Saturday, 03 November 2018 16:15

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(3 votes)

  “ወጣትነት ፍላጎት ነው፡፡ ወጣትነት የለውጥ ጊዜ ነው፡፡ ሁሌም እንደቸኮልክ፣ ሁሌም እንደሮጥክ ነው፡፡ ወጣትነት ኑሮ ያላጠላበት ሳቅ ነው፡፡ ወጣትነት ስሜት ነው፡፡ ራስንም ሌላውንም የሚያቃጥል … የጋመ ፍም፡፡”
        

    አንድ አስተዋይ ወጣት ገጠመኙን አጫወተኝ፡፡ አንድ ቀን፣ ምሽት ላይ፣ አሳቻ ቦታ ያሸመቁ ወሮበሎች ንብረቱን ዘረፉት፡፡ … ላፕቶፑን፣ የኪስ ቦርሳውን፣ ሞባይሉንና የመሳሰሉትን፡፡ የደረሰበትን ጉዳት በመዘርዘር ለፖሊስ አመለከተ፡፡ ቃሉን የተቀበለው ብዙ ልምድ ያለው ፖሊስ …
“ሰዎቹን ብታያቸው ትለያቸዋለህ?” በማለት ጠየቀው፡፡
“አዎን” መለሰ፡፡
 ፖሊሱም፤ “እኛ ስራችንን እንሰራለን፡፡ ምናልባት በአጋጣሚ አንዱን ወይም ሁለቱን ዘራፊዎች ካየህ ለኛ ደውለህ አስታውቀን” አለውና ስልክ ቁጥር ሰጠው። ጎረምሳው ከጥቂት ወራት በኋላ መካኒሳ አካባቢ ሲዘዋወር አንደኛውን ሌባ አየው፡፡ ወዲያውም በተሰጠው ስልክ ጉዳዩን ለያዘው ፖሊስ ደወለለት። ፖሊሱም፤ “በአይነ ቁራኛ ጠብቀው፡፡ እዛው አካባቢ የተሰማሩ ሲቪል የለበሱ ተከታታዮች (Plain cloth detectives) ስለሚገኙ ስልክህን እሰጣቸውና ይደውሉልሃል” አለው፡፡ ሌባውን ባይነ ቁራኛ እየጠበቀው ስልኩ ጮኸ፡፡
“አቤት”
“ተከታታይ ፖሊስ ነኝ፡፡ የት ነው ያለኸው?”
“ሳሪስ አካባቢ ነኝ”
“መካኒሳ ነህ ተብሎ ነው የተገነረኝ፡፡ ለምን ወደ ሳሪስ ሄድክ?”
“ዘራፊው ወደ ሳሪስ በሚሄድ ታክሲ ስለተሳፈረ፣ ተከትዬው መጥቼ ነው” አለው ውሸቱን፡፡
በዚህ ተለያዩ፡፡ … ግን ለምን ዋሸ?
***
“ሰው የተፈጠረው ለሌላ ሰው ነው” ሲባል ሌላውም ሰው የተፈጠረው ለሱ ነው እንደ ማለት ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ከሌሉ፣ ሰው ብቻውን ‹ሰው› አይባልም። ፍቅር፣ ደስታ፣ ፅናት፣ መከራ፣ ችግርና ስቃይ የሚፈጥሩለት ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ እሱም ለነሱ ያው ነው፡፡ ቤተሰቦቻችን፣ ጎረቤቶቻችን፣ የመንደር ሰዎች፣ የስራ ባልደረቦች፣ በመንገድና በትራንስፖርት ላይ፣ በየት/ቤታችን፣ በየቴአትር ቤቱ፣ በሲኒማ አዳራሾች፣ በየቤተ እምነቱና ኤግዚቢሽን ማዕከላት የምናገኛቸውና የሚያገኙን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እዚህ ትስስሮሽ፣ እዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ባህሪ ይቀረፃል፡፡ በተለይ ደግሞ የወጣትነት፡፡ … በዚህ መጨናነቅና ፍትጊያ ውስጥ፣ በዚህ የኑሮ ጎዳና ላይ ጠባችንና ፍቅራችን ሲበራና ሲጠፋ ይውላል … በየቀኑ፡፡ በዚህ አንድነታችንና ተመሳሳይነታችን ውስጥ የአስተሳሰባችን ልዩነት፣ የዕውቀትና የግንዛቤያችን ልሂቅነትና ደቂቅነት ብልጭ፣ ድርግም ይልብናል … በየቀኑ፡፡ እዚህ ትርምስ ውስጥ ባህል፣ ፖለቲካ፣ እምነት፣ ጥበብ፣ ሳይንስና ፍልስፍና ይወለዳሉ፡፡ በዚህ ማህበረ ህላዌ ሞትና ህይወት ተመጥኖ፣ ተፈጭቶና ተቦክቶ በኑሮ ምጣድ ላይ ‹ሰው› ይጋገራል፡፡ … ለግላጋና እሸት፣ ብስልና ጣፋጭ፣ ጥሬና መራራ ሆኖ!!
