Monday, 12 November 2018 00:00

የማስቲሽ ሱሰኞች - በየጐዳናው! (የማንቂያ ደወል!)

Written by  ሒሮዬ ሹማቡኩሮ
Rate this item
(9 votes)

       አየሩ ሞቃት ቢሆንም ምቾት የማይነሳ ነው። የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ፣ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ነኝ፡፡ ዕድሜያቸው በግምት ከ6-7 የሚሆን ሁለት ህፃናት፣ መኪኖች በሚርመሰመሱበትና ሰዎች በሚተላለፉበት መንገድ ዳር ተቀምጠዋል። እየተጨዋወቱ ይሳሰቃሉ፡፡ ከዓለም ተነጥለው፣ የራሳቸውን ትንሽዬ ዓለም የፈጠሩ ይመስላሉ፡፡ ብቻቸውን ናቸው፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የአካባቢው ትዕይንት የተለየ ነበር፡፡ ችግረኛ ህፃናት ማስቲካ  ለመሸጥ ወዲያ ወዲህ ሲሉ አሊያም ሊስትሮዎች ደንበኞችን ሲጠባበቁ የሚታይበት ሥፍራ ነበር፡፡ በእርግጥ ይሄ ራሱ አሳዛኝ ትዕይንት ነው፡፡ በት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደ ልባቸው መቧረቅ የነበረባቸው ህፃናት፤ ጐዳና ላይ ወጥተው፣ ድህነትን ለማሸነፍ (ለመሸነፍም ጭምር!) እላይ ታች ሲሉ ወይም ሲለምኑ … ማየት ያስቆዝማል - ጥልቅ የሃዘን ስሜት ይፈጥራል፡፡
የአሁኑ ግን ከዚህኛውም ይብሳል፡፡ ሁለቱ ህፃናት በየመሃሉ፣ በሃይላንድ ላስቲክ የያዙትን ማስቲሽ ይስባሉ፡፡ በዚህ አደገኛ መርዝ ሰክረው መጦዛቸው ያስታውቃል፡፡ ባየሁት ነገር በእጅጉ ልቤ ተነካ። በጣም አዘንኩ፡፡ ግን ምን ያደርጋል? እኔን ጨምሮ ብዙዎች ምንም አያደርጉላቸውም - ከማዘንና ከንፈር ከመምጠጥ በቀር! ህፃናቱ በጐዳና ላይ ጦዘው እየነፈዙ…ዓይናችን ሥር ሲጠፉ … ዝም ብለን እናያቸዋለን፡፡
በእርግጥ ለአዲስ አበባ ድህነት ብርቅ አይደለም። ችግር ከቤት ገፍትሮ ያስወጣቸው በርካታ ህፃናት፣ ሁሌም ከጐዳና አይጠፉም፡፡ ቢያንስ ግን እንዳሁኑ ማስቲሽ በግላጭ አይስቡም ነበር፡፡
ማስቲሽም ሆነ ቤንዚን መሳብ አዲስ ክስተት አይመስለኝም፡፡ ከረዥም ዓመታት በፊት ቆሬ አካባቢ ቤንዚን የሚስቡ ወጣቶች ተበራክተው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው የታደጋቸው፡፡ ከሱስ እንዲላቀቁ ተሃድሶ እንዲያገኙ አግዟቸዋል፡፡
የአሁኑ ግን ትንሽ ይለያል፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ በማስቲሽ ሱስ የተጠመዱ ህፃናት ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በድብቅ ሳይሆን በአደባባይ የሚስቡ አንድ ፍሬ ህፃናት በዝተዋል፡፡ ህፃናት ማስቲሽ ሲስቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ባየሁ ወቅት ኢንተርኔት ገብቼ መረጃ አሰባሰብኩ፡፡ አስደንጋጭ እውነታዎችን ነው ያገኘሁት፡፡  ማስቲሽ የሳበ ሰው፤ ደስ ደስ ይለዋል-የደስታ ስሜቱ ጣራ ይነካል፤ ከፍርሃት ጋር ይፋታል፤ በስካር ይጦዛል - ይነፍዛል - ይደነዝዛል፡፡ ዕይታው ይዛባል፡፡ ጉንዳን አይቶ ዝሆን ያየ ሊመስለው ይችላል፡፡ በህልም ዓለም ይጋልባል፡፡  በዚህ ብቻ ቢያበቃ ደግ ነበር፡፡ ማስቲሽ መሳብ አደገኛ የጐንዮሽ ጉዳት አለው፡፡ ረሃብም ሆነ ጥማት የለም፡፡ በዚህም የተነሳ በሰውነት ፈሳሽ ማጣት (ድርቀት) ወይም በምግብ እጥረት ደክመው፣ ለድንገተኛ ህልፈት ይዳረጋሉ፡፡
ማስቲሽ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችንም ክፉኛ ይጐዳል፡፡ ለምሳሌ ኃይለኛ ሳል ለጉሮሮ (የመተንፈሻ አካላት) ቁስለት ይዳርጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለሳንባ ምች ያጋልጣል፡፡ የማታ ማታም ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡
ከዚህም ሌላ ጡንቻ በማሸማቀቅ፣ መራመድን ይገታል፡፡ አዕምሮንም ይጎዳል፡፡ አካላችሁና አዕምሮአችሁ አንድ ጊዜ ከተጐዳ ደግሞ፣ የተጎዳ ነው፡፡ ዳግም አያገግምም፡፡
እንግዲህ አስቡት… እንዲህ ዓይነት ጉዳት በ6 እና 7 ዓመት ህፃናት ላይ ሲደርስ! በቀላሉ ነው የሚሰበሩት - ሊቋቋሙት አይችሉም፡፡
ቆንጂት ተሾመ የተባለች ጋዜጠኛ፤ በቅርቡ ከእነዚህ የጐዳና ህፃናት መካከል  ጥቂቶቹን አነጋግራቸው ነበር - በቃለ መጠይቅ፡፡  አንደኛው የጐዳና ተዳዳሪ፤ ከ2 ዓመት በላይ (በየቀኑ) ማስቲሽ መሳቡን ያረጋገጠች ሲሆን ሁልጊዜም ፀሎቱ  ለማስቲሽ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንዳያጣ ነው፡፡ ጋዜጠኛዋ ምግብ ልትሰጠው ብትሞክርም እንደማይፈልግ ነው የነገራት፡፡ እሱ የሚፈልገው ገንዘብ ነው - ማስቲሽ የሚገዛበት፡፡ ማስቲሽ ደግሞ የምግብ ፍላጐቱን ይቆልፍለታል፡፡ ብዙዎቹም ከብርድ ይከላከለናል ብለው ያምናሉ፡፡
በነገራችን ላይ ይሄ ችግር ያለው በአዲስ አበባ ብቻ አይደለም፡፡ በሃዋሳ፤ ድሬዳዋና ሌሎች ከተሞችም በማስቲሽ ሱስ የተጠመዱ በርካታ ህፃናት አሉ፡፡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ማስቲሽ የሚስቡ ህፃናት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን እያየን ነው፡፡
እንደኔ እንደኔ፤ ህፃናቱን ከዚህ ችግር ለማላቀቅ በአፋጣኝ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ማንም እስካሁን ዘላቂና ጠንካራ እርምጃ ሲወስድ አላየንም። ሁሉም በየጐዳናው ግዙፍ ነስቶ ለሚያየው የህፃናት ሰቆቃና መከራ… ከማዘንና መቆዘም ውጭ ምንም እየሰራ አይመስለኝም፡፡   
