Monday, 12 November 2018 00:00

ዴሞክራቶች የሌሉበት የሐገራችን ዴሞክራሲ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 በአሁኑ ሰዓት የሐገራችን ሚዲያ በሐገራችን ፖለቲካ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ስንመለከት፤ ‹‹እኛ ኢትዮጵያዊያን በምን ዓይነት ሐገርና በምን ዓይነት ማህበረሰብ ውስጥ ለመኖር እንመኛለን?›› የሚል ጥያቄ ለማንሳት ያስገድደናል፡፡ ግን ጥያቄው ቀላል ነው፡፡ መልሱም ግልጽ ነው፡፡ እኛ ለመኖር የምንመኘው፤ በበለጸገች፣ ሰላማዊ በሆነች ሐገርና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህብረተሰብ ውስጥ ነው፡፡ ብልጽግና እንዴት ይገኛል? በሰላም ሰርቶ በመኖር ነው፡፡ በሰላም ለመኖርስ ምን ያስፈልጋል? አሁንም መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ያስፈልጋል። ዴሞክራሲ ከሰላም ይገኛል፡፡ ከሰላም ደግሞ ብልጽግና ይገኛል፡፡ ብልጽግና መልሶ ዴሞክራሲን ያጠናክራል፡፡ ጠንካራ ዴሞክራሲ፤ ለጠንካራ ሰላም ዋስት ይሆናል፡፡ ለሁሉም የምንመኘው ነገር መሠረቱ፣ ዴሞክራሲ መሆኑን መናገር ይቻላል። ታዲያ ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ስንል ምን ማለታችን ነው? የዴሞክራሲ ትርጉሙ ምንድነው?
ዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ ስንል፤ ህዝቡ የራሱን ጉዳይ በራሱ ለመወሰን ይችል ዘንድ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ መድረኮች የሚያገኝበትና ያልተገደበ የመረጃ ምንጭ ኖሮት ሐሳብ - አስተያየቱን በነጻት ለመግለጽ የሚችል ህብረተሰብ ማለታችን ነው። በዚህ ዓይነት ህብረተሰብ ውስጥ ሚዲያ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሚዲያ የዴሞክራሲ ስርዓትን በማጠናከር፤ ለዴሞክራሲያዊ ውይይት መድረክ በመሆን  እና አጠቃላይ የፖለቲካ ስርዓቱን በመገምገምና በስርዓቱ ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላቸውን ኃይለኛ ተዋናዮች አሰራር በሒሳዊ መነጽር በመፈትሽ ትልቅ ግልጋሎት ያበረክታል። ስለዚህም ሚዲያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ተኪ የለሽ ሚና ይጫወታል፡፡ ሆኖም ሚዲያ ሚናውን በአግባቡ ሊወጣ የሚችለው የሚዲያ ‹‹ብዝህነትን›› የሚፈቅድ ስርዓት ሲሆን እንጂ በርካታ የሚዲያ ተቋማት በመኖራቸው አይደለም። ብዝህነታቸውም በቁጥር በመበርከት፤ በባለቤትነት መለያየትና በይዘት ፈርጀ ብዙነት ይለካል፡፡ ብዝህነት፤ አንድ ዓይነት ይዘት ካላቸው እና በተለያዩ ሰዎች ከተያዙ ብዙ ሚዲያዎች ይልቅ፤ የይዘት ወይም የአመለካከት ፈርጀ ብዙነት ያለው አንድ ሚዲያን አብልጦ የሚያይ መስፈርት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ የተሟላ ብዝህነት የቀጥር፣ የባለቤትነትና የይዘት ብዝህነት ነው፡፡