ስናውቅና ሲገባን፣ አንዳችን ያለ አንዳችን መኖር እንደማንችል ስንረዳ፣ ደስታና ሃዘናችንን እየተጋራን፣ ችግራችንን በመተጋገዝ ተቋቁመን፣ የነገን ሰው እንቀርፃለን፡፡ ካልገባንና ካላወቅን ከትናንት ቤተሰቦቻችን መልካምነትን ለቅመን፣ ዛሬ ላይ ተክለን ለነገ ካላቆየን ግን … ዛሬ ላይ አብበን ዛሬ ላይ የረገፍን አበቦች፣ ከአቤልና ከቃየል የማንሻል የራስ ወዳድነት ተረቶች፤ የተፈጥሮ ፀጋዎች ሳንሆን ስህተቶቿ እንሆናለን፡፡
ወዳጄ፡- እየኖሩ የሚያኖሩን፣ እየኖሩ የማያኖሩን፣ ሳይኖሩ የሚያኖሩንና ሳይኖሩም የማያኖሩን ሰዎችና ሃሳቦች አሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በመሃከላችን ወይም ራቅ ባሉ ቦታዎች እየኖሩ ያኖሩናል፡፡ ጥሩ፣ ጥሩ መጻህፍት፣ ድራማ፣ ቴአትር፣ ሙዚቃ፣ ስዕል ወይም ቅርፃ ቅርፅ እየደረሱ፣ እየተጠበቡ ያነቁናል፡፡ ሃሳባቸውንና ልምዳቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች በማካፈል፣ ለስልጣኔ እንድናዋጣ ይመክሩናል፤ ያዝናኑናል፡፡ የህይወትን ብሩህ ገፅ (The sunny side of life) እያጎሉ ጭለማዋን ያርቁልናል፡፡ በችግሮቻችን ጊዜ የደረሱልን ምርጥ የዓለም አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ለጋሾችና አጋሮቻቸው ሁሉ “እየኖሩ የሚያኖሩ” ሰብዓውያን ናቸው፡፡
በመሃከላችን እያሉ፣ የጨቋኞች መሳሪያ ሆነው፣ በአስተሳሰብና በጥቅም ጡጦ ያደጉ፣ የዓለም አቀፋዊነትና የስልጣኔን ጥቅም ማገናዘብ ያቃታቸው፣ ከደሃ ህዝብና ሃገር እየሰረቁ የሚያሰርቁ፣ ፍትህን እየረገጡ የሚያስረግጡ፤ እንኳን ለሳይንስና ለጥበብ ሊያዋጡ፣ እንኳን ለዕድገትና ለብልፅግና ሊቆሙ ይቅርና በተቃራኒው ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዴሞክራሲና ለአገር አንድነት የሚታገሉ የለውጥ ኃይሎችን ለማደናቀፍ የሚተጉ “ኖረው የማያኖሩ” ጥቂቶች አይደሉም፡፡
መልካም ሃሳባቸውን፣ የፈጠራ ስራዎቸውን፣ ንብረታቸውንና ቅርሳቸውን ትተውልን፣ ዓለምን በጥበብ አስጊጠው ያለፉ፣ ለወጣቶቻችን አርአያ ሆነው “ሳይኖሩ የሚያኖሩንም” ብዙ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ አሉ፡፡ ከህይወት ከተፋቱ በኋላም ዕኩይ አስተሳሰባቸውና ፅሁፎቻቸው ስልጣኔን እየተገዳደረ፣ ዘመናዊነትን በማንኳሰስ፣ ለብዙ ኢ-ሰብዓዊ ችግሮች ምክንያት የሆነ፣ የዘረኝነት በሽታ፣ ዋልጌነት፣ ስራ አጥነትና አድሎአዊነት እንዲስፋፋ ያደረገ፣ ወጣትነትን ለማምከን፣ የዕውቀት ዋጋ እንዲቀንስ የተጋ፡፡ … “ሳይኖር እንኳ ያላስኖረ” የሙት መንፈስ!!
