Monday, 12 November 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ፣ የገደለ ይሙት” በሚባልበት ዘመን፣ በአንድ አገር የሚኖር የንጉሥ አጫዋችና አዝማሪ ነበር፡፡ ይኸ ሰው አንድ ቀን በማን አለብኝነት ተነሳስቶ፣ የአንድ ምስኪን አንጥረኛን ዓይኖች አጠፋ፡፡ የአንጥረኛው ልጆችና አገሬው … “ፍትህ ለተበዳይ!” ብለው አደባባይ ወጡ፡፡ ንጉሡም የቧለሟሉን ክፋት ያውቅ ነበርና እንደ ተበዳዩ የሱም ዓይን እንዲጠፋ ፈረደበት። የአንጥረኛው ቤተሰቦችና በአደባባይ የተገኘው ሁሉ “እልልልል!” አለ፡፡ ቅጣቱ ሊፈፀም ሲቃረብ…
“እንዳትነኩት!” የሚል ነጎድጓዳማ ድምፅ ተሰማ። ቀና ሲሉ የብርሃንና የፍትህ አምላካቸው ሻማሽ ነበር። እነሱም … “ስለ ምን እንተወዋለን? … ህግ ይሻራልን?” በማለት ጠየቁት፡፡ ...
“አይሻርም” አላቸው፡፡
“ታዲያ ጥፋታችን ምንድነው?” ሲሉት
“ዓይኑን አታጥፉት፣ ምላሱን ቁረጡት” አላቸው።
“አቤት! ፍርደ ገምድልነት!” እያሉ ተንጫጩ፤ አጉረመረሙ፡፡ … ሆኖም ትዕዛዙ ተፈፀመ፡፡ … በተሰጠው ፍርድ ከህዝቡና ከተበዳዩ ቤተሰቦች የበለጠ የተበሳጩት ግን ወንጀለኛውና ቤተሰቦቹ ነበሩ፡፡ ይህን ያስተዋለው ህዝብና የከሳሽ ቤተሰቦች…
“ፍርድ የተጓደለብን እኛ ሆነን እናንተ ስለ ምን ታዝናላችሁ?” በማለት ሲጠይቋቸው …
“አምላካችን አልፈቀደም እንጂ ዓይኑ ቢጠፋ ይሻል ነበር፤ የብርሃን አምላክ ነውና ፍትህን ሰጠ” በማለት ምክንያታቸውን ነገሯቸው፡፡ እነሱም ከድንቁርናቸው ባንነው … “ሻማሽ ሆይ! አንተ ታላቅ ነህ” እያሉ ለአምላካቸው አጨበጨቡ፡፡ … ግን ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?
*   *   *
 ወዳጄ፡- “ዲሞክራሲና ፍትህ የተዳሩ ናቸው” … ሲባል በዴሞክራሲያዊ ስርዓት፤ ህግ የአብዛኛውን ሰው ፍላጎት በሚያስከብርበት መንፈስ ይተረጎማል እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ዋጋ የሚኖረው ግን ግለሰብዓዊ መብትና ነፃነት እስከነ መገለጫዎቹ … ማለትም የመጻፍ፣ የመናገር፣ ስዕል የመሳል፣ ሙዚቃ የማቀናበር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ አድማ የመምታትና የመሳሰሉት ሲከበሩ እንደሆነ ይታሰባል፡፡
ብዙ ሊቃውንቶች … ፍትህ ድንጋጌ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ “ፍትህ …የኑሯችንን መደብ የምናደላድልበት ወይም የምናስተካክልበት ወይም ዕውነትን የምናሽሞነሙንበት ዘውግ ናት፡፡ ፍትህም ሆነ ኢ-ፍትሃዊነት አብሮን የሚገኝ፣ የኑሮ ዘይቤአችን መገለጫ እንጂ ፈልገን የምናገኘው፣ ስናገኘው የማናውቀው፣ ስናውቀው የማንረዳው … ሩቅ ያለ መንፈስ ወይም የፈላስፎች ዕንቁ (Philosophers’  stone) አይደለም” ይላሉ፡፡
ፍትህ … እንደ ፍቅር ውቃቢ (Romans) አየሩ ውስጥ የተዘራውን ወይም የሚወራውን ነገር በተለያዩ ቀለማት እያስዋቡ መደጋገም ሳይሆን … እንዴት “መባል”፣ እንዴት “መነገር” .. እንዳለበት ማወቅና ልከኛውን ገፅታ ማሳየት ነው፡፡ መደረግ የሚገባውን ወይም መሆን ያለበትንም እንዴት እንደሚደረግ ወይም እንዴት ሊሆን እንደሚችል አውቆና ፈፅሞ መገኘት ነው፡፡