በተጨማሪም፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጠናከር ጥሩ አስተዋጽዖ ሊያደርግ የሚችል ሚዲያ፤ በህዝብ አገልጋይነት ስሜት የተጠናከረ፤ ሥነ ምግባራዊነትን የተከተለና በገለልተኝነት እሴት የሚመራ የጋዜጠኝነት ባህልን ያዳበረ ሚዲያ ነው፡፡ ሚዲያ ዴሞክራሲያዊ የክርክር መድረክ እንዲሆን ከፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ከባለሐብቶችም ተጽዕኖ ነጻ መሆን ይገባዋል። እነዚህ ነገሮች ለአንድ ሐገር ሚዲያ ጠንክሮ መገኘት መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን የሚያረጋግጥ፣ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌና መረጃ የማግኘት ነጻነትን የሚያረጋግጥ አዋጅ መኖሩ መነሻ እንጂ መጨረሻ አይደለም። ሥነ ምግባራዊነትን በተከተለና በገለልተኝነት እሴት በተቃኘ አግባብ፣ ትክክለኛ መረጃዎችንና የተለያዩ አስተያየቶችን በማቅረብ ረገድ ያለው በተግባር የሚታይ ብቃት ነው፤ ወሳኙ ነገር፡፡
የሐገራችን ሚዲያዎች በዚህ ሚዛን የሚታይባቸው ጉድለት ብዙ ነው፡፡ ይህም ጉድለት ህገ መንግስቱን በቃልና በመንፈስ አሟልቶ በመተግበርና ሙያዊ የአሰራር ስርዓትን በመገንባት የሚፈታና ሰፊ ጥረት የሚጠይቅ ችግር ነው፡፡ ለጊዜው ይዋል - ይደር የማይባለው አጣዳፊ ችግራችን የግጭት ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ሣምንት የሐገራችን ሚዲያ ግጭቶችን ለመከላከል ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ለማስረዳት፤ የታሪክ ጉዟችንን ለመቃኘት ሞክሬአለሁ፡፡ በዚህ በዛሬው ጽሑፌ፤ ሚዲያዎች ግጭትን በመከላከል፤ ግጭቶች ከተከሰቱም በኋላ ቀውሱን ለማረጋጋት በመሥራት፤ እንዲሁም በድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ሂደት ምን ዓይነት የአሰራር መርህ መከተል እንዳለባቸው ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
ሐገራችን ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ዓመታት በአንጻራዊ ሚዛን የተሻለ የሰላም ዘመን አግኝታለች፡፡ ባለፉት ዘመናት ብዝሃነትን ማክበርና ከግጭት ነጻ መሆን አቅቷት፤ ለልማት ሊውል ይችል የነበረው ሐገራዊ ሐብትና ጉልበት በግጭት እሣት ተበልቷል፡፡ አሁን የግጭት ምንጭ ሆኖ የቆየውን ብዝሃነትን ያለማክበር ችግር ለመፍታት ተሞክሯል፡፡ በ1960ዎቹ የነበረው ትውልድ፤ ከባድ የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ፤ የጊዜው ዓለም አቀፋዊና ሐገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ እንዳመለከተው፤ ለኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ያለውን ፖለቲካዊ አቋም ይዞ ታግሏል፡፡ ለ17 ዓመታት ከአምባገነነን መንግስት ጋር ተፋልሞ፤ ትግሉን በድል በማጠናቀቅ፤ ፖለቲካዊ የሐሳብ ልዩነቶች በጠብመንጃ ሳይሆን በክርክር መስተናገድ የሚችሉበትን ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አቁሟል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ያለው ወሳኙ ሥራ የተተኪው ትውልድ ነው፡፡
