Saturday, 24 November 2018 12:19

“ለሰጠውም አላሳነሰው ላልሰጠውም አላቀመሰው!”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

በድሮ ጊዜ አንድ አንቱ የተባሉ አገረ ገዢ፣ በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወሩ፣ ህዝቡን እየሰበሰቡ፣ ያነጋግሩ ነበር ይባላል፡፡ አብረዋቸው አዋጅ ገላጮች ነበሩ፡፡ አዋጅ ገላጮቹ በታወጁ አዋጆች ላይ ጥያቄ ቢነሳ የሚያብራሩ የሚገልጡ ናቸው፡፡
 ህዝብ ከተሰባሰበ በኋላ፣ ባለሟሉ ይነሳና፤
“የአገራችን ህዝብ ሆይ! አገረ ገዢው እዚህ ድረስ የመጡት የእናንተን ማናቸውም ብሶት ሊያዳምጡ ነውና ጥያቄያችሁን አቅርቡ” ይላል፡፡
አንዱ ባላገር ይነሳል፡-
“ጌታዬ የግጦሽ መሬት አንሶናል” ይላል
አገረ ገዢው ወደ ፀሐፊው ዞረው፤
“ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል፤
“ማዳበሪያ ይሰጣችኋል ተብለን እስከ ዛሬ አልመጣልንም!”
አገረ ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል - “የዘር  እህል ይታደላል ተብለን ዛሬም አልተሰጠንም”
አገረ - ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር በንዴት፤
“ጌታዬ! ባለፈውም እንዲሁ እናስብበታለን ሲሉ ነበር፡፡ መቼ ነው በተግባር የሚፈፀምልን? ሁሌ እናስብበታለን ነው እንዴ?”
አገረ - ገዢው - “ይሄም ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን!”
ይሄ በጣም ያናደደው አንድ የጎበዝ - አለቃ፣ አገሬውን በመወከል ይናገራል፡፡
 “ጌታዬ ሆይ! በእኛ ላይ የደረሰውን በደል የሚያህል የትም አገር አይገኝም! ፍትህ ሲጠፋ አቤት የምንልበት ቦታ የለም! ጤና ሲጠፋ የምንታከምበት ቦታ የለም! ትምርት ሲጠፋ የምንማርበት ቦታ የለም፡፡ መንገዱ ሲጠፋ አሳብረን የምንሄድበት አቋራጭ እንኳን የለም፡፡ እህል ሲጠፋ አንጀታችንን የምንጠግንበት፣ ውሃ ጥም ስንቃጠል ጥማችንን የምንቆርጥበት ምንም መፍትሄ የለንም! አሁን እናንተ፤ እያስተዳደርን አገር እየመራን ነው ትላላችሁ? እኛ ህዝቡን ማስነሳትኮ አላጣንበትም! እናንተም ደግ ደጉን አርጋችሁልን፣ እኛም ደግ ደጉን አስበንላችሁ ብንኖር አይሻልም?” አለ፡፡
አገሬው አጨበጨበ!
አገረ ገዥውም፤
 “የአገሬ ህዝብ ሆይ!
ይሄ የጎበዝ አለቃ ጥሩ ይናገራል፤ ግን ዕድሜ የለውም!” አሉ
አገሬው አሁንም አጨበጨበ!
ያ ጎበዝ - አለቃም ከዚያን ቀን በኋላ አልታየም፡፡
***  
ሁልጊዜ “እናስብበታለን” አያዋጣም፡፡ አፈፃፀም ያስፈልጋል፡፡ በዘመንኛው ቋንቋ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ (Bureaucratic red - tape) መበጠስ አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ጥንት ንጉሡ የወሰኑትን አስፈፃሚዎቹ ባለሟሎች፤ “እሺ” “እሺ” እያሉ በተግባር ግን አንዷንም ነገር አያውሉም ነበር ይባላል፡፡ ይሄ ክፉኛ ያቆሰለው በደለኛ ንጉሡ ዘንድ ይቀርብና፤
“ጃንሆይ! ሁሉም ነገር ይቅርብኝና አንድ ሃያ አጋሠሥ ይሰጠኝ” ሲል አቤት ይላል፡፡
