Saturday, 03 November 2018 15:30

ለአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ህክምና የተሰበሰበው ገንዘብ እያወዛገበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  - “ቴዎድሮስ ተሾመ በስሙ የተሰበሰበውን ገንዘብ ወደ ዋናው አካውንት ያስገባ” - ኮሚቴው
    - “በኮሚቴው እምነት ስለሌለኝ ገንዘቡን ለህጋዊ ወራሾች አስረክባለሁ” - ቴዎድሮስ ተሾመ
      
    በኩላሊት ህመም በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን አንጋፋውን ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያምን ለማሳከም በተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ኮሚቴዎች ባለመስማማታቸው ጉዳዩ እያወዛገበ ነው ተባለ፡፡
በኢትዮጵያ አካውንት ገንዘብ ሲያሰባስብ የነበረው በኃይሉ ከበደ  የሚመራው ኮሚቴ፤ በአርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ስም በተከፈተው “ጐ ፈንድ ሚ” አካውንት የተሰበሰበውን ገንዘብ አርቲስቱ ሀገር ውስጥ በሚገኘው የባንክ ሂሣብ እንዲያስገባ ተጠይቆ “በኮሚቴው ላይ እምነት ስለሌለኝና በኋላ በህግ ስለሚያስጠይቀኝ ወደ አካውንቱ አላስገባም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ለሁለት የተከፈለው ኮሚቴ ትናንት በአፍሮዳይት ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ በአርቲስት መሠረት መብራቴ፣ መቅደስ ፀጋዬና የፍቃዱ ተክለማርያም የቅርብ ወዳጅ በሆነው ዮሐንስ በሚባል ሰው በአገር ውስጥ በተከፈተው አካውንት ከ1.2 ሚ. ብር በላይ የሚገኝ ሲሆን አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ከመሞቱ በፊት ለኩላሊት ታካሚዋ ወጣት ከለገሰው 200ሺ ብር ውጭ የተነካ ነገር እንደሌለ የኮሚቴው ሰብሰቢ አቶ ኃይሉ ፀጋዬ ገልፀው፤ በቴዎድሮስ ተሾመ ስም በተከፈተው “ጐ ፈንድ ሚ” አካውንት ከኮሚቴው እውቅና ውጭ ገንዘቡ ወጪ እየተደረገ መሆኑን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡
አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በበኩሉ፤ በአሁኑ ሰዓት በስሙ በተከፈተው አካውንት 73ሺ 900 ዶላር መሰብሰቡን ገልፆ፤ ለአርቲስቱ የህንድ የህክምና ጉዞና ለሌሎች ወጪዎች 8ሺ 280 ዶላር፣ ለአርባው መደገሻ ለባለቤቱ 20ሺ ብር መስጠቱን ጠቅሶ፤ አሁንም ለአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም የሚመጥንና ስሙን የሚያስጠራ ሃውልት ለማሰራትና እንዲሁም የዲያሊሲስ ማሽን ገዝቶ ለኩላሊት ህመምተኞች ማህበር ለመገለስ ከአርቲስቱ ቤተሰብ ጋር መስማማቱን በመግለጫው ላይ አስታውቋል።  ቤተሰቡ አውቆት ከሚወጣው ገንዘብ የተረፈውን በፍርድ ቤት ወራሽነታቸው ለተረጋገጠው የቤተሰቡ አባላት እንደሚያስረክብም የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ “በስሜ ለተሰበሰበው ገንዘብ ሙሉ ኃላፊነት እወስዳለሁ” ብሏል፡፡ የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፤ “አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ አራተኛ ፈራሚ በመሆን ገንዘቡን ወደ ኢትዮጵያው አካውንት አጐዛ ቅርንጫፍ አስገብቶ በጋራ ለመስራት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ እንሥራ፣ የዲያሊሲስ ማሽኑ ከሚገዛ ገንዘቡ ለኩላሊት ታማሚዎች ይሰጥ፣ ማሽን በመንግሥት በኩል እየተገዛ ነው፤ ያለው ኮሚቴው፤ “ቤተሰቡ ሃውልት ለማሰራት ማሰቡንም ሆነ የዲያሊስስ ማሽን የመግዛት ዕቅዱን ከቴዎድሮስ ተሾመ ጋር እየተመካከሩ የጀመሩት እንጂ እኛ እንደ ኮሚቴ የምናውቀው ነገር የለም” ብሏል፡፡
የአርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ታናሽ ወንድም አቶ ግርማ ተ/ማርያም፤ ወንድማቸው ከታመመ ጀምሮ ህይወቱን ለማትረፍ ህዝቡ፣ ሚዲያውና ኮሚቴው በጋራ ያደረጉትን እርብርብና ተሳትፎ አድንቀው፣ ሆኖም እሱ ካለፈ በኋላ ኮሚቴው ባለመግባባት ሚዲያ ፊት መቅረባቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀው፤ አሁንም ቢሆን ኮሚቴውና ቴዎድሮስ ተሾመ ተስማምተው በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡  
ኮሚቴው ከፍቃዱ እረፍት በኋላ ወደ ቤተሰቡ መጥቶ እንዴት ናችሁ ብሎ ባለመጠየቁና ገንዘቡ አይንቀሳቀስም የሚል አቋም በመያዙ እንዲሁም የፍቃዱ አድናቂዎችና ወዳጆች ሃውልቱ ከምን ደረሰ እያሉ በመጠየቃቸው ከቴዎድሮስ ተሾመ ጋር በመመካከር ሃውልቱን ለማስገንባት የዲያኪሲስ ማሽን ገዝቶ ለመለገስ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡
አርቲስት ቴዎድሮስ በበኩሉ፤ ገንዘቡን ኢትዮጵያ ወዳለው አካውንት ቢያስገባ እሱ ስለማያዝበትና ስለማይቆጣጠረው በህግ ተጠያቂ እንደሚሆን የህግ አማካሪው እንደነገረው ጠቅሶ፤ “አራተኛ ፈራሚ ሆነህ ገንዘቡን ወደ ኮሚቴው አካውንት አስገባ” ለሚለው የኮሚቴው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትና ለመወሰን ግን በድጋሚ ጠበቃውን ማማከር እንዳለበት ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል አርቲስት ፍቃዱ በደብረብርሃን አቋቁሞታል የተባለው “ሀበሻ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል” በተመለከተ እስከ ዛሬ የተረጋገጠ ነገር የሌለ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ አቶ ግርማ ሲመልሱ፤ በደብረብርሃን ያለው የአረጋውያን መርጃ ማዕከል ፍቃዱ የከፈተው ሳይሆን ከአራት ዓመት በፊት በስምህ ልጠራ ብሎ አስፈቅዶ በፍቃዱ ስም መጠራት የጀመረው የመንፈስ ልጁ ዮርዳኖስ ፍቃዱ የከፈተው መሆኑን ጠቁመው አርቲስት ፍቃዱን የበላይ ጠባቂ አድርጐት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
የአርቲስት ፍቃዱ የእህት ልጅ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የአርቲስት ፍቃዱ ቤተሰቦች በገንዘብ ጉዳይ ባለመስማማት ጉዳዩ ፍርድ ቤት ደርሷል እየተባለ የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ሃሰትና የቤተሰቡን ስም የሚያጐድፍ መሆኑን ገልፀው፤ “እንኳን ልንጣላ በየወሩ በፍቃዱ ቤት እየተሰበሰብን፣ እሱን የምናስብበት ፕሮግራም አለን” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ለአርቲስቱ መታከሚያ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጐዛ ቅርንጫፍ 1,200,895 ብር ከ69 ሣንቲም (አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሺ ስምንት መቶ ዘጠና አምስት ብር ከስልሳ ዘጠኝ ሳንቲም) የሚገኝ ሲሆን፤ በቴዎድሮስ ተሾመ ስም በተከፈተው “ጐ ፈንድ ሚ” አካውንት 73ሺ 900 ዶላር እንደሚገኝ ኮሚቴውና አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ ባቀረቡት ሪፖርት አረጋግጠዋል፡፡

Read 1271 times