ተተኪው ትውልድ አሁን የተመቻቸውን ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ እንደ ዓይን ብሌን ጠብቆ፤ በዴሞክራሲያዊ የሐሳብ ትግል የጎደለውን ሞልቶ፤ የተጣመመውን አቃንቶ፤ ይህን ከዘመናት መከራ በኋላ የተገኘ ምቹ ሁኔታ ሳያበላሽ ለተሻለ እና ለላቀ ድል ለመብቃት ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ታዲያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ገና ለጋ በመሆኑ፤ የስርኣቱ ምሰሶ የሆኑ ተቋማትን የማጠናከሩ ከባድ ሥራ ገና ብዙ የሚያደክም ነው። በመሠረታዊ የዴሞክራሲ ስርዓት መርሆዎች እና እሴቶች የተገነባ ፖለቲካዊ ባህል ሊዳብር የሚችለው በተጨባጭ የህይወት ልምድ በመሆኑ ተተኪው ትውልድ ዕድሉን በግርግር ካላባከነው፤ የተሻለ ሥራ መሥራት ይችላል-  አልፎ አልፎ መደነቃቀፍ ባይቀርም፡፡
ቀደም ባለው ዘመን የግጭት ምንጭ ሆኖ የቆየውን ነገር ለይተናል፡፡ ብዝሃነትን ያለ ማክበር ችግር ወደ ግጭት እንዳይወስደን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥረናል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ማሣው ተዘጋጀቷል፡፡ ሆኖም የዴሞክራሲያዊ ስርዓት እርሻውን የማለስለስ፣ የፖለቲካዊ እሴቶች ዘርን የመምረጥ፣ የማረምና መኮትኮት ሥራ ይቀረናል፡፡ ይህ ሥራ ከባድ ሥራ ነው፡፡ እናም ይህ ሥራ በተጨባጭ የህይወት ልምድ እየተሻሻለና እየተጠናከረ የሚሄድ በመሆኑ ትዕግስትና የአስተዋይነት መንፈስን የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ምህዳር የሚንቀሳቀሰው የሐገራችን ሚዲያ፤ ትልቅ ኃላፊነት የተሸከመ ሚዲያ ነው፡፡ ከኃላፊነቶቹ ዋነኛው የዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ነቅቶ በመጠበቅ፤ እየተጠናከረ እንዲሄድ የማድረግ ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት፤ ነጻ ወይም ገለልተኛ፤ ለሙያው ሥነ ምግባሮች ትልቅ ትኩረት የሚሰጥ፤ የውይይት መድረክ በመሆን ግጭቶችን ቀድሞ መከላከል፤ ሲከሰቱም የማረጋጋት ሚና መጫወትና በድህረ ግጭት የሰላም ግንባታ ሂደት ንቁ ተሳታፊ መሆን ያስፈልጋል፡፡
ሐገራችን ተስፋ ያላት ሐገር ነች፡፡ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ምህዋር ውስጥ የምትገኝ ሐገር ነች፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉንም የሚያረካ ባይሆንም፤ ሐገሪቱን ከድህነት ለማውጣት በሚያስችል ጎዳና ላይ መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከድህነት አዘቅት ጎትቶ እያወጣ ያለ የኢኮኖሚ ዕድገት ነው፡፡ አንዳች የተስፋ ጮራ ሳታይ ዘመናትን የተጓዘችው ሐገር ከአድማስ ባሻገር የፈነጠቀ የብርሃን ጭላንጭል መመልከት ከምትችልበት ሥፍራ እንድትደርስ ያደረገ የልማት እንቅስቃሴ ነው። ይህ የተስፋ ብርሃን ይበልጥ እየደመቀ፣ ሁሉንም አካባቢ የሚሸፍን ብርሃን እንዲሆን፤ ጉዟችን በግጭት ሳይደናቀፍ በጀመርነው ጎዳና መራመድ መቀጠል ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያውያን አንጻራዊ ሰላም ማግኘት በቻሉበት የታሪክ ምዕራፍ ሁሉ ተዐምር እየሰሩ የመጡ ህዝቦች ናቸው፡፡ እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ የጀጎል ግንብ ወዘተ ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነት እስር ቤት እንድትወጣ የተደላደለ የሰላም ዘመናት ያስፈልጋታል፡፡ ስለዚህ በታሪካችን ደጋግመን ካየነው የግጭት አዙሪት ውስጥ በድንገተኛ ክስተቶች ተጠልፈን እንዳንገባ በንቃት መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ በዚህ ሂደት ሚዲያ ትልቅ ኃፊነት አለበት፡፡
ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ወደ ግጭት ከመግባት በእጅጉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌሎች ሐገራትን ወደ ግጭት ወይም ወደ ጦርነት ሊያስገቡ የሚችሉ በቂ ምክንያቶችን (ችግሮችን) ጭምር በትዕግስት የማለፍ አስተዋይነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅማችንን ማጠናከር ይገባናል፡፡ የምንገኘው በቀላሉ ቱግ የሚሉ ብዙ ችግሮች ባሉበት የአፍሪካ ቀንድ በመሆኑ፤ በነዳጅ ጉድጓድ አካባቢ እሣት ይዘን መገኘት የለብንም፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘመናት በተከሰቱ ትላልቅ ግጭቶች ሳቢያ ሰላም አጥተን ኖረናል። የሰላም እጦቱ ከድህነት እስር ቤት ጥሎናል፡፡ ድህነትም የግጭት ምንጭ መሆኑ አይቀርም፡፡ አዎ፤ ድህነት የሰላም መዋቅሮችን ያዳክማል፡፡ ህዝብን ሆደ ባሻ ያደርጋል። ስለሆነም ከግጭት ለመራቅ ድህነትን ማስወገድ፣ ድህንትን ለማስወገድ ደግሞ ሰላም እንደሚያስፈልገን ተረድተን ወደ ግጭት ከሚወስድ ጎዳና ላለመግባት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህ ሂደት ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው፡፡
ሚዲያ ግጭትን በመከላከል ረገድ፣ ግጭትን በማገረም (በማስተዳደር) እና በድህረ -ግጭት ወቅት ሰላምን መልሶ በመገንባት ሂደት (Post-Conflict reconstruction) ያለው ሚና በደንብ መታየት አለበት፡፡ ይህ ትምህርት ለኛ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ማሰብና መወያየት ይኖርብናል፡፡
ሀ). ሚዲያ ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ችግርን በማርገብ ረገድ ያለው ሚና ምንድነው?
ለ). የግጭት ክስተቶችን በመዘገብ ወይም ባለመዘገብ ረገድ በተለያዩ ሚዲያዎች ዘንድ የሚታየው ልዩነት ምን ይመስላል?
ሐ). ሚዲያ ራሱ የግጭት ምንጭ የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል?
ሚዲያ በግጭት ውስጥ ሁለት ተቃራኒ የሆኑ ቁልፍ ሚናዎችን ይጫወታል፡፡ በአንድ በኩል፤ በግጭቱ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆን የተፈጠረውን ግጭት የማባባስ ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፤ ገለልተኛ አቋም ይዞ ራሱን ከግጭቱ ተሳታፊነት በማራቅ፣ ግጭቶች ሰላማዊ እልባት የሚያገኙበትን መንገድ ያመቻቻል፡፡ ወይም ለሁከቱ መወገድ ገንቢ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሚዲያ ከሁለቱ ተቃራኒ ሚናዎች በአንዱ ተሳታፊ የሚሆንበትን ዕድል የሚወስኑ በርካታ ውስብስብ ጉዳዮች አሉ፡፡
አንድ ግጭት ሲከሰት፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት እና ፊና ለይተው የቆሙት ወገኖች ተቃራኒ የሆኑ አቋሞች ይይዛሉ፡፡ ሁሉም ወገኖች የሚዲያው ሽፋን የእነሱን ጥቅም የሚያረጋግጥ እንዲሆን ይሻሉ፡፡ አንዱ በግጭቱ የደረሰው ጉዳት ተጋንኖ እንዲቀርብ፤ ሌላው ተኳስሶ እንዲዘገብ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለዘገባ የሚሰማራው ሚዲያ ገለልተኛ ካልሆነና በሥነ ምግባር የሚመራ ካልሆነ ግጭቱን የማባባስ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሚዲያው በግጭቱ ተሳታፊ ከሆኑ ወገኖች ጋር  ያለው ግኙነት፣ ትስስር ወይም ዝምድና፤
በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት ወይም ስልጣን ከያዙ ቡድኖች ቁጥጥር ነጻ መሆን አለመሆኑም በሥራው የሚኖረውን ነጻነት ይወስነዋል፡፡
በመሆኑም፤ ግጭትን በማስወገድ፣ ሰላምን ወይም መረጋጋትን በመመለስና በመጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና የሚኖራቸው ነጻ እና ገለልተኛ የሆኑ ሚዲያዎች ናቸው። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ‹‹ደካማ ወገኖች›› ግጭቱ ስፋት ያለው ሆኖ እና ተጋንኖ እንዲቀርብ ወይም የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ ይፈልጋሉ፡፡ የእነሱ ጥያቄ ሰፊ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ። በተቃራኒው፤ መንግስትን ጨምሮ ‹‹ጠንካራ ኃይል›› ያላቸው ወገኖች፤ ግጭቱ ስፋት የሌለው ሆኖ እንዲቀርብ ይፈልጋሉ፡፡ ወይም ጨርሶ የሚዲያ ሽፋን እንዳያገኝ ይጣጣራሉ፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሚዲያዎች የሚኖራቸው ሚና ግጭትን የማስወገድ ወይም ሰላምን የመመለስ እንዲሆን፤
ሀ. የፕሬስ ነጻነትን ማረጋገጥ፤
ለ.የግጭቶችን መንስዔ (ዎች) መረዳት እና መረጃዎችን ሳይሸፍጡ ማቅረብ፤
ሐ. ገለልተኛነትን መጠበቅ፤ ሥነ ምግባራዊ፣ ሚዛናዊ መሆን እና የዘገባ ስታንዳርዶችን ተከትሎ መሥራት፤
መ. ለድምጽ አልባዎቹ (ደካሞቹ) ድምጽ መሆን፤
ሠ. ሚዛናዊ የሆነ፣ የተሰበረውን ድልድይ የሚገነባ፤ የቀደመውን መልካም ግንኙነት የሚዘክሩ ድምጾች ጉልህ ሥፍራ እንዲይዙ ማድረግ ወይም የጥላቻ ንግግሮች መድረክ አለመሆን፤ ወዘተ ያስፈልጋል፡፡
ሚዲያዎች ይህን ማድረግ ሲሳናቸው፤ ሚዛናዊ ድምፆች እየተገፉ፤ የማረጋጋት ሚና የሚኖራቸው ሚዛናዊ ድምጾች እንደ ከሃዲ ተቆጥረው የሚገፉበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የፈጠራ ወንጀሎች ወይም ጥቃቶች እየቀረቡ፣ ቀውሱ የሚባባስበት ዕድል እየሰፋ ይሄዳል። በሩዋንዳና በባልካን ሐገሮች እንደተመለከትነው፤ ሚዲያዎች ግጭትን በማባባስ ብቻ ሳይሆን ግጭትን በቀስቀስ ረገድ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴውን የሚያደራጁ እና የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎችን አይተናል፡፡ በዩጎዝላቪያም አጥፊ የብሔርተኝነት ስሜት ማራገቢያ ሆነው ሲያገልግሉ ተመልክተናል፡፡
ከእነዚህ ክስተቶች ልንወስድ የምንችለው ትምህርት፤ መንግስት ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ ትኩረት መስጠትና ህዝቡ መጻዒ ዕድሉ ብሩህ ሆኖ እንደታየው የሚያደርግ የልማት ሥራን ማጠናከር እንደሚገባው፤ እንዲሁም ጋዜጠኞች ሙያዊ አሰራር የሚጠናከርበትና የዴሞክራሲ እሴቶች ሥር የሚሰዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ነው፡፡ ምክንያቱም፤ ዴሞክራቶች በሌሉበት የዴሞክራሲ ስርዓት ሊቆም አይችልም፡፡

Read 1236 times