 ጃንሆይም “ለምንህ ነው?” ቢሉት፣
“የሸዋን መኳንንት ‹እሺታ› የምጭንበት”፣ አለ ይባላል፡፡ ውሳኔዎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች፣ ወዘተ በሥራ ላይ ካልዋሉ፣ ካለንበት ንቅንቅ አንልም፡፡ ጌቶች ቢያስነጥሱ መሀረብ የሚያቀብሉ ዓይነት ሰዎች መቼም፣ የትም ድረስ አያራምዱንም! ጉዳያችሁን ተናገሩ፡፡ ብሶታችሁን አውጡ፡፡ ጥያቄያችሁን አቅርቡ፤ ብሎ ‹እድሜህ አጭር ነው› ከሚል ይሰውረን፡፡ ለአጥቂውም ለተጠቂውም ከሚያጨበጭብ ተሰብሳቢም ይሰውረን፡፡
ያልተመለሰ ጥያቄ ያልተከፈለ ዕዳ ነው፡፡ ነገ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ዛሬ አድበስብሰን የምናልፈው ጥያቄ፤ የነግ የቂም ቋጠሮ ይሆንብናል፡፡ ያ ደግሞ ዕድገትን ተብትቦ ያሰናክለዋል፡፡ የበላይ ወደ ታች የሚመራውን፣ የበታች እንደ “ኮምፒዩተር ጌም” ሲጫወትበት የሚውል ከሆነ፤ እንኳን ትራንስፎርሜሽን መደበኛውም ዕድገት አይገኝም፡፡ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ” መሆን የሚመጣው፣ ለትልቁ ስዕል አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ትናንሽ ስዕሎች በቅጡ ካልተሳሉና ሥጋና ደም ሳይለብሱ የቀሩ እንደሆነ ነው፡፡ የበታች አካላት ማያያዣ ክር ናቸው፡፡ እነሱ ከተበጣጠሱ የበላይ አካላት የሉም፡፡ ይሄ በቢሮክራሲያዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ ያው ነው፡፡ ትናንሽ ስህተቶች ለግዙፍ ስህተት አሳልፈው ይሰጡናል፡፡ ያኔ ውድቀት ቅርብ ይሆናል፡፡
 ሱን ሱ የተባለ የቻይና ጦር መሪ “በጦርነት ድል ማድረግ የሚደጋገም ነገር አይደለም፡፡ ሁሉ ቅርፁን ይለውጣል፣ ውሃ ሁሌም አንድ አይነት ቅርፅ የለውም - እንደ መያዣው ዕቃ ይለዋወጣል፡፡ እንደ ባላንጣህ አካሄድ ቅርፅህን እየለዋወጥክ ድል መቀዳጀት ረቂቅ - ሊቅ (genius) ይባላል” ይለናል፡፡ ስለ ህይወት፣ ስለ ማናቸውም ትግል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ለውጥ ስናስብ ሁሌም እንደ ሁኔታው  አካሄድን ቀይሮ በብስለት መጓዝን አንርሳ፡፡  ረቂቅ - ሊቅ የመሆን ጥበብ ይሄ ነው፡፡ በሌሎች ድክመት ላይ ከመንተራስ በራስ መተማመን ብልህነት ነው! አንዴ የሆነው ነገር ላይ ከማላዘን ይልቅ ሁኔታዎችን በሌላ አቅጣጫ ለመለወጥ (Reversal) መሞከር አዲስ ቅያስ ለማየት ይጠቅመናል፡፡ ሳይታለም የተፈታን ጉዳይ (de facto) ደግመን ደጋግመን መወትወት ያው ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ የተሰረቀው ተሰርቋል፡፡ የተሄደው ድረስ ተሄዷል፡፡ የባላንጣችን አቅም ታውቋል፡፡ ዘዴና መላው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ስለዚህ የታወቀን መንገድ ትቶ፣ ያልተሄደበትን መንገድ ወይም ብዙ ያልተሄደበትን መንገድ (The Road Less Travelled) ማሰብና ማስላት ይሻላል፡፡ የሆነውማ ሆኗል - “ለሰጠውም አላሳነሰው፣ ላልሰጠውም አላቀመሰው!” 

Read 8825 times