Monday, 12 November 2018 00:00

“ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ለማዘጋጀት በጣም ብዙ ይቀረናል”

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ኤግዚቢሽን አካሂዳለሁ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም
             
    በአጋጣሚ ነው ኢቬንት ወደ ማዘጋጀት የገባችው። “መጀመሪያ የመጣልኝ ማስታወቂያ ከኢቬንት ጋር የተያያዘ፣ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ማስተዋወቅ ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሚሰሩ ስራዎች ነበሩ፡፡ ጉምሩክ ጉዳይ ማስፈፀም፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ማምጣት፣ እንግዶች የሚመጡበትን መንገድ መከታተል …የመሳሰሉ ሥራዎች ተሰጡኝ፡፡  በዚህ ዓይነት ነው ከማስታወቂያ ሥራ ወጥቼ፣ ወደ ኢቬንት አዘጋጅነት የገባሁት” ትላለች - የኢትኤል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ፡፡
ኢትኤል የተቋቋመው በንግድ ኩባንያዎችና በማስታወቂያ ድርጅቶች መካከል የነበረውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ለመሙላት በማሰብ ነው። ማስታወቂያው እንዴት ይተዋወቅ? በምን መጠን? በቢልቦርድ ወይስ በጋዜጣ? በቴሌቪዥን ወይስ በራዲዮ? … የሚለውን ለመስራት ከአምስት ዓመት በፊት የማስታወቂያ ድርጅቷን እንደመሰረተች  ወ/ሮ ሃይማኖት ትናገራለች፡፡
ኢቬንት አዘጋጅነት እንዳሰበችው ቀላል ሆኖ አላገኘችውም፡፡ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ሆነባት፡፡ ያለቀሰችበትና ለማቆም ያሰበችበት ጊዜ ሁሉ እንደነበረ ታስታውሳለች፡፡ ነገር ግን እልህና አልበገር ባይነት ብርታት ሆነዋት እስካሁን ዘልቃለች፡፡ “ሁኔታዎች ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀሩ እየተሻሻሉ መጥተዋል፤ ለወደፊት ተስፋ ሰጪ ነገሮች ይታዩኛል” ብላለች - ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ 22 እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በ1982 ተወልዳ ያደገችው ወ/ሮ ሃይማኖት፤ ከአድማስ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተመርቃለች፡፡ በተለያዩ ድርጅቶች በማርኬቲንግ ሙያ፣ የቲቪ ፕሮግራም በማስተዋወቅና በማስታወቂያ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ መስራቷንም ትገልፃለች፡፡
