Saturday, 17 November 2018 11:23

18ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በፕሮፌሽናል አትሌቶች ተሳትፎ ተጠናክሯል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 የ2011 ቶታል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ እና ነገ በተዘጋጁ ሁለት ውድድሮች በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ከ47ሺ በላይ ይሳተፉበታል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች ትናንት በሂልተን ሆቴል ባዘጋጁት መግለጫ ላይ ያስታወቁት ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄደው የ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው የውድድር ዘመኑ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ሲሆን ባለፉት 10 ወራት 9 ውድድሮችን በአዲስ አበባ እና ሌሎች ክልል ከተሞች ማዘጋጀታቸውን ነው፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ባስተላለፈው መልዕክት የጎዳና ላይ ሩጫው ከ45 በላይ የአፍሪካ መሪዎች ከሚገኙበት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጋር የሚገጣጠም በመሆኑ የውድድሩ ተሳታፊዎች ለህዝብ ተምሳሌት የሚሆኑበት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአፍሪካ ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች የሆኑት  ኤርትራዊ ዘረሰናይ ታደሰ እና ኡጋንዳዊው ስቴፈን ኪፕሮቲች ታላቁ ሩጫን  በክብር እንግድነት ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡ በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው  ዘንድሮ ከመቼውም የላቀ ፉክክር ተጠብቋል፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ከተለያዩ አገራት የመጡት ፕሮፌሽናል አትሌቶች በመብዛታቸው ሲሆን ከኤርትራ 5፤ ከኬንያ 2፣ ከኡጋንዳ 2 እንዲሁም ከቦትስዋና 2 ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ ይህም በውድድሩ የ18 ዓመታት ታሪክ  ከፍተኛ የፕሮፌሽናል አትሌቶች  ስብስብ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የውድድሩን ደረጃ በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ለማድረግ ሲባልም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ፀረ ዶፒንግ ድርጅት ጋር በመተባበር በአሸናፊ አትሌቶች ላይ ምርመራ ማካሄዱም በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሚተገበር ይሆናል፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጆች በጋዜጣዊ መግለጫው ለዘረሰናይ እና ለኪፕሮቲች የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ሞዴል ልዩ ስጦታን፤ ለሜክሲኮው አምባሳደር በአምባሳደሮች ውድድር የሚሳተፉበትን የመሮጫ ቁጥር፣ የዓለም የግማሽ ማራቶን ሪኮርድ ያስመዘገበችው እና በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አሸንፋ ለምታውቀው ነፃነት ጉደታ  ሽልማት አቅርበው የታላቁ ሩጫ ለኢትዮጵያ የቦርድ ሰብሳቢ ኃይሌ ገ/ስላሴ አበርክቶላቸዋል፡፡
የቶታል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገሩት ኩባንያቸው የጐዳና ላይ ሩጫውን በስፖንሰርሺፕ በመደገፍ ረጅም ጉዞ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ሩጫ የኢትዮጵያ ልዩ መንፈስ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ በተሳተፏችን ደስተኞች ነን ብለዋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን የመራው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድር ዲያሬክተር ኤርምያስ አየለ  ይህን ተከትሎ በሰጠው መረጃ ቶታል ኢትዮጵያ የጐዳና ላይ ሩጫውን እስከ 2021 እ.ኤ.አ  ስፖንሰር በማድረግ ለመስራት ተስማምቷል፡፡ ባለፉት 10 ወራት ከ11 በላይ ውድድሮችን ማዘጋጀቱን በተጨማሪ ያስታወቀው ኤርምያስ አየለ፤  የእሁድ ውድድርና የዓመቱ መርሃ ግብር ማጠቃለያ ይሆናል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት ተወካይ የሆኑት አቶ ሲሳይ ጌታቸው ደግሞ “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ  የቱሪዝም ምርት መሆኑን ጠቁመው ውድድሩ በተለያዩ አገራት መካከል በሚፈጥረው ትስስር  በጐ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ካመሰገኑ በኋላ፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስኬት ያላቸው አትሌቶች መፍለቂያ መሆኗ ከድርጅታችን አዲስ መርህ ጋር የሚጣጣም  ብለውታል፡፡
