Saturday, 19 May 2012 11:18

አርቲስት ሙላቱ ከበርሌይ ዩኒቨርስቲ የክብር ዲግሪ ተሰጠው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ፈጣሪው አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ታላቁ የበርክሌይ ዩኒቨርስቲ የክብር ድግሪ እንደሰጠው “ዘ ቦስተን ግሎብ” ዘገበ፡፡ ባለፈው ሳምንት የበርክሌይ ኮሌጅ በቦስተን ባከናወነው የምረቃ ስነስርዓት ከ58 አገራት የተውጣጡ 900 ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ምሩቃኑ የክብር ዲግሪ ላገኙ ባለሙያዎች ልዮ የሙዚቃ ኮንሰርት አቅርበዋል፡፡  ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር የክብር ድግሪ ከተሰጣቸው ባለሙያዎች መካከል ኪውንሲ ጆንስና ጆን ሜየር የተባሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሲገኙበት ባለሙያዎቹ በጋራ ከ221 በላይ የግራሚ ሽልማቶችን እንዳገኙ ቦስተን ግሎብ አመልክቷል፡፡ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ከ4ሺ በላይ እንግዶች እንደነበሩ የጠቀሰው ዘገባው፤ ሙላቱ አስታጥቄ በኮሌጁ ከተመረቁ የሙዚቃ ባለሙያዎች የመጀመርያው አፍሪካዊ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

ሙላቱ በምረቃው ስነስርዓት ላይ ባሰማው ንግግር፤ የበርክሌይ ኮሌጅ ለታዳጊ አገራት የሙዚቃ ባለሙያዎች በሩን መክፈቱን አመስግኖ ምሩቃኑ በአዳዲስ ፈጠራዎች እንዲተጉ ያሳሰበ ሲሆን ኢትዮ ጃዝ በዚህ መንገድ የተፈጠረ የሙዚቃ ስልት መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሶአል፡፡ አርቲስቱ ቫይብራፎን የተባለ የሙዚቃ መሳርያ እየተጫወተ “የከርሞ ሰው” የተባለውን ሙዚቃ ከተመራቂ ተማሪዎቹ ጋር ለታዳሚው ማቅረቡንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ላለፉት 40 ዓመታት በሙዚቃ ሥራው ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘት የቻለው የ68 ዓመቱ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ፤ በ1960ዎቹ በታላቁ የበርክሌይ የኮንቴምፖራሪ ሙዚቃ ኮሌጅ፣ በቫይብራፎንና በፐርኩዌሽን ሙዚቃ መሳርያዎች ተጫዋችነት እንደተመረቀ ይታወቃል፡፡

 

Read 1124 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 11:22