Saturday, 19 May 2012 10:42

አረረም መረረም እኛ ነን ኑሮዋን የምንኖራት!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(0 votes)

እነ ቦብ ጌልዶፍ የማያውቁት አንዳንድ ነገር አለ

ባለፈው  ሳምንት “ፖለቲካ  በፈገግታ” ለምን ተዘለለ የሚል ስጋት የገባው አንድ የጋዜጣውና የዓምዱ ደንበኛ” “ፀሃፊው ምን ገጥሞት ነው?” ሲል መጨነቁን ሰምቼ ትንሽ ሆዴ ቢባባም  ባሳየኝ አጋርነት ግን ረክቼአለሁ፡፡ ለነገሩ በየቤቱ እንዲሁ አጋርነታቸውን የሚገልጡልኝ ብዙዎች እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ - ድምፃቸውን ባያሰሙም ማለት ነው (ኢህአዴግ ብቻ ነው እንዴ አጋር ያለው?)  ለማንኛውም ለተጨነቁልኝም ላልተጨነቁልኝም ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳቸው - Thank you so much! (የፈረንጅ አፉን ጨርሶ እንዳልረሳው ብዬ እኮ ነው)

አንዱ ወዳጄ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ዓምዱን ቢያጣው “አንተ አሰሩት ብዬ ሳስብ ነበር እኮ” አይለኝ መሰላችሁ? ቆይ ለምንድነው የምታሰረው? (የሻዕቢያ ተላላኪ አይደለሁ!) ይልቅስ ይሄ ወዳጄ የተናገረው ነገር የሚያሳስር ነበር - ያለስም ስም በመስጠት (ያለስሜ ስም እየሰጡኝ ያለው ማን ነበር?) ለማን? ለአውራው ፓርቲያችን ለኢህአዴግ ነዋ! ተቃዋሚዎችማ ይታሰራሉ እንጂ አያስሩም እኮ - አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማለቴ ነው፡፡ ተጨባጭ ሁኔታው ሲለወጥ ግን ሊያስሩ ይችላሉ (ማነህ ባለተራ ያለው ማን ነበር?)

ወደቁም ነገሩ ስንመለስ --- ወዳጄ አሰሩት ሲል መስጋቱን ያጣጣልኩበት ውለታውን “ኢግኖር” ለማድረግ አስቤና አቅጄ አይደለም፡፡ ቅዱስ ስጋት ባለመሆኑ ብቻ ነው፡፡ አያችሁ በኢህአዴግ ዘመን ሰው ተናገረ ወይም ፃፈ አሊያም ተቸ ተብሎ ወህኒ ቤት አይወረወርም፡፡ አንዳንዴ ግን ሊወረወር ይችላል - በስህተት! (ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት እንደሚባለው!) ባለፈው የታላቁ ሩጫ ውድድር ላይ የንባብ መፈክር ይዘው የወጡ ወጣቶች በስህተት እንደታሰሩት ማለት ነው (በስህተት አይደለም እንዴ?) ይኸውላችሁ በአሁኑ ዘመን ሰው አወራ ተብሎ የማይታሰረው ኢህአዴግ ወይም ልማታዊ መንግስታችን የመላዕክት ስብስብ ስለሆነ አይደለም (ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት የመላዕክት ስብስብ አይደለም ማለታቸውን ልብ ይሉዋል) ኢህአዴግ ለዓመታት በዱር በገደሉ ከታገለባቸው ዓላማዎች አንዱ ሃሳብን ሰሙኝ አልሰሙኝ ሳይሉ እንደፈለጉ የመግለፅ ነፃነትን ለማስከበር በመሆኑ ነው (ኢህአዴግ ጆሮ ጠቢ አለው እንዴ?) እናም ወዳጄን አይዞህ አትፍራ” ይታሰራል ብለህም አትስጋ ልለው እፈልጋለሁ፡፡ ለነገሩ አውራው ፓርቲያችን ልሰርም ቢል የሚችል አይመስለኝም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ሃባ ጊዜ የለውማ! ያልማ ወይስ ሃሜተኞችን ይሰር? (ኢህአዴግ እኮ በሃሜት የሚፈታ ድርጅት አይደለም!)

