Monday, 12 November 2018 00:00

ሳስበው ሳስበው ደከመኝ!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

ታሪኩን ለተወካዮች ምክር ቤት የነገሩት የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ አንድ የወሎ እናት፣ ልጃቸው አንድ ቦታ  ጉዳይ ፈጽሞ እንዲመጣ ይልኩታል፡፡ ልጁ ግን ከተቀመጠበት አልተነሳም፡፡ የሚገጥመውን ድካም ያሰላስላል፡፡ በመጨረሻም  የተላከበት ቦታ አለመሄዱን ለእናቱ የነገራቸው፤ “ሳስበው ሳስበው ደከመኝ” በማለት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 54. ንዑስ አንቀፅ 4 “የምክር ቤቱ አባላት የሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ነው” ይላል፡፡ ሆኖም ዛሬም የምክር ቤቱ አባላት፤ ከዚህ ቀደም ከለመዱት ድርጅታዊ አሠራር ነፃ ወጥተው፣ በነፃነት እያሰቡ ይንቀሳቀሳሉ ለማለት  የሚያስችል ምልክት አላየንም፡፡  
ዛሬም የመንግሥት ተጠሪ ተብለው በምክር ቤቱ የተመደቡ ሰዎች፤ እንዴት ማሰብ እንዳለባቸው፣ የቱን ደግፈው ድምፅ መስጠት እንደሚኖርባቸው እየተመሩ የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ አሉ፡፡ በየቦታው ሰዎች በጅምላ ፍርድ በተደጋጋሚ ሲገደሉ፣ መንገድ እየተዘጋ፣ የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና ሰርቶ የማደር ህገ መንግስታዊ መብት ሲጣስ፣ ምክር ቤቱ፤ አስፈፃሚውን “ምን እየሆነ ነው?” ብሎ ሲጠይቅ አልሰማንም፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ወደመረጣቸው ሕዝብ ወርደው፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  ሕዝብን የማነጋገር ሃላፊነት ቢኖራቸውም፤ በችግር የተጠመዱ አካባቢ ተመራጮች ሳይቀሩ፣ ይህን ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ እናም  የምክር ቤቱ ነገር፣ ሳስበው ሳስበው ደከመኝ ያሰኛል፡፡
ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላ የመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ የተካሄደው በዚያው አመት በ1987 ቢሆንም ስለ እሱ ትውስታ ኖሮት የሚናገር ሰው እምብዛም አላገጠመኝም፡፡  በ1992 የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት “ምረጥ አዲስ አበባ” የሚል ፕሮግራም ከፍቶ፣ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች፣ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል ክርክሮች እንዲካሄዱ፣ ተቃዋሚዎችም ወደ ሕዝብ ለመውረድ እድል እንዲያገኙ ማድረጉን አስታውሳለሁ፡፡ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ ኢሠመጉ፣ የሴትና የወጣት ማኅበራት ውይይት አዘጋጆች እንደነበሩም አይዘነጋም፡፡
ይህ ጅምር በ1997 ምርጫም ቀጥሏል። ኢሕአዴግ፤ ምርጫውን “ዲሞክራሲያዊ አደርገዋለሁ” ብሎ በማወጁ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሮች ለተቃዋሚዎች በመጠኑም ቢሆን ከፈት ብለው ነበር፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሾች በርካታ የፖለቲካ ክርክሮች ተካሂደዋል። ብዙዎቹም በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ተላለፉ፡፡ የሕዝብ ግንዛቤ ከፍ አለ፡፡ ውጤቱም  በሕዝብ ድምጽ ታየ፡፡
ሁሉም ፕሮግራሞች የተካሄዱት በመንግሥት ወይም በፓርቲዎች ወጪ አልነበረም፡፡ ለቀጣዩ ምርጫ እንዲህ አይነቱ መንገድ እንዳይኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ኢሕአዴግ አመነ፡፡ ስለዚህም እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ዲሞክራሲያዊ መብቶች በሚሰበኩበት ሥፍራ ድርሽ እንዳይሉ የሚያደርግ አፋኝ ሕግ ወጣ፡፡ ሰላማዊና  ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የማሳወቅ የማስረፅ፣ የምርጫ ተግባርን የመከታተል መብትን፣ የገንዘብ አቅሙ ለሌላቸው ለኢትዮጵያ የበጐ አድራጐት ማህበራት ሰጠ፡፡ ይህ የደባ  አዋጅ ዛሬም አልተሻሻለም፡፡
ሌላው የደባ አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጅ ነው። ያልተፈፀመ ጉዳይ ማሰብን፣ መዘጋጀትን ወንጀል የሚያደርገው ይህ አዋጅ፤ የሰዎችን የሰብአዊ መብት አፈር ድሜ አብልቶ፣ የመልዕክት ልውውጣቸውን ሳይቀር፣ ለፖሊስ ክትትል አጋልጦ ይሰጣል፡፡ በአዋጅ ማስረጃ ሳይሆን ጥርጣሬም የሚያስጠይቅና የሚያሳስር ነው። እሱን ከለላ አድርጐ ሰዎችን ማንገላታትና ማሰቃየትም ያስችላል፡፡ በትራፊክ ጥፋት የተከሰሰ ባለቤቷን ጉዳይ ስትከታተል የነበረች አንዲት ሴት፤ “ለምን ባለቤቴን እንደ ልዩ ወንጀለኛ ታንገላታዋለህ!?” በማለት ፖሊሱን በመቃወሟ፤ “አንቺንም በአሸባሪነት ልጨምርሽ እችላለሁ!” ሲል እንዳስፈራራት አውግታኛለች፡፡ እንዲህ ያለው ለዜጎች ስጋት የሆነ ሕግ መኖሩ፣ምክር ቤቱን እብዛም አያሳስበውም፡፡ ይህንንም ሳስበው ሳስበው ይደክመኛል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በየአመቱ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ንግግር ያደርጋሉ። ንግግራቸውን ለምክር ቤቱ የሚያቀርቡት፣ መንግሥት በአመቱ ውስጥ ሊሰራ ያሰባቸውን ተግባራት ለማመላከት ነው፡፡ በእኔ እምነት፤ ምክር ቤቱም ያንን አድምጦ በዚያው መንገድ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡ ይሁን እንጂ ምክር ቤቱ አንድም ጊዜ ለፕሬዚዳንቱ ንግግር ዋጋ ሰጥቶ፣ ይኸ ጉዳይ ከምን ደረሰ? ብሎ ካቢኔውን ሲያፋጥጥ ወይም በቅርብ የሚመለከተውን የሚኒስትር መ/ቤት ሲጠይቅ አይታይም፡፡
ሚኒስትሮች በተያዘላቸው ጊዜ ፓርላማ ቀርበው ሪፖርት ሲያደርጉ እንጂ በምክር ቤቱ ተጠርተው እንዲያስረዱ ሲደረጉ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በአጭሩ የምክር ቤቱ ነገር፣ ሳስበው ሳስበው ደከመኝ ይሆንብኛል፡፡     

Read 1410 times