Saturday, 17 November 2018 11:28

ኢትዮጵያ በአፍሪካ 2ኛውን የንብ ሃብት ሲምፖዚየም ታዘጋጃለች

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 “እኛ ንቦቹ ሊሰጡን የተዘጋጁትን ያህል ማለብ አልቻልንም”


   ኢትዮጵያ ከ130 ዓመታት ላይ ባደጉ አገራት በሞኖፖል ተይዞ የቆየውን፣ በአፍሪካ ምድር ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል፣ 2ኛውን ኢፒሞንዲያ (የንብ ሀብት) ሲምፖዚየም፣ “በምግብ ምርት ሂደት ውስጥ የንቦች ሚና” በሚል መሪ ሐሳብ በቅርቡ ታዘጋጃለች፡፡  
የሲምፖዚየሙ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ በአፍሮዳይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣው መግለጫ፤ ለአምስት ቀናት ከሕዳር 21-25 ቀን 2011 በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ የሚካሄደውን ሲምፖዚየም፣ የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ቦርድ፣ ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስቴርና ከዓለም አቀፍ አናቢዎች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡  
የንብ ሀብት ያልተዘመረለት ቁልፍ የልማት ዘርፍ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ፣ ከ10 ሚሊዮን በላይ ኅብረ - ንብ (የንብ መንጋ)፣ 2 ሚሊዮን ያህል ንብ አናቢዎችና ከ7ሺህ በላይ የንብ ቀሰም ዕፅዋት ባለቤት ብትሆንም ከዘርፉ አልተጠቀመችም ያሉት የኢትዮጵያ ንብ ሀብት ቦርድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋሽ በቀና፤ ካለን 10 ሚሊዮን ኅብረ - ንብ እየተጠቀምን ያለው 70 ከመቶ ብቻ እንደሆነ፣ ከዚህም ውስጥ 95 ከመቶው በልማዳዊ መንገድ የሚገኝ ነው ብለዋል፡፡
ያደጉት አገሮች ከአንድ የንብ ቀፎ ከሰባት በላይ በኤክስፖርት ገበያው እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ያገኛሉ ያሉት አቶ ነጋሽ፤ የሚገኙትም ምርቶች የንብ ሙጫ፣ ንቦች ቀፎአቸውን ለማሞቅ የሚጠቀሙበት ምርት አንድ ኪሎ ከ600-700 ዶላር፣ ፖለን (የወንዴ አበባ ዘር) በኪሎ 500 ዶላር፣ የንብ ወተት የሚባለው ምርት አንድ ኪሎ 1000 ዶላር፣ የንብ መርዝ የሚባለው ምርት አንድ ኪሎ ከ20-25 ሺህ ዶላር እንደሚሸጥ፣ እኛ ለ3 ሺህ ዘመን የማር ምርት እንጠቀማለን እያልን የምናወራው ማርና ሰም ብቻ ነው የምናገኘው ብለዋል፡፡ እኛ ንቦች ሊሰጡን በሚችሉት መጠን ሳይሆን መውሰድ በቻልነው ደካማ አቅም መጠን ነው የምንወስደው በማለት በቁጭት የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ኢትዮጵያ ካላት የዕፅዋት ሀብት (ኢኮሎጂ) አንፃር ከዚህ በጣም ከፍ ማለት ነበረበት፡፡ ባደጉት አገሮች ከአንድ ቀፎ በአንድ ዓመት ከ150 ኪ.ግ በላይ ይሰበሰባሉ እኛ ካለን ኢኮሎጂ አንፃር ከአንድ ቀፎ ከ250 ኪ.ግ በላይ ማግኘት እንችል ነበር፡፡ እኛ ንቦቹ ሊሰጡን የተዘጋጁትን ያህል ማለብ አልቻልንም በማለት ገልፀዋል፡፡
የኋላ ቀርነታችንን መገለጫ ሲናገሩ፣ ዓለም ለንቦች የሚጨነቀው ለሚጣፍጠው ማር ወይም ለመዋቢያ የኮስሞቲክስ ኢንዱስትሪው ለሚጠቅመው ሰም አይደለም፡፡ “ንቦች ከሌሉ ሕይወት የለም” ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ የንቦች ጥቅም ማርና ሰም ብቻ አይደለም፡፡ በፖሊኔሽን፣ ወንዴ ዘር ወደ ሴቴ ዘር በመውሰድ ዕፅዋት እንዲራቡ የሚያደርጉት ንቦች ናቸው፡፡ በዚህ ዘዴም ምድሪቷ አረንጓዴ ምንጣፍ ትለብሳለች። ንቦች የተፈጥሮ ሚዛን፣ የአካባቢ የአየር ንብረት ሚዛን ይጠብቃሉ በማለት አስረድተዋል፡፡
የንብ ሀብት ዘርፍ ማደግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሲኖረው ከእነዚህም መካከል ለሥራ ፈጠራ፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለእርሻ ሰብሎች ምርታማነት፣ የውጭ ንግድ ለማስፋፋት፣ ቤተሰባዊ ሥርዓተ - ምግብና ጤናን ለማሻሻል፣ የተሻለ የተክል ዘር ለማምረት፣ ለመዋቢያ ቅባቶችና ከፍተኛ መድኃኒቶች ቅመማና ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያስችል አቅም ያለው የኢኮኖሚ አካል በመሆኑ፣ ዘርፉ የሚያስገኘው ጥቅም እንዲታወቅና ኅብረተሰቡ ስለ ንብ ሀብት ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር፣ ሲምፖዚየሙን ማዘጋጀታቸውን አቶ ነጋሽ ተናግረዋል፡፡
የኢፒሞንዲያ ሲምፖዚየም፣ ኮንፈረንስና ኤግዚቢሽን ያካተተ ሲሆን ኤግዚቢሽኑ በግዮን ሆቴል እንደሚካሄድ፣ ከ1 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ አምራቾችና የዘርፉ ተዋናዮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግንቦት 12 “የንቦች ቀን” እንዲሆን ማወጁን፣ በዚህም ዕለት ስለ ንቦች ጤና፣ ሕይወታዊና ልማታዊ ሚናቸው የሚዘከርበት ቀን መሆኑን አቶ ነጋሽ በቀና ገልፀዋል፡፡

Read 2504 times