በአሁኑ ወቅት እየሰራች ያለችው በዋናነት ሁለት ነገሮችን ነው - የንግድ ትርዒቶች (ትሬድ ፌር) እና ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት፡፡ በዓመት ውስጥ አምስት ኤግዚቢሽኖችን ታዘጋጃለች፡፡ የኮንስትራክሽን፣ የግብርናና የምግብ፣ አዲስ ፓወርና ኤሌክትሪክ ኤግዚቢሽንም እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር ጋር በመተባበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ዓመታዊ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን፣ ከጀመርን ድርጅት ጋር በተባባሪ አዘጋጅነት “አፍሪካ ሶርሲንግ ኤንድ ፋሽን”ን በአገር ውስጥ ታስተዋውቃለች። ከዚህ ሌላ የፋብሪካና የቤት ምርቃት፣ የፕሬስ መግለጫ ዜናዎችንና ምርት የማስተዋወቅ ሥራ እንደምትሰራ ጠቁማለች፡፡
የኢቬንት አዘጋጅነት ዘርፍ ለብዙ ጊዜ ስለተሰራበት አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ማደግ ባለበት ደረጃ አላደገም - ትላለች ሃይማኖት፡፡ “ሕዝቡ አስፈላጊነቱ ብዙም የገባው አይመስልም፤ ለምሳሌ፡- አዲስ ፋብሪካ፤ አዲስ ምርቱን ሆቴል ተከራይቶና ቦታውን ትንሽ አሰማምሮ፣ ቢሮ ውስጥ ባሉ የማርኬቲንግ ሠራተኞች ማስተዋወቅ ይችላል። ኢቬንት ማዘጋጀት ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ ኢቬንት ማዘጋጀት፣ የፋብሪካ ምርቃትም ሆነ ምርት ማስተዋወቅ፣ ለሕዝብ ማቅረብ ነው፡፡ ሰው ለመምጣት የሚመቸው ቦታ የት ነው? የሚቀበለው ሰው ማነው? የሚቀመጡበት ቦታ አመቺነት እንዴት ነው? መፀዳጃ ቤቱስ? በመድረክ የሚቀርበው ምንድን ነው? የድምፅ ሲስተሙ ጥራት እንዴት ነው? መድረኩን የሚመራው ሰው ማንነትስ? ከመድረኩ ጀርባ ያለው ሳቢነት? ...በኢቬንቱ ወቅት የሚሰራው አጠቃላይ ሁኔታ፣ … ሰዎች “እንዲህ ዓይነት ቦታ ሄጄ ደስ ብሎኝ መጣሁ” የሚል ስሜት እንዲፈጥርባቸው፣ ዝግጅቱን ወደ ፐርፌክሽን (ፍፁማዊነት ደረጃ)ማምጣት ያስፈልጋል፡፡” ትላለች።
 “ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን አዘጋጆች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ከማን ጋር እንሥራ? የሚለውን ጥያቄ መፍታት ከቻሉ ወይም አንድ ኤግዚቢሽን አዘጋጅ ድርጅት አገር ውስጥ ካለ፣ እንደ ዘርፍ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ አገር የምንገኝ ኤግዚቢሽን አዘጋጆችና ውጭ አገር (ለምሳሌ ጎረቤት ኬንያ) ያሉ ኤግዚቢሽን አዘጋጆች የሚሰሩበት መንገድ በጣም ይለያያል። ለብዙ ዓመታት ኤግዚቢሽኖች ሲዘጋጁ የቆዩት በኤግዚቢሽን ማዕከል ነው፡፡ በቅርቡ ነው ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላል በተባለው ሚሌኒየም አዳራሽ ማዘጋጀት የተጀመረው። አንድና ሁለት አዳራሾች ባሉበት፣ ነገር ግን በተለያዩ ዘርፎች ፍላጎቱ ከፍተኛ በሆነበት አገር፤ ኤግዚቢሽን አዘጋጆች መኖራቸውና ዘርፉ መስፋቱ፣ የውጭ አገር አዘጋጆች ወደዚህ እንዲመጡ ያደርጋል” ብላለች፡፡
ኤግዚቢሽኖች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳላቸው ወ/ሮ ሃይማኖት ትናገራለች፡፡ ምክንያቱም በየዘርፉ ላይ ያተኮሩ ኤግዚቢሽኖች ናቸው የሚዘጋጁት፡፡ በኮንስትራክሽን፣ በእርሻና በምግብ፣ በኤሌክትሪክ፣ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዙ … ወዘተ ብዙ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ኤግዚቢሽኖች