Sunday, 18 November 2018 00:00

በቤኒሻንጉል ላሉ የግጭት ተፈናቃዮች እርዳታ ማድረስ አልተቻለም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል

 በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ አሁንም አስተማማኝ ባለመሆኑ በግጭት ለተፈናቀሉ ከ57 ሺህ በላይ ዜጐች አስፈላጊውን ዕለታዊ እርዳታ ለማድረስ መቸገራቸውን ዓለማቀፉ የረድኤት ድርጅቶች ገልፀዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፣ በቅርቡ ተፈጥሮ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት ተፈናቅለው ኦዳ አካባቢ ለሚገኙ 15 ሺህ ያህል እንዲሁም ካማሺ ዞን ውስጥ ለሚገኙ 42 ሺህ ያህል በድምሩ ለ57 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች የእለት ደራሽ እርዳታ ለማቅረብ በአካባቢው ግጭት ባለመቆሙና የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ የተነሣ መቸገሩን ጠቁሟል፡፡
ዜጐቹ ከተፈናቀሉ 2 ወር ያህል ቢሆናቸውም እስካሁን እርዳታ የቀረበላቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያለው ጽ/ቤቱ፤ አሁንም መንግስት የራሱን መዋቅር ተጠቅሞ በወታደራዊ ከለላ ነው ያቀረበው ብሏል።
በሁለቱ አካባቢዎች የሚገኙ ከ57ሺህ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ የገለፀው ጽ/ቤቱ፤ መንግስት ለሁኔታው ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
በወቅቱ ተፈጥሮ በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት በአጠቃላይ ከተፈናቀሉ 240 ሺህ ዜጐች ውስጥ 182 ሺህ ያህሉ በኦሮሚያ በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ መጠለላቸውንና በቂ ባይሆንም እርዳታ እያገኙ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት 2.2 ሚሊዮን በግጭትና በአየር ፀባይ ለውጥ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ጨምሮ በድርቅና በተለያዩ ምክንያቶች እርዳታ ጠባቂ ለሆኑ 7.95 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የገለፀው የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ፤ እስከ 2018 እ.ኤ.አ መጠናቀቂያ ድረስ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ለእርዳታ ያስፈልጋል ብሏል፡፡

Read 6085 times