Saturday, 17 November 2018 11:25

አቢሲኒያ ባንክ ከ765 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 ሰኔ 30 ቀን 2018 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አቢሲኒያ ባንክ ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት ያልተጣራ 765.7 ሚሊዮን ብር ማትረፉን ገለጸ፡፡
ባንኩ የዛሬ ሳምንት በሂልተን ሆቴል ባደረገው የባለአክሲዮኖች 22ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታዬ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ ባለፈው ዓመት የተገኘው ትርፍ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 1.13 በመቶ ወይም የ88.89 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ባደረገው እንቅስቃሴ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት ክምችት 31.98 ቢሊዮን ብር፣ የካፒታል መጠኑ ወደ 4.25 ቢሊዮን ብር ማደጉን ጠቅሰው፣ የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ የ24 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 25.79 ቢሊዮን መድረሱን፣ የባንኩ አስቀማጮች ቁጥርም ከቀደመው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ34.89 በመቶ ወይም በ261,790 በመጨመር፣ 1,012,177 መድረሱን አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡
የባንኩ የብድርና ቅድሚያ ክፍያ መጠን ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ28.26 በመቶ ወይም የ3.96 ቢሊዮን ብር ጭማሪ በማሳየት 17.99 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ በጊዜ ገደብ የተሰጠ ብድር ከበፊቱ ዓመት ጋር ሲተያይ 34.58 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 3.06 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ የኦቨር ድራፍት ብድር ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 34.09 በመቶ ብልጫ በማሳየት፣ 973.62 ሚሊዮን ብር፣ የቅድሚያ ክፍያ ብድር 3.28 በመቶ ቀንሶ፣ 75.72 ሚሊዮን መሆኑን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልፀዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ባንኩ ያገኘው የውጭ ምንዛሬ፣ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 10 በመቶ ወይም 43 ሚሊዮን ብር ቀንሶ፣ 382 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ምክንያቱ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው የፖሊሲ ማሻሻያና ወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው ዕቅድ በታች መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 37.78 በመቶ ወይም የ891.71 ሚሊዮን ብር ብልጫ በማሳየት 3.27 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ጠቅላላ ወጪው ደግሞ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 47.59 በመቶ ወይም 808.81 ሚሊዮን ብር በመጨመር 2.51 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ የባንኩ አጠቃላይ ካፒታል ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 27.11 በመቶ ወይም 905.45 ሚሊዮን በመጨመር 4.25 ቢሊዮን ብር መድረሱን፣ እንዲሁም የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 42.24 በመቶ ወይም 761.1 ሚሊዮን ብር በመጨመር ወደ 2.56 ቢሊዮን ብር ማደጉን አመልክተዋል፡፡
የሠራተኞች ብዛት ከቀደመው ዓመት ጋር ሲተያይ 820 ብልጫ በማሳየት 5,825 መድረሱን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 53 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመጨመር ቁጥሩን ወደ 286 ከፍ ማድረጉን፣ እንዲሁም በተያዘው በጀት ዓመት 43 ቅርንጫፎች በመጨመር አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 329 ለማድረስ እየሠራ መሆኑን፣ በ2017/18 የገበያ አማራጮቹን ለማስፋት 3 አገልግሎቶች ማለትም ከ50 ዓመት ዕድሜ በላይ “የባለውለታዎች የቁጠባ ሂሳብ”፣ ለሴቶች “አደይ የቁጠባ ሂሳብ”፣ ለወጣቶች “አፍላ የቁጠባ ሂሳብ” ማዘጋጀቱን አቶ መሠረት ታዬ አስታውቀዋል፡፡

Read 2083 times