ይዘጋጃሉ፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ፣ የቴክኖሎጂ ልውውጡንና ንግዱን ለማስፋት፣ አገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለውጪ ለማሳየት፣ ውጭ አገር ያሉና ወደዚህ ያልገቡ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ ገበያ እንዲገቡ ለማድረግ… በእጅጉ ይጠቅማሉ፡፡ በተለየ ዘርፍ ጥሩ ኤግዚቢሽን ለመፍጠርና የወደፊት ኢንቨስትመንት ለማምጣትም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ትላለች - ሃይማኖት፡፡  
አንድ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ የአገር ውስጥ ከሆነ፣ አገር ውስጥ ያሉ አምራቾች ለአገር ውስጥ ገዢዎቻቸው “አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አምጥተናል፤ ከአሁን በፊት እንጠቀምበት የነበረው ሲስተም ይኼ ነው፤ አሁን ግን የምንጠቀመው ይኼንን ነው፣ አዲሱ ሲስተም እንዲህ እንዲህ ላሉ ነገሮች ይጠቅማል” በማለት.. በራዲዮና በቴሌቪዥን ከሚቀርበው በተሻለ በገሃድ በማቅረብ  ያስተዋውቃሉ፡፡
የውጪዎቹ አዘጋጆች ደግሞ አገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ያያሉ፡፡ በአንዳንድ ዘርፎች ካሉን ነገሮች ይልቅ የሌሉን ይበዛሉ፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ዓመት ሲመጡ፣ የህዝቡ ፍላጎት የሆነውን ምርት ይዘው ይመጣሉ፡፡ የምግብ ምርቶች፣ የልጆችና የእናቶች አልባሳት፣ ዳይፐር ሳይቀር ብዙ ምርቶች ከውጭ ነው የሚገቡት፡፡ የአገር ውስጥ ኢንቨስተር ያለውን ፍላጎት አይቶ ወደ ዘርፉ ይገባል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ደግሞ በተገነዘቡት የሕዝቡ ፍላጎት መሰረት፤ ብዙ ዕቃዎችን ይዘው በመምጣት፣ ገበያው ብዙ አማራጮች እንዲኖሩት ያደርጋሉ፡፡ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት ይጠነክራል፤ የህዝቡን ፍላጎት ያዩ ኢንቨስተሮች፣ አገሪቱን የኢንቨስትመንት ማዕከል በማድረግ፣ ዕቃዎቹን እዚሁ በማምረት ለገበያም ያቀርባሉ፡፡
ከዚህም በላይ ኤግዚቢሽን፤ ቱሪዝምን የማሳደግ አቅሙ ከፍተኛ ነው የምትለው ሃይማኖት፤ አንድ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን በዚች አገር ሲዘጋጅ፤ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና ከማን ጋር መስራት እንደሚችሉ ለማየትና ግንኙነት ለመፍጠር በትንሹ 100፣ ከፍ ሲልም 500 እና 600 ያህል ሰዎች ይመጣሉ - ብላለች፡፡ አምስትና ስድስት መቶ የሚሆኑ ሰዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ለአራትና አምስት ቀን ቆይተው አገሪቷን ካዩ፣ ሆቴሎች ካረፉ፣ ምግብና መጠጥ ከተጠቀሙ፣ … የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ፤ የአገሪቷን ገጽታ በመቀየር ረገድ የሚጫወቱትም ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
