ቁጥር የማይገመቱ ኢትዮጵያውያን ጥረቱን ሐገር የማፈራረስ ፕሮጀክት አድርገው ይመለከቱት ነበር። አሁንም ተመሳሳይ ስሜት ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ስሜት የመጥፋት አዝማሚያ ሲከተል ቆይቶ፤ አሁን (እንደ ድሮው የሴራ ትንታኔ ያለው አቀራረብ የተከተለ ባይሆንም) የተለየ ቅርጽና ይዘት ይዞ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚታዩ መጥፎ አዝማሚያዎች በተጨማሪ፤ በተለይ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ በሰፊው የሚታዩ አንዳንድ ባህርያትንና የተለያዩ የማህበራዊ ኑሮ አጋጣሚዎችን በመጥቀስ፣ ስርዓቱ አደጋን ያረገዘ ስርዓት መሆኑን የሚናገሩ ሰዎች ዳግም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡   
በኢትዮጵያ ግጭቶች የብሔር መልክ የመያዝ ሰፊ ዕድል ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ አደረጃጀት የሚያሰጋቸው ሰዎች እውነት አላቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያቀርቡትን አስተያየትም፤ ከጠቅላይ ግዛት የፖለቲካ ዝንባሌ ጋር ብቻ አያይዞ ማየት ተገቢ አይሆንም፡፡ ስለዚህ በብሔር ፖለቲካ ላይ ጥርጥሬ ያላቸውን ሰዎች አቋም ከጠቅላይ ግዛት የፖለቲካ ዝንባሌ ጋር ብቻ ማያያዝ አይቻልም፡፡ በዚሁ ሚዛን፤ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን መብት ለመቀበል መወሰንን ሐገር ከማፍረስ ጋር ማያያዝ ትክክል አይሆንም፡፡ የብሔር ጥያቄ መፍትሔ የሚሻ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ከጠረጴዛችን ተቀምጦ ነበረ፡፡    
ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከመግባቱ ከአንድ ወር በፊት፤ ምናልባትም ሚያዚያ 14 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም የተናገሩትን አንድ ነገር ማስታወስ ይቻላል፡፡ የሐገር አንድነትን ለማስከበር መቆማቸውን የሚያምኑትና ብዙዎችም በዚሁ ዓይን የሚያዩዋቸው ኮሎኔል መንግስቱ ከሸንጎው ፊት ተቀምጠው እንደሚከተለው ተናግረው ነበር፡፡
‹‹ጓዶች ተፈተንን፣ ተቸገርን፤….ልጄ ውትድርና ሄደብኝ፣ መሬቴ ተቀማብኝ ያለ አማራ ጫካ ገብቷል። ትግሬ ድሮም ሽፍታ ነበር፡፡ ሸፍቷል፡፡ ኦሮሞ ነጸ ካልወጣሁ እያለ እየወጋን ነው፡፡ አፋር ብረት አንስቶ ለነጻነቴ እታገላለሁ ይላል፡፡ ዛሬ እኮ ይህን መንግስት የሚወጉ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ ድርጅቶች ወደ አርባ ተጠግተዋል፡፡ ማንን ነው ከማን ነጻ የሚያወጡት? እዚህ ውስጥ ኦሮሞ የለም፤ አማራ የለም፤ ትግሬ የለም? ይህን ምን እንደምናደርግ ነው ግራ የገባን?›› ብለው ነበር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ በወጣ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጠው፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ የነበረውን የኃይል አሰላለፍ ሲገልፁ፤ ‹‹በአንድ ወገን፤ የሐገራችሁን ህዝብ አንድነት፣ ዕድገትና ብልጽግና በደማችሁ የምትዋጁ፤ አጥንታችሁን የምትከሰክሱ፤ መተኪያ የሌላት ህይወታችሁን የምትሰዉ፤ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆችና ጀግኖች፡፡ በሌላ ወገን፤ ለወገናችሁ ሞት፣ ስቃይና ስደት በአንደበታችሁ የምትመርዙ፣ በብዕራችሁ የምትደልዙ፣ በጠብመንጃ አፈሙዝ የምትገዘግዙ፤ እንዲሁም ራሳችሁን ብቻ ሳይሆን የወለዷችሁን እናትና አባቶቻችሁን ጭምር የካዳችሁ፤ የዘመኑ የኢትዮጵያ እንቆቅልሾች……›› ብለው ነበር፡፡
ኮሎኔሉ፤ የብሔር፣ የብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት መከበር አለበት የሚል አቋም የያዙትን ‹‹የኢትዮጵያ እንቆቅልሾች›› ወይም ‹‹ከሃዲዎች››፤ በተቃራኒው በኃይል የሐገሪቱን አንድነት እናፀናለን የሚል አቋም የሚያራምዱትን ‹‹እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች-ጀግኖች›› አድርገው ይፈርጃሉ። ይህም መንግስታቸው ጨርሶ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ቁመና እንዳልነበረው ያመለክታል፡፡
የብሔር፣ የብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት መከበር አለበት ብሎ የሚጠይቅ ወገን ሲመጣ፤ ‹‹ምን አልክ አንተ ጎሰኛ?! አሁን ከዚህ ግድም አትሄድም!›› እያለ ሐገሪቱን በሁሉም አቅጣጫ የጦር አውድማ ያደረገው ያ መንግስት፤ የኃይል አንድነት መፈክሩን እንደያዘ ከመንበሩ ተፈነገለ። የተከተለው ጎዳና የሐገሪቱን ሰላም አደፍርሶ፣ አንድነቷን ለባሰ አደጋ እንዲጋለጥ አደረገ እንጂ የፈጠረው ለውጥ አልነበረም፡፡