ወዳጄ፡- ፍትህ ስትደበቅ … እምነት ‹ሃይማኖት› መሆኑ ቀርቶ ‹ስሜት› ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ዜጎች መብታቸው በህግ ሊከበርላቸው ካልቻለ፣ መንግስት በንፅህናና በተሰጠው ኃላፊነት ለማገልገል አቅም ካጣ፣ ከታበየና ከነቀዘ ወይም … በሥራ፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በመኖሪያ ቤት ቦታ፣ በዳኝነት ወንበር፣ በጤና ጥበቃ፣ በመብራትና ውሃ አቅርቦትና በመሳሰሉት ሲቪል አገልግሎቶች አድሏዊ ከሆነ፣ በአጠቃላይ በመንግስት ሃብትና ንብረት ላይ ዜጎች ዕኩል መብት፣ እኩል ጥቅምና እኩል ኃላፊነት እንዳላቸው ካልተገነዘበ ዜጎች ይቆጣሉ፡፡ አንዱ የበኩር፣ ሌላኛው የእንጀራ ልጅ ሲሆን እምነት ይጠፋል፤ ጥርጣሬ፣ ቁጭት፣ ምሬት --- እየበዛ የሃገር ፍቅር ይቀንሳል፡፡ ፍትህ አልባ ስርዓት “ያለግዛብሔር ማን አለን፣ ምነው ከዚህ አበሳ ቢገላግለን፣ እሱ ያመጣብን መዓት ነው፣ ለሱ ካልሆነ ለማን አቤት ይባላል?” የሚሉ ብሶተኛ ዜጎችን ያፈራል። ከፍቅር ሳይሆን አማራጭ ከማጣት፣ ከልብ ሳይሆን ከስጋት የመነጩ እርስ በራሳቸው እንኳ የማይተማመኑ አምልኮቶች የሚስተናገዱባቸው የእምነት ድርጅቶች ከተማውን ይሞሉታል፡፡ ወዳጄ፡- እምነት ስሜት ሲሆን አክራሪነት ይወለዳል፡፡ አክራሪነት ከስሜት፣ ስሜት ደግሞ ፍትሃዊ አስተዳደር ካለመኖር ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
መጥፎ አስተዳደራዊ ስርዓት ባለበት ፍትህ የጨቋኞች መሳሪያ ልትሆን ትችላለች። ምክንያቱም መንግሥት የሚያወጣቸውን ህጎች ራሱን በሚጠቅመው መንገድ ለመተርጎም እንዲያስችላቸው አድርጎ ነው፡፡ ለመሰለው ‹ፍትሃዊ›፣ ላልመሰለው በፍትሃዊነት ስም ኢ-ፍትሃዊ ይሆናል። በዳንስ ምሽት ላይ በተጭበረበሩ ብዙ ካርዶች “Queen of the night” ሆና እንደተመረጠች ውብ ኮረዳ ያደርጋታል፡፡ “ኢ-ፍትሃዊ መንግስት፤ ጉልበትና ገንዘብ ካለ የማይቻል ነገር የለም” እያለ ወደ መቃብሩ ይወርዳል ይባላል፡፡ “… ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ” እንዲሉ፡፡
ወዳጄ፡- ቀመር ምን መሆን እንዳለበት ታላቁ ሊቅ ኸርበርት ስፔንሰር እንዲህ ብሎ ጽፎልናል፤ “እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን የማድረግ ነፃነት አለው። ይኸ ነፃነቱ ግን ‹ነፃነት› የሚሆነው ሌሎችም ሰዎች እንደሱ የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ሲረጋገጥ ነው .. (Every man is free to do that which he wills, provided he infringes not the equal freedom of any other man)”
 የሃርቫርዱ ጆን ራውሊንግም “ሁለቱ የፍትህ መርሆዎች” በሚለው ፅሑፉ፤ (ፕሪንሲፕል ኦቭ ኢንኢኳሊቲስ የሚለውን ትተን) የስፔንሰርን ሃሳብ … “Each person engaged in an institution or affected by it has an equal right to the most extensive liberty compatible with a like liberity for all” በማለት አብራርቶ ፅፎታል። ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የወርቃማው ህግ መቋጫዎች ይመስላሉ፡፡
ጥያቄው፡- “ሃይማኖተኛ ነን” እያሉ የሚናገሩ የፍትህና የአስተዳደር ባለስልጣናት ሌላው ቢቀር ስለ ‹ወርቃማው ህግ› ያውቃሉ ወይ? … የሚል ነው። መልሱ፡- ‹ደ ዠ› ሌላ! ‹ደ ፋክቶ› ሌላ!!