ወዳጄ፡- ወጣትነትን ካነሳን አይቀር፣ ወጣትነት ‹መከነ› ማለት ዕድሜ ከሰረ፣ ብርሃን ደበዘዘ፣ ዕንቡጥ ረገፈ፣ አበባ ሳያብብ፣ ፍሬ ሳይዘረዝር ቀረ እንደ ማለት ይመስላል፡፡ … ባካናነት!! ምክንያቱም ወጣትነት ጉጉት ነው፡፡ ወጣት ስትሆን ታላላቆችህን ለመምሰል ትጥራለህ፡፡ አክተር፣ ኳስ ተጫዋች፣ ዘፋኝ፣ ሰዓሊ፣ ገጣሚና ደራሲ፣ አባት ወይም እናት፣ ፕሬዚዳንት ወይም ጠ/ሚኒስቴር ሆነህ አገር መምራት ያምርሃል። … ወጣትነት ፍላጎት ነው፡፡ ወጣትነት የለውጥ ጊዜ ነው፡፡ ሁሌም እንደቸኮልክ፣ ሁሌም እንደሮጥክ ነው፡፡ ወጣትነት ኑሮ ያላጠላበት ሳቅ ነው፡፡ ወጣትነት ስሜት ነው፡፡ ራስንም ሌላውንም የሚያቃጥል … የጋመ ፍም፡፡
ፍራንሲስ ቤከን፤ “ወጣቶች በዳኝነት ወንበር ከሚቀመጡ ለፈጠራ ስራ ቢያመቻቿቸው ይሻላል፣ ጊዜ ወስደው ነገሮችን ከመመርመር ይልቅ ለድርጊትና ለአፈፃፀም ይጣደፋሉ፣ ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተሻለ ለአዳዲስና ለመጪዎቹ ይጓጓሉ፡፡ በአንድ ስራ ላይ ረግቶ መቆየት ይሰለቻቸዋል፤ የመሰላቸውን ለማድረግ አጋጣሚ ካገኙ ወደ ኋላ አይመለሱም፡፡ መጪውን አደጋ ቆም ብለው ለማሰብ አይጨነቁም። ጠና ያሉ ሰዎች ግን መከራከርና መቃወም ይቀናቸዋል፣ የመጣው ይምጣ ብለው አይወስኑትም፣ ስህተቶቻቸውን ለማረም ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ ስራቸው አካባቢ ሆነው መቆየታቸውን እንጂ ውጤታማ መሆን አለመሆናቸውን ልብ አይሉም…” በማለት ፅፏል፡፡
ወዳጄ፡- አገር በወጣት ይደምቃል፡፡ ወጣትነት ህብረ ቀለም ነው፡፡ ፋሽን የሚያምረው በወጣት ዕድሜ፣ ስሜትና ሰውነት ነው፡፡ ስታይልና ፓሽን (style and passion) ግን ከብስለት፣ ከልዩነት፣ ከውስጣዊ ፍላጎትና ከችሎታ ጋር የሚቆራኙበት መንገዶች ናቸው።
ወዳጄ፡- “ወጣትነት በጥሩ ቃላት የሚከፈትና የሚዘጋ የባዶ ሃሳብ ጎተራ ነው” ብለው ለሚያስቡ ጊዜው አልፏል፡፡ እያንዳንዱ ወጣት የራሱ ህልም አለው፡፡ የጅምላ ፍረጃ፤ “የወሬ ተራራ በትንፋሽ ይናዳል!” መባሉን ላልሰሙ ብቻ ነው፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፤ ህይወቱን ለማዳን ሲል ንብረቱ የተዘረፈበት ጉብል፣ ከመርማሪው ፖሊስ በተነገረው መሰረት፣ ሌባውን በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለ ሳለ፣ ከተከታታዮቹ ስልክ ተደውሎለት፣ ውሸቱን ወደ ሳሪስ መሄዱን እንደነገራቸው አውርተናል። የዋሸው በመደናገጡና ያልጠበቀው ነገር በመከሰቱ ነበር። ምክንያቱም በቅርብ ርቀት ሆኖ ስልክ የደወለለት ‹ተከታታይ ፖሊስ›፤ በዓይነ ቁራኛ ሲጠብቀው የነበረ ሌባ ነው፡፡  
ሩቅ አሳቢ ሆነህ
ስታንጋጥጥ ወደ ሰማይ፣
አደናቅፎ እንዳይጥልህ
አጠገብህ ያለ ድንጋይ፣
ቀጥ ብለህ ለመራመድ
ዓይንህ ወደታች ይውረድ! …. መባሉ ያለ ነገር አይደለም፡፡
“Two souls do dwell, alas! …
Within my breast” (Faust)
ሠላም !!!

Read 2729 times