Saturday, 27 October 2018 10:24

“የሚሰራው ህንፃ ከአካባቢው መብቀል አለበት”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

 • በአዕምሮ የምታስበውን ወደ መሬት ለማውረድ ነፃነት ያስፈልጋል
• ከተማን እኛ እንሰራዋለን፤ መልሶ ደግሞ ከተማ እኛን ይሰራናል

  ከኩባንያህ ዓላማና ራእይ በመነሳት ውይይቱን ብንጀምረውስ?
ለኩባንያችን “አስፓየር” የሚለውን አዲስ ስም በቅርቡ ብናወጣም፣ የሚታወቀው “ሐብታሙ ኢንተርናሽናል አማካሪ መሐንዲሶችና አርክቴክቶች ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” በሚል ስያሜ ነው፡፡ በመስክና በቢሮ ከ200 በላይ ሰራተኞች የሚያስተዳድር ሲሆን በኮንስትራክሽን ዘርፍ  ለ14 ዓመታት ሰርተናል፡፡ በመጀመርያ የተነሳነው ከደረጃ አምስት ሲሆን በደረጃ 1 አጠቃላይ አማካሪ መስራት የጀመርነው  ከ12 ዓመት በፊት ነው፡፡ ስንመሰረት ባስቀመጥነው ራዕይ፣ ዓላማና ግብ መሰረት መድረስ የምንፈልገው፣ ዓለም አቀፍ ሚና በምንጫወትበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ በምህንድስናው  የላቁ ስራዎችን ማምጣትና መስጠት እንፈልጋለን፡፡ በየጊዜው ደረጃችንን በማስተካከልና በማሻሻል እየሰራን ቆይተናል፡፡ በ2008 በአይኤስኦ እውቅና አግኝተናል፡፡ ከጀርመን ቴክኒካል ተራድኦ ጂቲዜድ አይኤስ  ጋር የሰራንበትም ልምድ አለ። ጂቲዜድ አይኤስ  ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረበት ወቅት ሁለት የዩኒቨርስቲ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ለመስራት ፕሮፖዛል ፅፈን ተወዳድረናል፡፡ በመጀመርያ  ለአይኤስኦ ሰርተፍኬት የሚያበቃ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሰጥተውን፣ በጥሩ ውጤት አለፍን፡፡ ከዚያ ፕሮጀክቶቹን ለመስራት የቻልነው ከተራድኦ ድርጅቱ ጋር በዋናነት ከሰሩ አማካሪ መሐንዲሶች አንዱ ለመሆን በመብቃታችን ነው፡፡ ኩባንያችንን የምናስተዳድረው በአይኤስኦ ማኔጅመንት መሰረት ነው። የኩባንያችንን የአጭር ጊዜ ግቦች ብዙዎቹን አሳክተናል፡፡ በአንድ ክፍል ቢሮ መስራት ስንጀምር በአጭር ጊዜ ግባችን በራሳችን ፎቅ ላይ ለመስራት እንዳቀድነው፣ ያንን ለማሳካት የምንችልበት የገንዘብ አቅም ፈጥረናል። ከምህንድስናው አንፃር ግን ብቻችንን መፍጠር የምንችለው ነገር ስለሌለ ብዙ ርቀት አልተጓዝንም፡፡ እንደ አገር ስታንዳርድና ኮድ ባለመኖሩ ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ በራሳችን አደረጃጀት ብቻ ለመቆም አይቻልም፤ ምክንያቱም ከሌሎች ተቋማት ጋር ስትገናኝ የሚያግባባ ብሄራዊ መዋቅር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው የላቁ የምህንድስና ስራዎች በአገር ውስጥ ለማከናወን ገና ብዙ እንደሚቀረን የማስበው፡፡
ዓለም አቀፍ ሚና ለመጫወት ባስቀመጣችሁት የረጅም ጊዜ እቅድ ምን ያህል ርቀት ተጉዛችኋል?