አንድ ነገር ልንገራችሁ  የፖለቲካ ሃሜት ያሳስራል ከተባለም ብቻዬን አይደለሁም - በሺዎች የሚቆጠሩ አጋሮች አሉኝ (ማን ሞኝ አለ ተደራጀሁዋ !) አያድርገውና ከአንባቢ ጋር ከታሰርኩ ሻርኩኝ ማለት ነው፡፡ ወህኒ ቤት ቁጭ ብለን አውራ ፓርቲውን እንደጉድ እንቦጭቀዋለን፡፡ የሃሜት ሱስ እኮ አይጣል ነው! አንድ የቀድሞ መንግስት ጄነራል ምን አሉኝ መሰላችሁ? “ኢህአዴግ የፈለግኸውን ያህል ብትጮህ ደንታ የለውም” ለምን ተናገርክ ብሎ አያስርህም”  “እና  ምንድነው የሚያደርገኝ?” አልኩዋቸው  “ምንም!” አሉኝ (ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ይተውሃል ማለታቸው ነው)  እናም በአጋርነት ከጎኔ ለቆመው ውድ አንባቢዬ ላስታውሰው የምፈልገው” ውዱ ፓርቲያችን ሰው ተናገረ ብሎ የማሰር አባዜ እንደሌለበት ነው፡፡ በሰበብ አስባቡ ማሰር እኮ የአምባገነኖች እንጂ የዲሞክራቶችና በህዝብ የተመረጡ መንግስታት ተግባር አይደለም፡፡

በነገራችሁ ላይ ባለፈው ሳምንት በመዲናችን በተካሄደው “ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም” ላይ ስለአፍሪካ መንግስታት በተደጋጋሚ ሲባል የነበረው ነገር ግርም ብሎኛል፡፡ እኔ የምለው ግን እኛ የማናውቃት አፍሪካ አለች እንዴ? (ለፎረሙ ብቻ የተፈጠረች!)  ለምን መሰላችሁ? አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የአፍሪካ መንግስታት በህዝብ የተመረጡ ናቸው ሲባል ሰምቼ እኮ ነው! የ87 ዓመቱ የዚምቡዋቤው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እንዳይሰሙና ቀውጢ እንዳይፈጠር፡፡ እሳቸው ውሸት አይወዱማ! ዘንድሮ ምርጫ አጭበርብረዋል ተብለው  የታሙትና “አላህ ከፈቀደልኝ ቢሊዮን ዓመት ብገዛስ?” ያሉት የጋምቢያው ፕሬዚዳንትም ማጉረምረማቸው አይቀርም፡፡ እሳቸውም ውሸት አይመቻቸውም! (አምባገነን ሁሉ ይዋሻል ያለው ማን ነው?) ምናልባት ምርጫ ማጭበርበርና በህዝብ መመረጥ አንድ ነው ከተባለ” በእርግጥም የአፍሪካ መንግስታት በህዝብ የተመረጡ ናቸው ቢባል ያስኬዳል፡፡ በነገራችን ላይ ያሁኑ አጀንዳ ውዱ ፓርቲያችንን  አይመለከተውም፡፡ ምናልባት ለ30 እና 40 ዓመታት በስልጣን ላይ መቆየት እፈልጋለሁ ያለውን ነገር አጥብቆ መጠየቅ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ በተረፈ ግን ---- (በድሮ በሬ ያረሰ የለም)