ውድ አንባቢያነ ፡- የሌሎች አገራትን ተሞክሮ ስትመለከቱ፣ ጉዳዩ ምን ያህል አንገብጋቢ  እንደሆነ ትገነዘባላችሁ፡፡ በዛምቢያ፣ ኒጀር፣ ህንድ፣ ሜክሲኮና ፊሊፒንስ የመሳሰሉ አገራት … ማስቲሽ የሚስቡ የጐዳና ህፃናት ጉዳይ፣ ለረዥም ጊዜ አስከፊ ችግር ሆኖ ዘልቋል።
ኢንተርኔት ገብታችሁ “Street Children Sniffing glue” ብትሉ … መረጃውን እንደ ጉድ ያወርድላችኋል፡፡  በፊሊፒንስ ደግሞ ህፃናት የሚስቡት ማስቲሽ ለማግኘት ሲሉ የወንበዴ ቡድኖችን በመቀላቀል፣ ወንጀል እስከ መፈፀም ይደርሳሉ፡፡ ህፃናቱ አባል የሆኑበትን የወንበዴ ቡድን የሚወክል (ምልክት የሚሆን) ንቅሳትም ሰውነታቸው ላይ ይነቀሳሉ፡፡
በሜክሲኮ ደግሞ ህፃናቱ ማስቲሽ በመሳብ ከተለማመዱ በኋላ አደገኛ ወደሚባሉት አደንዛዥ እፆች እንደሚሸጋገሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እዚህች ጐረቤት ኬንያ፣ የ5 ዓመት ህፃናት ሳይቀሩ የማስቲሽ ሱሰኛ ሆነዋል፡፡  
ከእነዚህ አገራት አንፃር ሲታይ፣ በኢትዮጵያ የችግሩ ተጠቂ  ህፃናት ቁጥር በጣም ትንሽ ነው፡፡ ስለዚህም ችግሩን ለማስወገድ አሁኑኑ ፈጥነን መነሳት ይገባናል፡፡  
የጐዳና ህፃናትን ስናይ … ማባረርና ፊት መንሳት መፍትሔ አይደለም፡፡ ይልቅስ እንዲህ እናድርግ፡-
እነዚህ ህፃናት ከሱስ ተላቀው ወደ መደበኛ ህይወት እንዲመለሱ እናግዛቸው፤ መኖሪያ ቤት እንዲሁም የትምህርትና የሥራ ዕድል ያስፈልጋቸዋል፤
ማስቲሽን ከገበያ ማገድ ወይም ቁጥጥር ማድረግ፤
ማስቲሽ ለህፃናት የሚሸጡ ሰዎችን እየያዙ ለህግ ማቅረብ፤
ማስቲሽ መሳብ የሚያስከትለውን አደጋ በተመለከተ በሬዲዮና በቴሌቪዥን መረጃ ማሰራጨት፤ በት/ቤቶችም ማስተማር፤
ከዚህም በተጨማሪም የጐዳና ህፃናትን ቁጥር መቀነስም ያስፈልጋል፡፡ እኔ በበኩሌ፤ የጐዳና ህፃናት የሌሉባት አዲስ አበባን በእጅጉ እመኛለሁ፤ አልማለሁም፡፡ እነዚህ ሁሉ ህንፃዎች፣ ውድ አውቶሞቢሎች፣ ቡቲኮች፣ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች… በሚገኙባት መዲናችን፤ የጐዳና ህፃናት መብዛታቸው ስላቅ ነው፡፡
ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ በእጅጉ ያስፈራል፡፡ እስቲ አስቡት… የእነዚህን ህፃናት ስቃይና መከራ! የነገ ህይወታቸው ምንድነው የሚሆነው?! ወገኖቼ፤ አሁኑኑ ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ ትውልዱን እናድን!!
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ጃፓናዊቷ ሂሮዬ ሹማቡኩሮ፤ በኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በላይ የኖረች ሲሆን፤ በሙያዋ የቱሪዝም ኤክስፐርትና የቢዝነስ አማካሪ ናት፡፡ ላለፉት ዓመታት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በቱሪዝምና አገልግሎት ዘርፍ በርካታ መጣጥፎችን አቅርባለች፡፡


Read 2731 times