በጋዜጣው መግለጫው ላይ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ አማካሪ የሆነው እንግሊዛዊው ሪቻርድ ኔሩካር በ1968 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ ማሞ ወልዴ ያስመዘገበውን የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ ቪዲዮ ለእይታ ያቀረበ ሲሆን፤ የማሞን የኦሎምፒክ ድል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ስጦታ መዘጋጀቱን ከገለፀ በኋላ በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ለሆኑት ቪክቶር ቲርናዬ 507 የመሮጫ ቁጥር ከኃይሌ ገ/ስላሴ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ መደሰቱን በመግለጫው ላይ ሲናገር ኃይሌ ገ/ስላሴ በበኩሉ ስፖርት የሰላም መሳርያ መሆኑን ለማመልከት ‹‹ ተመልከቱን ምንም ልዩነት የለንም፣ በሌላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራዊያን ለይቶ የሚመለከት የለም፡፡›› ብሏል፡፡ በ2004 አቴንስ ኦሎምፒክ ቀነኒሳን እና ስሺን ተከትሎ  በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈው አትሌት ዘረሰናይ ታደሰ በረጅም ርቀት የትራክ፤ የአገር አቋራጭ እና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ከኤርትራ አትሌቶች ከፍተኛውን ስኬት ያስመዘገበ ነው፡፡  ዘረሰናይ በተለያዩ የዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች 6 የአሸናፊነት ሽልማቶች ያገኘ ሲሆን አራቱን በግማሽ ማራቶን፣ አንዱን በ20 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ሌላኛውን በ12 ኪሎ ሜትር እና የሞምባሳው የዓለም አገር አቋራጭ ላይ የተቀዳጃቸው ውጤቶች ናቸው፡፡ የቀድሞ የግማሽ ማራቶን ሪከርድ ባለቤት የነበረም ሲሆን ክብረወሰኑን በኬንያዊ አትሌት የተነጠቀው በቅርቡ ነው፡፡   
ኡጋንዳዊው ስቲፈን ኪፕሮቲች በበኩሉ በረጅም ርቀት ሩጫ ለደረሰበት ውጤት ተምሳሌት ካደረጋቸው ስፖርተኞች በተለይ ለኃይሌ ገ/ስላሴ ልዩ ክብር እንዳለው ተናግሯል፡፡ ከ2007 እ.ኤ.አ በበፊት ኃይሌ ገ/ስላሴ በአትሌቲክሱ ውጤታማ ለመሆን ልምምዶችን በልዩ ትኩረትና ጥንካሬ  እንድሠራ፣ ገንዘብ ላይ እንዳላተኩር ፤ገንዘብ ከስኬትት በኋላ እንደሚመጣ መክሮኝ ነበር፡፡ ይህን ምክሩን በመስማቴ ዛሬ ለኡጋንዳና ለአፍሪካውያን አትሌቶች ተምሳሌት ሆኛለሁ ብሏል፡፡ አትሌት ስቴፈን ኪፕሮቲች  በ2012 እኤአ ላይ በለንደኑ ኦሎምፒክ በማራቶን የመጀመርያን የወርቅ ሜዳልያ ለኡጋንዳ ማስገኘቱ እና በ2013 እኤአ ላይ ደግሞ በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ሌላ የወርቅ ሜዳልያ ማሸነፉ ይታወቃል፡፡
በ10 ኪ.ሜ የጐዳና ሩጫው  የኢትዮጵያ አትሌቶች ጠንካራ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፤ በወንዶች ምድብ በ16ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሸነፈው አቤ ጋሻሁን፣ በ12ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ያሸነፈው ሐጐስ ገ/ህይወትና የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብን የወከለው አዱኛ ታከለ ከፍተኛ ግምት ወስደዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ አትሌት እታገኝ ወልዱ፣ አትሌት ዘውድነሽ አየለ፣ አትሌት ስለናት ይስማው እና አትሌት ሐዊ ዓለሙ ይወዳደራሉ፡፡
ባለፉት  ሁለት ዓመታት በ10 ኪሎሜትር የጎዳና  ሩጫው ተግባራዊ የሆነው የሁለት ዓይነት ማእበል አነሳስ ዘንድሮም እንደሚኖር የገለፁት አዘጋጆች ከ6 ኪሎ ወደ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚሰለፉት የቀይ ማዕበል ተሳታፊዎች ውድድሩ ተጀምሮ አካባቢውን ለመልቀቅ 20 ደቂቃ ሊፈጅባቸው እንደሚችል እንደሚችል ገምተዋል፡፡ በሌላ በኩል በዛሬው እለት 3ሺ ተሳታፊዎች ያሉት የፕላን ኢንተርናሽናል የልጆች ውድድር ከጠዋቱ 3 ሰዓት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡

Read 1756 times