በነገራችን  ላይ  በዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ከበርካታ ታዋቂ የአፍሪካ መንግስታትና ከዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ባለቤቶችና መሪዎች ጋር የተገኙት ጠ/ሚኒስትራችን በሰጡት አስደማሚ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማብራሪያ ተደምሜአለሁ፡፡ ምንም እንኩዋን አንዳንዶች” ፓርላማ ያሉ እየመሰላቸው ቁጣ ቁጣ ብሎዋቸው ነበር ቢሉም፡፡ ለነገሩ የድሃ አገር መሪ ያልተቆጣ ማን ሊቆጣ ነው! ሳይበዛ ትንሽ ትንሽ ቁጣማ አስፈላጊ ነው ፡፡ በተለይ እንደበቀደሙ በኒዮሊበራሎች በተሞላ ፎረም!  እኔ የምለው --- ኢቴቪ በፎረሙ ላይ ያሳየውን ትጋት አላደነቃችሁለትም? እነቦብ ጌልዶፍን የመሳሰሉ ዝነኞችን ኢንተርቪው በማድረግ ያሰባሰበው ምስክርነት በዌብ ሳይት ላይ ቢለቀቅ ድንቅ የአገር ገፅታ ግንባታ ይወጣዋል፡፡ ግን ሚዛናዊ እንዲሆንና “አገሪቱ የራሱዋ ዜጎች የላትም እንዴ?” የሚል ጥያቄ እንዳያስነሳ እኛንም ኢንተርቪው አድርጎ ቢቀላቅለን አይከፋም፡፡ ለሌላ እኮ አይደለም! መረጃውን የበለጠ ተዓማኒ ለማድረግ ነው፡፡ ለነገሩ ከቦብ ጌልዶፍ ይልቅ የአገራችንን እውነት የምናውቀው እኛ ነን፡፡ እስቲ አንድ ጥያቄ ለኢቴቪ - ከእኛና ከቦብ ጌልዶፍ ማንን ነው የሚያምነው? በተለይ የኑሮና የኢኮኖሚውን ነገር በተመለከተ እኛን ቢያምነን ነው የሚሻለው - ነዋሪዎቹን! አረረም መረረም እኮ እኛ ነን ኑሮዋን የምንኖራት፡፡ በእኛ ኑሮ ጌልዶፍን በጥያቄ ማፋጠጥ “ፌር” አይደለም (ኢቲቪዎችን ማለቴ ነው!) እኔ እስከማውቀው ድረስ ቦብ ጌልዶፍ  አገር ጎብኚ እንጂ የዚህ አገር ነዋሪ አይደለም  (የክብር ዜግነት ተሰጠው እንዴ?)  ለነገሩ ቢሰጠውም ይገባዋል!  ረሃባችን ጊዜ ደርሶልናል!

እውነቴን ነው የምላችሁ --- ኢቴቪ ልብ ካለው እኛን ነው መጠየቅ ያለበት (እኛን ነው ማየት ያለው ማን ነበር?) እናስታጥቀው ነበር - እውነት እውነቱን፡፡ ለምሳሌ የመንገድ ስራው እንዴት ነው ሲለን እንደነቦብ ጌልዶፍ “ወርቅ ነው” እንለዋለን፡፡ ልማቱስ? እሱም ወርቅ ነው! ግን ብዙ ይቀራል፡፡ ለነገሩ ልማት እኮ አያልቅም! የመሬቱ ልማት--- የኢንዱስትሪው ልማት--- የጤናው ልማት--- የዲሞክራሲው ልማት--- እንዴ ዋናውን ጉዳይ ዘንግቼው! የሰው ልማትስ? (ዋናው የቸገረን እኮ እሱ ነው! )

እንግዲህ ከጌልዶፍ ጋ የምንለያየው ከዚህ በሁዋላ ነው፡፡ እሱ የማያውቀው እኛ ብቻ የምናውቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ ሙጭጭ አድርጎ ስለያዘን የኑሮ ውድነት እናነሳለን (የኢኮኖሚ እድገት ጣጣ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ቢነግሩንም) ስለሸቀጦች ዋጋ መናርና እጥረት ስሞታ እናቀርባለን (የስርጭት እንጂ የአቅርቦት ችግር እንደሌለ ብንሰማም) የመኖርያ ቤት ችግርም መጥቀሳችን አይቀርም (ኮንዶሞኒየሞች እየተገነቡ መሆናቸውን ብናውቅም ካልገባንበት ስለማናምን!)  የስልጣን መንበሩን ለተቆናጠጡ ወገኖች ቅንጦት የሚመስላቸው ሌሎች ጥያቄዎችም አሉን - የፖለቲካ ! ለምሳሌ የምህዳር መጥበብ” የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት” የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፍ  ወዘተ--- (ኢህአዴግ ጉዱ ፈላ በሉኛ!) ለመሆኑ 20 ዓመት ሙሉ የማንን ጎፈሬ ሲያበጥር ነበር? (ልማቱ ፋታ ነሳዋ!)