ደርግ በጦርነት ከተሸነፈ በኋላ ሐገሪቱን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ የብሔር፣ የብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እውቅና እንዲያገኝ ማድረጉ፤ ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ነጻ መንግስት ከመመስረት ውጪ ሌላ አማራጭ መኖሩን ለማየት ፈቃደኛ ያልሆኑ ወገኖች ትንሽ እንዲረጋጉና የህዝቦችን ዘላቂ ጥቅም ከማረጋግጥ አንጻር መተኪያ የሌለውን፤ (በኢህአዴግ አገላለጽ) ‹‹የዴሞክራሲያዊ አንድነት›› አማራጭን ለመሞከር ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ አስችሏል ብዬ አስባለሁ፡፡
በወቅቱ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ ገለል ለማድረግ የሚያስችል ሌላ አማራጭ ያለ አልመሰለኝም፡፡ ለሐገር አንድነት ቆምኩ የሚለው መንግስት፤ ‹‹ለዘማች አሞራ›› ጥሎት የሄደውን የሐገር አንድነት ጉዳይ፤ ከእሳት አውጥቶ በክብር ለማኖር በኢህአዴግ ከቀረበው አማራጭ የተሻለ ሌላ መንገድ ሊታየኝ አልቻለም። ይህን ሳስብ የደርግ መንግስት ለአንድነት የቆመ መስሎ መታየቱ አስገራሚ ይሆንብኛል፡፡ የደርግ መንግስት በዚሁ መልክ የመታየት ሰፊ ዕድል ማግኘቱ ይደንቀኛል፡፡
ይሁንና ደርግ ዋና የፖለቲካ ፕሮግራሙ ትኩረት አድርጎ ባይዘውም፤ እከተለዋለሁ ይል በነበረው ሶሻሊስታዊ መርህ መነሻ፤ ወይም በኢትዮጵያ ተማሪዎች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ግፊት (አለያም በሁለቱም ጣምራ ስበት)፤ ለብሔር - ብሔረሰቦች ጉዳይ  ‹‹ከሥራ ሰዓት ውጪ›› የሆነ ትኩረት መስጠቱ ግልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ተቋም›› የተባለ መንግስታዊ መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ደርግ የቡድንም ሆነ የግለሰብ መብቶችን ለማክበር የሚችል ወይም የማክበር ፈቃደኝነት ያለው መንግስት አልነበረም። ስለዚህ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለማስከበር ያደረገው ጥረት አልነበረም፡፡
በሌላ በኩል፤ ‹‹ኢትየጵያ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እስር ቤት ሆና ቆይታለች›› ብሎ የሚያምነው ኢህአዴግ የሚያቀርበው የታሪክ ትንታኔ ትክክል ሆኖ ታይቶኝ ባያውቅም፤ ‹‹ወደድክም ጠላህም በኢትዮጵያ አንድነት ሥር ትኖራለህ›› የሚል አቋም የተሳሳተ መሆኑን ሲናገር ትክክል መሆኑን መቀበሉ ከብዶኝ አያውቅም። ይህን አቋሙን ሐገር ከማፍረስ ዓላማ ጋር የሚያያይዙት ወገኖችም የተሳሳቱ ይመስለኛል። የኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞ ትልቅ ጥያቄ አድርጎ ከፊታችን የደቀነውን ይህን ጥያቄ ለመመለስ ደፋር ውሳኔ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠል የሚያስችል ደፋር አማራጭ መውሰዱን አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ታሪክ ከፊታችን የደቀነውን ከባድና ወሳኝ ጥያቄ ሌላ ችግር በሚጎትት መንገድ መልሷል፡፡ አሁን ሌላ ጥያቄ ከፊታችን ተደቅኗል፡፡ ይህንን ጥያቄም መመለስ ይኖርብናል፡፡  
ታዲያ የአንዳንድ ሰዎችን የነገር አያያዝ ስመለከት፤ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በኢህአዴግ የተፈጠሩ መስሎ እየተሰማቸው የሚናገሩ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ እንደዚያ ዓይነት ስሜት መያዛቸው ሊያስገርም አይገባም፡፡ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፖለቲካ ሐቲቱ (Political Discourse) ‹‹የዘወትር ጸሎት›› ሆኖ ብቅ ያለው ኢህአዴግ ከመጣ ወዲህ በመሆኑ፤ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በኢህአዴግ የተፈጠሩ መስሎ ቢታየን አስገራሚ አይሆንም፡፡ በዚህም አያያዙ ብሔራዊ ህልም አሳጥቶናል፡፡ የቡድን መብቶች የጭቆና መከላከያ ጋሻዎች መሆናቸው ቀርቶ፤ ልዩነት መፍጠሪያ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ተደርገዋል፡፡ ልጆቻችን አንድ ብሔራዊ መዝሙር እንዳይዘምሩ አድርጓቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የምንለው የሚዘመረው፤ በአዲስ አበባ በሚገኙ የሬዲዮ ጣቢያዎች፤ በአዲስ አበባ በሚገኙ (ምናልባትም በድሬዳዋ) ት/ቤቶች፤ እንዲሁም ጀግኖች አትሌቶቻችን በሚያሸንፉባቸው የስፖርት አደባባዮች ብቻ ነው፡፡ አሁን ረጋ ብለን፤ የተጣመመውን ለማቃናት፤ የተሰበረውን ለመጠገን እንስራ፡፡ ለዚህ ሥራ ሰላም ያስፈልገናል፡፡ ሰላም የሚገኘውም፤ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለህግ በመገዛት ነው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱን እናክብር!!  










Read 6660 times