Sunday, 18 November 2018 00:00

መቄዶንያ በ10ሩ ክ/ከተሞች ተጨማሪ ማዕከላትን ለመገንባት አቅዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

· አየር መንገድ ለማዕከሉ ህንፃ ሊገነባ ነው
· ፓይለቶች 10ሚ. ብር ለመለገስ ቃል ገብተዋል

  መቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል የከተማ አስተዳደሩ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች ሊሰጥ ቃል በገባው ቦታ ላይ ተጨማሪ ማዕከላትን ለመገንባት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ፤ አንድ ህንፃ በነፃ ገንብቶ ለማስረከብ ቃል ገብቷል፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማዕከሉ በ10ሩም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ቦታ ለመስጠት ቃል መግባቱን ያስታወሱት የማዕከሉ መስራችና ስራ አሥኪያጅ አቶ ቢኒያም በለጠ፤ ሊሰጥ የታሰበው ቦታ ፕሮጀክቱን የበለጠ ለማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በአሁን ወቅት በማዕከሉ 2 ሺህ ያህል ዜጎች ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን በአጭር ጊዜያት ውስጥ የማዕከሉን አጠቃላይ የመቀበል አቅም 10 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊነት ህብረተሰቡና የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን አቶ ቢኒያም ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ አሁንም ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማዕከሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ሰርግ፣ ተዝካርና ልደት ደጋሾች በማዕከሉ እየመጡ ከማዕከሉ ነዋሪዎች ጋር ቆይታ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ በማዕከሉ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “እውነተኛ አክሊል የሚገኘው ከእንደዚህ አይነት ስፍራ ነው፤ መጥታችሁ በጉልበት ብታገለግሉ፣ ባላችሁበትም ሆናችሁ 8151 ላይ ቴክስት ብታደርጉ ምስጋናው ከላይ ነው እባካችሁ እርዱ” ሲሉ የተማፀኑ ሲሆን፤ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው ማዕከሉን በተደጋጋሚ እየጎበኙ መሆኑም ታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ በማዕከሉ ጉብኝት ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ለማዕከሉ አንድ ሙሉ ህንፃ ገንብተው ለማስረከብ ቃል ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም የአየር መንገዱ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ፓይለቶች እያንዳንዳቸው ከኪሳቸው 10 ሺህ ብር በማውጣት፣ በድምሩ 10 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡
የአየር መንገዱ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅትም አስር ተሽከርካሪዎችን፣ የምግብ ማብሰያ እቃዎችን አልባሳትና የተለያዩ ቁሳቁሶችን አበርክተዋል፡፡ አየር መንገዱ ወደ ውጪ ሄደው ለሚታከሙ የማዕከሉ ተጠቃሚዎች በአመት የመቶ ደርሶ መልስ ነፃ ቲኬት ለመስጠት ቃል ገብቷል፤ በተጨማሪም የጁስ መጭመቂያ ዘመናዊ ማሽን ገዝቶ ለመስጠትም አየር መንገዱ ቃል ገብቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አየር መንገዱ ለማዕከሉ ነፃ የካርጎ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ በሁሉም በረራዎች ላይ ማዕከሉን ለማስተዋወቅና የእርዳታ ማሰባሰቢያ ሳጥኖችን አውሮፕላን ውስጥ ለማስቀመጥ ቃል መግባቱ ታውቋል፡፡
ማዕከሉ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እያገኘ ቢሆንም አሁንም ለማዕከሉና ማዕከሉን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል፡፡   


Read 6147 times