ወዳጄ፡- የፍትሃዊነት አንዱ መገለጫ; “ትክክለኛን ሰው በትክክለኛው ቦታ ላይ” (The right man at the right place) ተቀምጦ ማየት ነው፡፡ በልከኛ ቦታቸው ላይ የሚገኙ ሰዎች ህዝባቸውን ለመርዳት የሚቻላቸውን ያደርጋሉ፡፡ ከሚቀበሉት የሚሰጡት በእጅጉ ይበዛል፡፡ በዜጎች መሃል መተማመን እንዲኖር፣ ፍትህና ወዳጅነት እንዲጎለብት ‹ዋስ› ይሆናሉ፡፡ ህመማቸው የዜጎች ስቃይ የሆነው የተነቃነቁ ጥርሶች ወልቀው፣ የሚታከሙትም ድነው, “እፎይ” የሚያሰኝ ፍትሃዊ ስርዓት በእግሩ ማቆም ነው፡፡
ወዳጄ፡- መልካም ሰዎችና የለውጥ ተሟጋቾች የሚያደርጉት ትግል ፍሬያማ የሚሆነው እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን ሲወጣ ነው፡፡ ታላቅ ኦርኬስትራ ትርጉም ያለው፣ ውብና ማራኪ ሙዚቃ የሚፈጥረው እያንዳንዱን መሳሪያ በሚጫወተው ሙዚቀኛ አስተዋፅኦ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ሰሞን ያየነው ሹመት በፍትህ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሴክተሮች “ሴቶች አልተቻሉም!” የሚያሰኝ ነው፡፡
አርስቶትል … “Educate a man, you educate an individial. Educate a woman, you educate a nation” በማለት የፃፈው ከ2400 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ቢዘገይም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አመራረጥ እኔ እንደሚመስለኝ፣ ፍትሃዊና ለውጡን በከፍተኛ ደረጃ እንደ ማገዝ ሊቆጠር የሚገባ ነው፡፡ እዚህ ጋ ግን “The right woman at the right place” በማለት የእንግሊዝኛውን አባባል ብናስተካክለው ፍትሃዊ የሚያሰኘን ይመስለኛል፡፡
*   *   *
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አምላክ ሸማሽ፤ ወንጀለኛው ዓይኑ እንዳይጠፋ፣ ምላሱ እንዲቆረጥ ያደረገው ተበዳዩ አንጥረኛ በመሆኑ በዓይኑ እያየ ካልሰራ፣ ቤተሰቦቹን ማስተዳደር እንደማይችል በማወቁ ነው፡፡ በዳዩ ግን የንጉሥ አጫዋችና አዝማሪ ስለሆነ ዓይኑ ቢጠፋ ስራው ይቀጥላል፣ ቤተሰቦቹ አይቸገሩም፡፡ ምላሱ ከተቆረጠ ግን ስራው አበቃ፣ ቤተሰቦቹ እንደ ተበዳዩ ቤተሰቦች ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ ፍትህ መስጠት ነበረበት፡፡ ህዝቡ ይኸን ሲያውቅ፤ ሸማሽ በርግጥም ፍትሃዊ አምላክ ነው ብሎ ነበር ጭብጨባውን ያቀለጠው። እዚህ ጋ ፍትህ ድንጋጌ ሳይሆን አተረጓጎም ነው አያሰኝም? … ከባለሙያዎቹ እንማራለን፡፡
ሠላም!!

Read 1640 times