Saturday, 03 November 2018 16:16

“በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተሸረሸረውን የህዝቡን አመኔታ ለመመለስ እሰራለሁ”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(12 votes)

 በአገሪቱ የፍትህ ነፃነትን ለማረጋገጥ እንደሚታገሉና ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲያድርበት እንደሚሰሩ አዲሷ የመጀመሪያዋ የጠቅላይ ፍ/ቤት ሴት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ገለፁ፡፡
ታዋቂዋ የሴቶች መብት ተሟጋችና የሰብአዊ መብት ጠበቃዋ ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ከሹመታቸው በኋላ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ “ይህ አሁን ለእኔ የተሰጠኝ ክብርና ልዩ እድል ለአገሬ አዲስ ምዕራፍ ነው” ብለዋል፡፡
የፍትህ ነፃነት እንዲከበር ለማድረግ እተጋለሁ ያሉት አዲሷ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት፤ ለዚህ እንቅስቃሴዬም ከመንግስቴ ሙሉ ድጋፍ እንደማገኝ አምናለሁ” ብለዋል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት በአገራችን የህግ ስርዓቱ የመንግስት የመ;; ኃይል ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህም ህዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጐታል ብለዋል፡፡
“በተሰጠኝ ሹመት በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ሴት ልጅ መድረስ የምትችለው እዚህ ጋ ነው ተብሎ የተከለለው ድንበር ተሰብሯል” ያሉት ወ/ሮ መአዛ፤ አሁን “ሴት ልጆቼ መሆን የሚፈልጉትንና የሚመኙትን ለመሆን ይችላሉ፤ ይህ ለአገሬ አዲስ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ዜጐች ፍትህ እንዲያገኙ አበክሬ እሰራለሁ” ያሉት የ55 ዓመቷ የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት፤ “በፍ/ቤቶች ላይ የተሸረሸረው የህዝብ አመኔታ መመለስ እንዳለበት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቀረቡትን የወ/ሮ መአዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንትነት ሹመት ያፀደቀ ሲሆን አቶ ሰለሞን አረዳን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጐ መርጧቸዋል፡፡  
የፍትህ ስርዓቱ በመጓደሉ ምክንያት ህዝቡ ሲጉላላና ሲሰቃይ ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  ይህንን የፍትህ ስርዓት ለማሻሻልና ህዝቡ የናፈቀውን ፍትህ እንዲያገኝ ለማድረግ የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀው፡፡ የወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ሹመትም የዚሁ ሂደት አካል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በ1956 ዓ.ም ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ውስጥ ተወልደው ያደጉት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፤  የህግ ባለሙያና ስመ-ጥር የሴቶች መብት አቀንቃኝ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስራችና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ወ/ሮ መአዛ፤ ከ1981 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ድረስ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በመሆን ሰርተዋል፡፡ በ1985 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ኮሚሽን የህግ አማካሪ ነበሩ፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ያገኙት ወ/ሮ መአዛ፤ ከአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ በአለም አቀፍ ግንኙነት የማስተርስ ድግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን የመመረቂያ ጥናታቸውም ሴቶች በህዝበ ውሣኔ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በጥልቀት የሚፈትሽ ነው፡፡
የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን በ1987 ዓ.ም የመሰረቱት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፤ ማህበሩን በከፍተኛ የአመራር ብቃት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። በጠንካራና ከፍተኛ ራዕይ በሰነቁ እንስቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተቋቋመው እናት ባንክ መሥራችና የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም ተሹመው ላለፉት 3 ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ ቆይተው ሰሞኑን ለምክር ቤቱ መልቀቂያቸውን ባቀረቡት በአቶ ዳኜ መላኩ ምትክ የተሾሙት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፤ በርካታ አለም አቀፍ ሽልማቶችንም አግኝተዋል፡፡
በ2003 ዓ.ም የአንገር ፕሮጀክት የአፍሪካ ሴቶች ሽልማት አሸናፊ የነበሩት ወ/ሮ መአዛ፤  ከሁለት ዓመት በኋላ የኖቤል የሰላም ሽልማት እጩ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ በተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ኢኮኖሚክስ ኮሚሽን በኃላፊነት ደረጃ ተመድበው የሰሩት እኚህ ሴት፤ ዕድሜ ዘመናቸውን ለኢትዮጵያ ሴቶች መብት መከበር ያለመታከት ሰርተዋል፡፡
የስራ መልቀቂያቸውን ያቀረቡት የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩም በጡረታ በክብሩ እንደሚሸኙ ታውቋል። በተያያዘም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበትና የስራ መልቀቂያቸውን ባቀረቡት በአቶ ፀጋዬ አስማማው ምትክ አቶ ሰለሞን አረዳ ተሹመዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ድግሪ፣ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በአለማቀፍ የኢኮኖሚ ህግ ማስተርስ እንዲሁም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በህዝብ አስተዳደር ማስተርስና በተጨማሪም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በህግ የማስተርስ ድግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሰለሞን አረዳ፤ በከፍተኛው ፍ/ቤት በዳኝነትና በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ “ዘ ሔግ” በተሰኘው አለም አቀፍ የግልግል ፍርድ ቤት በገላጋይ ዳኝነት የሰሩ ሲሆን በታላላቅ አለም አቀፋዊ ድርጅቶች ለበርካታ ዓመታት በመስራትም ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፡፡  

Read 10601 times