Monday, 12 November 2018 00:00

ቅንነት የጎደለው “ይቅርታ” ምን ይመስላል?

Written by  ኤልያስ- ከአራዳ
Rate this item
(0 votes)


   ባለፈው እሁድ በኢቢኤስ “ሰይፉ ሾው” የአንጋፋውን ድምጻዊ መሃሙድ አህመድ ዘፈኖች በማቀንቀን የሚታወቅ፣ “ትንሹ መሃሙድ” የተባለ ወጣት በእንግድነት ቀርቦ ነበር፡፡ ወጣቱ የመሃሙድን ዘፈኖች መዝፈን ብቻ ሳይሆን በአልበምም ሳያወጣው አልቀረም - ለገበያ፡፡
በ”ሰይፉ ሾው”  የቀረበበት ዋና ምክንያትም፣ አንጋፋውን ድምጻዊ ይቅርታ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ከተቀመጠበት ተነስቶም በይፋ ይቅርታ ጠየቀ፡፡
የሰው የአዕምሮና የፈጠራ ንብረት ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ለራስ ጥቅም ማዋል ከዝርፊያ የማይተናነስ  ድፍረትና ነውር ቢሆንም፣ አንዴ ለተፈጸመው ስህተት ይቅርታ መጠየቅ ትክክልም  ተገቢም ነው፡፡ ስለዚህም ወጣቱም ይቅርታ መጠየቁ፣ ሰይፉም ዕድሉን መስጠቱ ድንቅ  ነው፡፡
መጨረሻው ግን አላማረም፡፡ ሰይፉ፤ ወጣቱ አንድ የመሃሙድን ዘፈን “ለመጨረሻ ጊዜ”  በዚያው ይቅርታ በጠየቀበት መድረክ እንዲያቀነቅን ጠየቀው። (“ለመጨረሻ ጊዜ ዝረፍ” እንደማለት ነው) ወጣቱም ዘፋኝ “አላደርገውም” አላለም፡፡ ከተቀመጠበት  ተነስቶ “ቆንጂት እባክሽን” የሚለውን የመሃሙድን ዘፈን ያለ አንዳች  ሃፍረት ተጫወተው፡፡ ያ ሁሉ ይቅርታ በአንድ ጊዜ አፈር ድሜ በላ፡፡ ወይስ በቀጣዩ የ”ሰይፉ ሾው” እንደገና ይቅርታ ሊጠይቅ አስቦ ይሆን? ለእኔ ግን ቅንነት የጎደለው ይቅርታ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ኤልያስ- ከአራዳ

Read 1925 times