የኢቬንት ኦርጋናይዚንግ  ዘርፍ ብዙ ችግሮች እንደነበሩት፣ አሁን ግን ችግሮቹ እየተቀረፉ መምጣታቸውን የጠቀሰችው ወ/ሮ ሃይማኖት፤ ችግሮቹ ይፈጠሩ የነበሩት ሆን ተብሎ  ሳይሆን አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ስለ ኤግዚቢሽን ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ እንደነበር ጠቅሳለች፡፡ “አሁንም ችግሮች ሙሉ  ለሙሉ  ባይቀረፉም ፍላጐቱ ስላለ፣ እኛም እየተጋፈጥን፤ የውጭ አዘጋጆችም እየመጡ እንሠራለን” ብላለች - ሃይማኖት፡፡
የቪዛ ውጣ ውረድ
አሁን ትልቁ ነገር የቪዛ ኦንላይን መፈቀድ ነው ያለችው ማኔጂንግ ዳሬክተሯ፤ሰዎች ኦንላይን በማመልከት ኤግዚቢሽኑን መጥተው መሳተፍ ይችላሉ፤ ብላለች፡፡ ነገር ግን አሁንም የኮንፈረንስ ቪዛና ለአጭር ጊዜ ቢዝነስ የሚመጡ ሰዎች ቪዛ ጉዳይ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ለእነዚህ ቪዛዎች ማመልከት የሚቻለው ኤግዚቢሽኑ 10 ቀን ሲቀረው ነው፡፡ 10 ቀን ሲቀረው ማለት ደግሞ ሁሉም የኤግዚቢሽኑ ነገር አልቋል ማለት ነው፡፡ ያ ሰው ቪዛ ቢከለከል ለቦታ ከፍሏል፤ ከሚያርፍበት ሆቴል ጋር ተዋውሏል፤ ለአየር መንገድ ከፍሎ ቲኬት ቆርጧል፤ ምንም የሚያደርገው ነገር ስለሌለ ከፍተኛ ፍርሃት ነው የሚፈጥርበት። የቪዛ ጉዳይ በአገር ደረጃ የሚወሰን ስለሆነ ቀደም ብሎ ታይቶ፣ ይቻላል አይቻልም የሚለውን ነገር አመልካቹ  ማወቅ አለበት፡፡
“የኮንፈረንስ ቱሪዝም በተስፋፋባቸው አገሮች፤ ለኮንፈረንስና ለኤግዚቢሽኖች ያን ያህል ዝግ የሆነ የቪዛ ክልከላ የለም፡፡ ለምሳሌ በጐረቤት ኬንያ፤ የቪዛ ነገር በጣም ቀላል ነው፡፡ የአየር ቲኬት ገዝተህ መሄድ ብቻ ነው፡፡ እኛ አገር ለኤግዚቢሽን ብለህ ያመጣኸውን ዕቃ መሸጥ አትችልም። ለማስታወቂያ እንደ እስክሪብቶ ኮፊያ፣ በራሪ ወረቀቶች… ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ዕቃ ማስገባት አይቻልም፡፡ በውጭ አገራት ግን የፕሮሞሽን ዕቃዎች እነዚህ አይደሉም። አንድ የእምነበረድ ኩባንያ፣ የእምነበረዶቹን ቁርጥራጮች ለሳምፕል ይዞ መጥቶ፣ ለሚገዛው ሰው “እንዲህ ዓይነት ጥንካሬ አለው፤ በእንዲህ ዓይነት ቅርፅ ሊሠራ ይችላል” ብሎ ማሳየት ይችላል፡፡ በእኛ አገር ግን እንዲህ ዓይነት ቁሳቁሶችን ለሳምፕል ማስገባት አይቻልም፡፡ እስክሪብቶ፣ ቦርሳና ኮፊያ ደግሞ ታክስ ይከፈልባቸዋል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ነው፣ ቢዝነስ ካርድና በራሪ ወረቀቶች ያለ ታክስ እንዲገቡ የተፈቀደው፡፡”    
 ከመንግሥት መ/ቤቶች ጋር ትብብር
አሁን ጥሩ ነገር የማየው፣ በንግድ ሚኒስቴርና በጉምሩክ በኩል ነው የምትለው ወ/ሮ ሃይማኖት፤ ኤግዚቢሽን የሚያስገኘውን ጥቅም ስለተረዱ እየተግባባን ነው፤ ትልቁ ጥረታችንም ይኸው ነው። በፊት ክልከላ ብቻ ነበር፤ አሁን ኤግዚቢሽን ያለውን ዋጋ ስለተረዱ፣ በፊት የነበረውን መጥፎ አሠራር መለወጥ ይፈልጋሉ፤ አብረውንም እየሠሩ ናቸው፡፡” ብላለች፡፡