በነገራችን ላይ እኛ የምንሰጠው ኢንተርቪው ለገፅ ግንባታ እንደማይሆን ኢቴቪን ልጠቁመው እወዳለሁ፡፡ የእኛ የሚሆነው ለጠቅላላ እውቀት ወይም ለታሪክ ዘገባ አሊያም የዓለም ድንቃድንቆችን ለሚመዘግበው ኩባንያ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን ስለኢትዮáያ እውነቱን ማወቅ የሚፈልግ ካለ ኢትዮáያውያንን ይጠይቅ - እኛን ማለት ነው (ጌልዶፍ እኮ የስኩዋርና የዘይት እጥረት እንዳለ አያውቅም)

አሁን ደግሞ ከፎረሙ ወጣ ብለን ሌሎች ጉዳዮችን እንቃኝ፡፡ እኔ የምለው --- “መደራጀት ማለት ምን ማለት ነው?” ጠ/ሚኒስትሩ መብትን ለማስከበር መደራጀት ወሳኝ ነው ካሉ ቀን ጀምሮ “ በሚያስገርም ሁኔታ የበታች ሹማምንቶች ሳይቀሩ ለሁሉም ችግር “መፍትሄው መደራጀት ነው!” እያሉ ስላስቸገሩ እኮ ነው፡፡ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ በሰማሁት ዜና” በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት ብቸኛው መስፈርት ስራ ፈላጊነት ነው ያሉት አንድ የመንግስት ሃላፊ” ከአንድ ሰው ጀምሮ እስከፈለገው ድረስ መደራጀት ይቻላል ብለዋል (አንድ ሰው ብቻውን ይደራጃል እንዴ?)

ሰሞኑን በቲቪ በሸቀጦች አቅርቦትና ስርጭት ችግር ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይትም” አንዱ ሃላፊ የሸቀጦች ስርጭት ችግርን ለመፍታት ህብረተሰቡ መደራጀት እንዳለበት አሳስበዋል (አንድም ሰው ቢሆን?) ሃላፊው በማከልም የተበታተነ ህዝብ ትርጉም ያለው ስራ ወይም ለውጥ አያመጣም ብለዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ እስከዛሬ ድረስ አንድ ሰው ብቻውን ይደራጃል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር (ለካስ የማይቻል ነገር የለም!) ይሄ ለብቻ የመደራጀት ነገር በ97ቱ የምርጫ ግርግር ወቅት የሰማሁትን ቀልድ አስታወሰኝ፡፡ ያኔ እንግዲህ ከተማዋ ቀውጢ ሆና ስለነበር  ሰብሰብ ብሎ መቆም ወይም መንቀሳቀስ አይቻልም ነበር (መደራጀት ግን እኔጃ?) እናላችሁ ሰብሰብ ብለው የሚሄዱ ሰዎች  ከተገኙ “ተበተኑ!” ይባሉ ነበር፡፡ እናም አንዱ ፀጥታ አስከባሪ ወዲህ ወዲያ እያለ ሲቃኝ”  አንድ ጎረምሳ ዛፍ ስር ቆሞ ይመለከታል፡፡ ቢጠብቀው ቢጠብቀው አይነቃነቅም፡፡ ይሄኔ ወደ ጎረምሳው ጠጋ አለና” “ተበተን!” አለው (ይሞታል ወይ ታዲያ ያለው ማን ነበር?)  የትኛው መፅሃፍ ላይ እንዳነበብኩት ትዝ ባይለኝም” አንዱ ወታደር በፃፈው የጦር ሜዳ ውሎ ማስታወሻው ላይ በዛ ብለው የመሸጉትን የጠላት ወታደሮች” በጥንቃቄ ጠጋ ብዬ “ከበብኩዋቸው”ሲል ፅፎዋል፡፡ ይታያችሁ --- አንድ ሰው ብዙ ሰዎችን ሲከብ!  (በነገራችሁ ላይ መበተን መክበብና መደራጀት በሚሉት ፅንሰሃሳቦች ዙሪያ የሚዘጋጅ ሴሚናር ካለ እንዳትረሱኝ አደራ እላችሁዋለሁ- ባይሆን ወሮታውን ጠይቁኝ )

