Monday, 12 November 2018 00:00

“በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ መስራት እፈልጋለሁ” ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

ከሰባት ዓመታት የአሜሪካ የስደት ህይወት በኋላ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ወደ አገራቸው የተመለሱት የህግ ባለሙያዋና ፖለቲከኛዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት ጠቁመው፤  በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ለመሥራት እንደሚሹ ተናግረዋል፡፡
ለሁለት ጊዜያት ያህል በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ለእስር የተዳረጉት ወ/ት ብርቱካን፤ በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት በሃገሪቱ የተጀመረው ፖለቲካዊ ለውጥ አነሳስቷቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“በተለያየ ደረጃ በሙያዬ በህግ እውቀት ወገኖቼን ለማገልገል ሙከራ ሣደርግ ነበር” ያሉት ወ/ት ብርቱካን፤ “አሁን በሃገሪቷ የመጣው ለውጥና ሃገሪቷ ባለችበት ሁኔታ ይህን ፍላጐቴን ለማሳካት እድሎች እንዳሉ ስለተመለከትኩኝ፣ የአቅሜን በሙያዬ፣ በልምዴ፣ በእውቀቴ ለማድረግና ለማዋጣት ነው የመጣሁት” ብለዋል፡፡
“እኔ ማተኮር የምፈልገው በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ነው” ያሉት ወ/ት ብርቱካን፤ “የትኛው ተቋም ላይ እንደምሳተፍ በቀጣይ የምወስነው ይሆናል” ብለዋል፡፡
“በአሜሪካን ሃገር ከጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በተገናኘንበት ወቅት ለለውጥ ተነሣሽነት ያላቸው መሆኑን ተረድቻለሁ፤ ለዚህም ነው ወደ ሀገር ቤት ተመልሼ፣ በዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ላይ ለመሳተፍ የወሰንኩት” ይላሉ፡፡
የህግ ባለሙያዋ፣ ፖለቲከኛዋና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዋ ወ/ት ብርቱካን፤ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ወይም ለእንባ ጠባቂ ተቋም አሊያም ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሊሾሙ እንደሚችሉ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ ተወልደው ያደጉት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያው ድግሪያቸውን አግኝተዋል፤ አሜሪካ ከሄዱ በኋላም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህዝብ አስተዳደር ሁለተኛ ድግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ “በታፈነ ማህበረሰብ ውስጥ የዳኝነት ነፃነት ምን ይመስላል” በሚል ርዕስ የመመረቂያ ጽሑፋቸውን መስራታቸው ታውቋል፡፡
ወ/ት ብርቱካን በዳኝነት፣ በአቃቤ ህግነትና በጥብቅና የሠሩ ሲሆን፤ በ1997 “ቅንጅትን” በተቀዳሚ ም/ሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡ ለሁለት አመታት ታስረው ከተለቀቁ በኋላም ከአጋሮቻቸው ጋር “አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ” ፓርቲን መስርተው የመጀመሪያዋ ሊቀመንበርም በመሆን በድጋሚ እስከታሰሩበት 2001 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡

Read 6770 times