Saturday, 03 November 2018 15:30

የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ!

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ብለነዋል፤ ማንም ስላልሰማን ደግመን እንለዋለን ይላል - አንድ የጥንት ታሪክ ፀሐፊ፡፡ የእኛም እንደዚያው ነው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ደገኛ ገበሬዎች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ሳር ቤት ነው ያላቸው፡፡ ደሳሳ ጎጆዎች ናቸው፡፡ በድንገት አንድ ቀን የአንደኛው ገበሬ ቤት ተለወጠ፡፡ ቆርቆሮ ቤት ሆነ፡፡ ጎረቤትየው ደነገጠና፤
“ወዳጄ፤ እንዴት ይሄ ቤትህ ሊለወጥ ቻለ? ምን ተዓምር ተገኘና ነው?”
ገበሬው፤
“አየህ በሬዎቼን ሸጥኳቸውና ታች ቆላ ወርጄ ብረታ ብረት ገዛሁ፡፡ ከዚያ ደጋ አምጥቼ ለቀጥቃጩ፣ ለባለእጁ፣ ማረሻ ለሚፈልገው ገበሬ ሸጥኩ፡፡ ብዙ ብር አገኘሁ፡፡ ቤቴን ለወጥኩ፡፡ አጥሬን ለወጥኩ፡፡ ራሴን ለወጥኩ!”
“በቃ፤ እኔም እንዳንተ አደርጋለሁ” አለና ሄዶ በሬዎቹን ሸጠ፡፡ ከዚያም ገበያ ገብቶ ማጭድ፣ አካፋ፣ ዶማ፣ ማረፊያ፣ ገሶ … ብቻ አለ የሚባል የብረት ግብዓት ገዝቶ፣ ተሸክሞ፣ ወደ ደጋ ዳገቱን ተያያዘው፡፡
ሆኖም ያን ሁሉ ብረት አቅሙ አልችል አለና ዳገቱ ወገብ ላይ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ የመንደሩ ሰው በዚያ ሲያልፍ አየውና፤
“አያ እገሌ ምን ሆነህ ነው?”
“ያ ጎረቤቴ ገበሬ ጉድ አርጎኝ ነው!”
“ምን አደረገህ?”
“ንግድ ጀምሬያለሁ ብሎ የንግዱን ጠባይ ነገረኝ፡፡ ባለኝ መሰረት ንግድ ውስጥ ገባሁ”
“ታዲያ እሱ ምን በደለህና ነው ጉድ አደረገኝ የምትለው?”
“ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ!”
***
አያሌ ትርፍ ያስገኛሉ የተባሉ ነገሮች መከራ እንዳላቸው መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ቀላል የሚመስሉ ግን ውስብስብ የሆኑ፣ ውስብስብ ሆነው የባሰ የሚወሳሰቡ፣ ሳንማርባቸው ያለፉ፣ ተምረንባቸው የተረሱ፣ ጨርሶ ያላጠናናቸው ብዙ ብዙ ቁምነገሮች አሉ፡፡
“ከበሮ በሰው እጅ ያምር
ሲይዙት ይደናገር!” የሚባለው ተረት፣ ለተሿሚዎቹ ሁሉ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው! በተለይ ሴት ተሿሚዎች መብዛታቸው አኩሪ የመሆኑን ያህል ኃላፊነታቸውን መወጣታቸው፣ ከሙስና የፀዱ መሆናቸው፣ የፆታ እኩልነትን ማበልፀጋቸው፣ ለበርካታ ሴቶች አርአያ መሆናቸው፣ ከወንዶች ይልቅ ዝርዝር ጉዳይ ላይ የማተኮር ክህሎታቸው (Meticulousness) እጅግ የላቁ ያደርጋቸዋል! ይሄ ቢሳካልን ላሜ ወለደች ነው! ይህን ዕድል እንደ ሌሎች ያመለጡን ዕድሎች እንዳይሆን መትጋት ያስፈልጋል፡፡ የእናቶች ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የህፃናት ፀጋ በእጃችን ነው፡፡ የትምህርት ፀጋ በእጃችን ነው! የሚያስጎመጅ ዕድል ባያመልጠን መልካም ነው! የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የተስፋ፣ የራዕይ ጊዜ እየጀመረ ነውና እንጠቀምበት! ለብዙ ዓመታት የጮህንለት የሴቶች አጀንዳ መልካም ጉዞ ይጓዝ ዘንድ የወንዶችም የሴቶችም ጥያቄ አድርገን እንየው፡፡ አለበለዚያ “የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ” ይሆንብናል!!

Read 8002 times