ከመሰነባበታችን በፊት ሶስት የዓለማችንን አምባገነን መሪዎች ከነአገዛዛቸው ገርስሶ የጣለውን የአረቡን አብዮት (The Arab Spring ይሉታል ሲያሰማምሩት) በወፍ በረርኛ ላስቃኛችሁ እፈልጋለሁ፡፡ እንግዲህ በቱኒዝያ በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ አነሳሽነት የግብፅ” የሊቢያና የየመን አምባገነኖች ከስልጣናቸው ተባርረው” አሁን የቀሩት የሶሪያው አምባገነን መሪ ባሺር አል - አሳድ ብቻ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን በወጣ ዘገባ ላይ እንዳነበብኩት” የቱኒዝያ ህዝቦች አብዮታቸውን ሀ ብለው ሲጀምሩ ልክ እንደፊልም ለአብዮቱ ሳውንድ ትራክ አዘጋጅተው ነበር አሉ - አብዮታቸውን የሚያጅቡበት፡፡

የቱኒዝያው የአብዮት ማጀቢያ ምን የሚል መሰላችሁ? “ህዝቡ አገዛዙን መጣል ይፈልጋል!” የግብፅ ህዝባዊ አብዮት ደግሞ በዝነኞቹ የጎዳና ላይ የግጥም ንባቦች የታጀበ ነበር፡፡ እናላችሁ የሙባረክ አገዛዝ የተገረሰሰው በአመፅ ብቻ ሳይሆን በቅኔም ጭምር ነው! (ጥበባዊ “ተች” ነበረው ማለት ነው)

የሶሪያ አብዮት የመጀመርያ ሳውንድ ትራክ “Syria wants freedom”   (ሶሪያ ነፃነቱዋን ትፈልጋለች )  የሚል ሲሆን በቅርቡ ደግሞ አንድ ሌላ ትኩስ የአብዮት ማጀብያ እንደተለቀቀ ተገልፁዋል - “Come on Bashir, Leave”  የሚል፡፡ (ባሺር-- ባክህ ከስልጣን ውረድ እንደማለት!) ምንም እንኩዋን አምባገነኑ የሶሪያ ፕሬዚዳንት ጆሮአቸውን ደፍነው “አይሰማም!” ቢሉም፡፡ በአሁኑ ሰዓት በሶሪያ ተቃዋሚዎች ዘንድ እጅግ ከፍተኛ ተወዳጅነትን ያተረፈው ይሄ ዜማ “Hey Bashir , Hey  liar , Damn you and  your speech, freedom is right at the door, so come on Bashir, leave!” የሚል ነው (ስማ ባሺር --- አንተ ቀጣፊ---- አንተና ዲስኩርህ እንጦሮጦስ  ግቡ--- ነፃነት ደጃፉ ላይ ነው ያለው --- ስለዚህ ባክህ ባሺር---- ስልጣንህን ልቀቅ! እንደማለት ነው ) በነገራችሁ ላይ ኢህአዴግም እኮ ደርግን የታገለው በመሳሪያ ብቻ አይደለም - በሳውንድ ትራክም ጭምር ነው! (በአጃቢ ሙዚቃ)

በቅዳሜ ምድር በደረቁ እንዳንለያይ አንድ ቀልድ ከኦባማ አገር እንስማ!

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ሄነሪ ኤም ፓልሰን” ኒውዮርክ ሴንትራል ፓርክ ውስጥ ሲዝናኑ ከአንድ ቁጥቁዋጦ ስር ጭምብል ያጠለቀና መሳሪያ የያዘ ሰው ይወጣና “

“ያለህን ሁሉ ቁጭ አድርግ!” ይላቸዋል የደነገጡት ፓልሰን- “ተው እንጂ የኔ ወንድም --- እኔ እኮ የገንዘብ ሚኒስትሩ ነኝ” ይሉታል ዘራፊም- “እንዲያ ከሆነማ ---- በል ገንዘቤን ስጠኝ” አለ - ከዝርፊያ ገላገልከኝ በሚል ቃና

 

 

Read 3580 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:59