“ለምሳሌ ያለፈውን ኤግዚቢሽን ያካሄድነው ከኮንስትራክሽን ሚ/ር ጋር በመተባበር ነው፡፡ ብዙ ችግሮችን የተወጣነው ከእነሱ ጋር በመሥራታችን ነው፡፡ አንድ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ፣ መንግሥት ጥቅሙን ተረድቶ እውቅና እስኪሰጠው ድረስ ከፍተኛ ችግር አለው፡፡“
የአዘጋጆች ራስ ምታት  
ለኢቬንት አዘጋጆች ከፍተኛ ችግር ነው ብዬ በምሬት የምገልጸው ነገር “ፈቃድ አምጡ” የሚባለውን ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ በሚሌኒየም አዳራሽ ኤግዚቢሽን ስናዘጋጅ፣ “ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ አምጡ” እንባላለን። አንድ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ፤ በትንሹ አንድ ዓመት ይፈጃል፡፡ የእኛ ኤግዚቢሽን ጥቅምት ላይ ተካሂዶ እንዳበቃ ለሚቀጥለው ኤግዚቢሽን ፎርም ይሞላል፡፡ እነዚያ ሰዎች በተለያዩ አገሮች ኤግዚቢሽኖች ስለሚያዘጋጁና ስለሚሳተፉ በዕቅድ ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቅምት የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን ከተዘጋጀ፣ ይኼ እቅድ ውጭ ላሉት ወኪሎች ይሰራጫል፡፡ አዳራሽ ይያዛል፤ ኪራይ ይከፈላል፡፡
በዚያ አንድ ዓመት ውስጥ መቶና መቶ ሃያ ድርጅቶች ቲኬት ይቆርጣሉ፣ ሆቴል ይይዛሉ። ሊመጡ 10 ቀን ሲቀራቸው ከማዘጋጃ ቤት የሚወሰድ የስብሰባ ፈቃድ አለ፡፡ 10 ቀን ሲቀረው ማለት ዕቃዎች በአውሮፕላንና በመርከብ ተጓጉዘው፣ ለጉምሩክ ዲፖዚት ተከፍሏል። ሁሉንም ነገር ጨርሰው፣ ዕቃዎቹን አዳራሽ ውስጥ የማዘጋጀት ሥራ ብቻ ነው የሚቀራቸው፡፡ በዚያን ጊዜ የማዘጋጃ ቤት ፈቃድ አምጡ ይባላል፡፡ ትንሽ የጸጥታ ችግር ካለ፣ ማዘጋጃ ቤት “በዚህ ጊዜ ስብሰባ ማዘጋጀቱን አላምንበትም፣ ሰው መሰብሰቡ ትክክል አይደለም፤ ስለዚህ ይቅር” ይላል፡፡
“ሆኖም ፀጥታን የሚያውኩ ነገሮች ይታወቃሉ። ለአንድ ኤግዚቢሽን 10 እና 20 ሺህ ሰዎች አይመጡም፡፡ ብዙ ሰው መጣ ቢባል 6 ሺህ ነው። በየቀኑ ኤግዚቢሽኑን ለመጐብኘት አንድ ሺህ ሰዎች ይመጣሉ ብንል እንኳን፣ ይህንን ለመቆጣጠር የሚከብድ አይሆንም፡፡ 10 እና 12 አገራትን የሚወክሉ ተሳታፊዎችን ኤግዚቢሽኑ 10 ቀን ሲቀረው፤ “አገሪቱ ውስጥ ሰላም የለምና አትምጡ” ሲባል የሚያስተላልፈው መልዕክት አሉታዊ ነው። የገንዘብ ኪሳራ ያስከትላል፤ የአገሪቱንም ገጽታ ያበላሻል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ አዘጋጆቹና ከውጨ የሚመጡት ተሳታፊዎች ስለከሰሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ሰው አይኖርም፡፡” ትላለች - ከተሞክሮዋ ስታስረዳ፡፡  
“ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ዓለምአቀፍ ኤግዚቢሽን፣ በዚህ የጊዜ ሠሌዳ ውስጥ ደንብና ሕግ አክብሬ እሰራለሁ ብለህ በእርግጠኝነት መናገር አትችልም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ጊዜ ሊከለከል ይችላል፡፡” የምትለው ወ/ሮ ሃይማኖት፤”ይህ ለዘርፉ ከፍተኛ ፍራቻና ስጋት የሚፈጥር ነገር ነው፤ለእኛ ሁልጊዜ ራስ ምታት ነው፤ ስለዚህ አፋጣኝ መፍትሔ ይሻሉ፡፡” ብላለች።

Read 1569 times