Saturday, 17 November 2018 11:27

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ከፍተኛ ትርፍ አስመዝግቧል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)


                 የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት ወይም ያልተጣራ 938 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2011 ባንኩ በሚሊኒየም አዳራሽ ባካሄደው 9ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ጉዲሳ ቡልቶሳ ባቀረቡት ዓመታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ሪፖርት፤ ባንኩ ያስመዘገበው ትርፍ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ140 በመቶ ወይም የ547 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 41 በመቶ ዕድገት በማሳየት 19.93 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ አጠቃላይ ሀብቱ ደግሞ 23.5 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በቀደመው ዓመት ከነበረው 1.17 ቢሊዮን ብር ወደ 1.61 ቢሊዮን ብር ቢያድግም በ2019/20 በጀት ዓመት መጨረሻ 3  ቢ. ለማድረስ ከታቀደው ጋር ሲተያይ አዝጋሚ እንቅስቃሴ ስለሆነ ባለአክሲዮኖች ክፍያቸው እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል፡፡
ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት 25 አዳዲሶችን በመጨመር የቅርንጫፎቹን ቁጥር 248 ማድረሱን የጠቀሱት የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር፤ በተጠናቀቀው በዓመት 166 ወኪሎችን በመመልመል የወኪሎችን አጠቃላይ ቁጥር 200 ማድረሳቸውን፣ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 36,144 ሲሆኑ፣ ኦሮ-ካርድ ያላቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ 69,618 መድረሱን ገልፀዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ200 ዜጐች የሥራ ዕድል በመፍጠር የሠራተኞቻቸውን ቁጥር 3,226 ማድረሳቸውን የጠቆሙት አቶ ጉዲሳ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለ5ሺህ ሠራተኞች ሥልጠና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ ባንኩ፣ በአዳማ ከተማ ባለ 4 ፎቅ ሕንፃ፣ በሰንጋ ተራ ኮንዶሚኒየም ሁለት ቅርንጫፎች፣ እንዲሁም አንድ ቅርንጫፍ በክራዎን ሳይት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ በጐማ ቁጠባ የዋና መ/ቤታቸውን ሕንፃ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 24 ቢሊዮን ብር ደርሷል ያሉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ፤ የባንኩ ተቀማጭ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 48 በመቶ በመላቅ 20 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የተሰጠው ብርድ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 41 በመቶ አድጐ 11.65 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ በተጠቀሰው በጀት ዓመት ባንኩ ያገኘው የውጭ ምንዛሬ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 43 በመቶ ዕድገት በማሳየት 314.2 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡
በተጠቀሰው በጀት ዓመት የባንኩ ገቢ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 65 በመቶ በማደግ 2.47 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡ በተጠቀሰው በጀት ዓመት የባንኩ ገቢ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ 65 በመቶ በማደግ 2.47 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ ወጪው ደግሞ ካለፈው ዓመት ጋር ሲተያይ 38 በመቶ በመጨመር 1.53 ቢሊዮን ብር መሆኑን አቶ አቢ ሳኖ ገልፀዋል፡፡
የቦርድ ዳይሬክተሮች ሊቀመንበሩ አቶ ጉዲሳ ቡልቶሳ በሪፖርታቸው መጀመሪያ ላይ ባንኩ 10 ዓመት ስለሞላው 10ኛ ዓመት ክብረ-በዓሉን ከጥቂት ወራት በኋላ፣ የ10ኛ ዓመቱን አንፀባራቂ ጉዞ ሊገልጹ በሚችሉ ድርጊቶች እንደሚያከብሩ አስታውቀዋል፡፡


Read 2427 times