በምህንድስና አማካሪነት ስትሰራ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዶች አሉ፡፡ ብሄራዊና አህጉራዊ ስታንዳርዶችም ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ  የኮንስትራክሽን መስክ ያለበት ደረጃ አያረካም፡፡ ምህንድስናው ዘመናዊ አገራዊ መዋቅርና መለኪያ ደረጃ የለውም፡፡ ስለዚህም ከረጅም ጊዜ እቅዳችን አንፃር ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻልንም፡፡ በኮንስትራክሽን ዓለም አቀፍ ትኩረት የምናገኝበትን ደረጃ ብቻችን ልንፈጥረው አንችልም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጉን ልምዶች ቢኖሩንም፤ እንደፈለግነው እየሰራን ግን አይደለም። በምህንድስናው በአገር ውስጥ የላቀ ደረጃ ብንደርስም፣ ዓለም አቀፍ ሚና ለመጫወት ለብቻችን የምንራመድበት አቅጣጫ የለም፡፡ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተግባብተን የምንሰራበት ብሄራዊ የጥራትና የብቃት ስታንዳርድ ወሳኝ ነው፡፡
በረጅም ጊዜ እቅዳችን ዓለም አቀፍ ሚና ለመጫወት ስናቅድ በበቂ ምክንያት ነው፡፡ በምህንድስና አማካሪነት ማሟላት ያለብንን ዓለም አቀፍ ደረጃ እንደያዝን አምናለሁ። ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ ‹‹ትሪፕል ኤ›› ወይም የአሜሪካ አርክቴክቶችና አማካሪዎች ማህበር በሚያወጣው ደረጃ መሰረት ልንለካ እንችላለን። በኮንስትራክሽን አማካሪነት ይህ ተቋም ቢፈትነን፣ የዓለምን ደረጃ ጠብቀን የምንሰራበት አቅም ስላለን ለማለፍ አንቸገርም፡፡ የፋይናንስ አቅም ካልገደበን በቀር በእውቀት ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር ተጣጥመን እንደምንሄድ ነው የማስበው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤በአህጉራዊ ደረጃና በብሄራዊ ደረጃ ያሉትን ስታንዳርዶች በምናሟላበት አቅጣጫ እየተጓዝን ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን መስክ ያሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኙ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሰብን፣ በብሄራዊ ደረጃ እየተገበርን መስራታችንን እንቀጥላለን፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመስራት እንፈልጋለን ስንል፣ ከኢትዮጵያም ውጭ ለመስራት አቅም እስከ መፍጠር ድረስ ይዘልቃል። በአገር ውስጥ ከተለያዩ አገራት ኩባንያዎች ጋር በጥምረት የሰራንባቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸው፣ የምንፈልገውን ዓለም አቀፍ ደረጃ ለመቀዳጀት በቂ ልምድ አስገኝተውልናል፡፡ ከእስራኤል ኩባንያዎች ጋር ተጣምረን፣ ጆይቴክ በተባለ የአበባ እርሻ መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ሰርተናል፡፡ ከቻይና ኩባንያዎች  ጋር የሰራናቸው ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሰብን በብሄራዊ ደረጃ እየሰራን ነው ብለሃል፡፡ ልታብራራው ትችላለህ?
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የላቀ የምህንድስና ደረጃ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እየሰራን ነው፡፡ ይህንንም በአንድ ወቅታዊ ምሳሌ ማስደገፍ እፈልጋለሁ። ዘንድሮ ኦህዴድ ስሙን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ብሎ  የቀየረበት ጉባኤ ጅማ ላይ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ይሄን ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ያስተናገደው እኛ የገነባነው ልዩና ሁለገብ ስታዲየም ነው፡፡ ይህን መሰረተ ልማት ከህንድ ኩባንያዎች ጋር በፈጠርነው ጥምረት ገንብተነዋል። የኩባንያችንን የዳበረ ልምድና የተለየ ብቃት የሚያስመሰክር ነው፡፡ አዳራሹ የተገነባበት የምህንድስና ደረጃ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ የሚጠቀስ ነው። ስፓኑ ወደ 100 ሜትር በ52 ሜትር ሆኖ፣ በ26 ሜትር ቁመት የተገነባ ነው፡፡ በንፅፅር ለማሳየት የአየር መንገድን ተርሚናል መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአየር መንገድ ተርሚናል ስፋቱ ትልቁ 23 ሜትር ነው፤ የጅማ ሁለገብ አዳራሽ ግን 52 ሜትር ይደርሳል፡፡ ይህም የግንባታ ቴክኖሎጂውን በእጥፍ ማሳደጋችንንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን  ጠብቀን መስራታችንን ያረጋግጣል፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስቡ ብቁ ባለሙያዎች በተለያዩ መስኮች ከሌሏት፣ ከውጭ የሚመጡ ወቅታዊ  ቴክኖሎጂዎችን ልትጠቀም አትችልም፡፡ በዚህ ደረጃ መስራት ካልቻልን ደግሞ ሁሉንም በራሳችን አቅም ለመገንባት የሚሳካልን አይሆንም፡፡ ስለዚህም ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የሚግባባና የሚቀራረብ እውቀትና የብቃት ደረጃ ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ደረጃ የእኛ ኩባንያ ያለውን አቅም ለማሳደግ በተለያዩ መንገዶች ሲሰራ ቆይቷል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት የነበረንን መልካም ተመክሮ ማንሳት እፈልጋለሁ። ሁለት የውጭ አገር ባለሙያዎችን በኩባንያችን ቀጥረን በማሰራት ያገኘነው ልምድ ነበር። በኩባንያችን ተቀጥረው ለ1 ዓመት በሰሩበት ወቅት ትኩረት የሰጠነው  ከስራ ባህላቸው ለመማር ነበር። ከተማርናቸው የስራ ባህሎቻቸው ዋንኛው የተሟላ ጥናትና እቅድ ከግንባታ በፊት አስፈላጊ መሆኑን ነው። በምህንድስና የላቀ ደረጃ  በደረሱ አገራት አንድ ፕሮጀክት ከመገንባቱ በፊት ረጅሙን ጊዜ የሚወስደው ጥናቱ ነው፡፡ ለምሳሌ የዲዛይን ስራው 1 ዓመት ከፈጀ፣ ግንባታው 3 ወር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት እቅድን ከክንውን ማስቀደም እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብዙ ፕሮጀክቶች በቂና ሰፊ ጥናት ተደርጎባቸው አይሰሩም፡፡ በአጭር ጊዜ እቅድ ወደ ግንባታ የመግባት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በዓለም አቀፉ ደረጃ ግን እቅድ ከክንውን ይቀድማል፡፡ አንድ ፕሮጀክት ዲዛይን ሲደረግ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ሲተገበር ደግሞ በአጭር ጊዜ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮንስትራክሽኑ መስክ በዝቶ የሚታየው ግንባታዎች ከእቅድ የበለጠ ጊዜ ሲወስዱ  ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የቤቶች ልማትን ብትወስድ፣ የቤቶች ፖሊሲ ሳይኖር ነው ፕሮጀክቱ መተግበር የተጀመረው። ስለዚህም አፈፃፀሙ ላይ ችግር ተፈጥሯል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ለግዙፍ ግንባታ የታሰበው ዲዛይን ይመረቅና ከዚያም ወደ ግንባታ ከተገባ በኋላ ለመጨረስ ያዳግታል፡፡ አንዳንዴ እንደውም ዲዛይንን በማስመረቅ  ገቢ ለማሰባሰብም ይሞከራል፡፡ በዘመናዊው ኮንስትራክሽን  ቅደም ተከተሉ እንዴት ነው?
የኮንስትራክሽን ሂደቱ መነሻ ሃሳብ ከመጀመሩ በፊት አገልግሎቱ ያስፈልጋል አያስፈልግም በሚል የሚደረገው ጥናት ነው፡፡ ማናቸውም ግንባታ በአገር፤ በክልል፤ በከተማ፤ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ተዋረዱን ጠብቆ መታቀድ ይኖርበታል፡፡ ሁሉን ነገር በተሟላ ሁኔታ አስቦና እቅዶ መነሳት ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ መሃል አንድ ውስን ፕሮጀክትን መነሻ አድርጎ፣ በጀት ለማግኘት በተለያየ መንገድ መስራት ይቻላል።  ሃሳብ ብቻ ተይዞ ገንዘብ ወደ ማሰባሰብ መግባት፣ ከትክክለኛው የጥናት ሂደት የሚፃረርና የተገላቢጦሽ የሆነ አካሄድ ነው፡፡ መሆን ያለበት በኪስ ውስጥ በጀት ተይዞ ወደ ትግበራ መግባት ነው፡፡  በቂ ገንዘብ ሳይኖር የግንባታ ፕሮጀክቱን መጀመር ገንዘብ ሲያንስ ሂደት ለማጓተትና ለማቋረጥ ምክንያት ይሆናል፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ፕሮጀክቱ የሚጠይቀውን የገንዘብ አቅም መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቱን በምን አይነት መንገድና ግብዓት እሰራዋለሁ የሚለውን ለማቀድ ወሳኝ ነው፡፡
የፈረንሳይ መዲና የሆነችውን ፓሪስ ያሳወቃት ልዩ ላንድ ማርክ ‹‹ኤፈል ታወር›› የገነባው ጉስታቭ ኤፍል የሚባለው ግለሰብ የብረታብረት መሐንዲስ ነበር። በወቅቱ ፈረንሳይ በብረታብረት ኢንዱስትሪው በአምራችነት ከፍተኛ ድርሻ ስለነበራት፣ይህንኑ በግንባታው ለማስተዋወቅ ከመነሻው አቅዶ ነበር፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የመሰረተ ልማት ግንባታ፤ የየአገሩን ማህበረሰባዊ ደረጃ፤ ኢኮኖሚያዊ አቅምና  የአኗኗር ሁኔታና ደረጃ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። በዚህ መንገድ ከተሰራ ማንኛውም ግንባታ  የአገሩን ህልውና የሚጠብቅ ብሎም  የሚያስተዋውቅ ይሆናል።
ሲንጋፖር ሌላዋ ምሳሌ ናት፡፡ በመጀመርያ አገሪቱ ምንም የረባ መሰረተ ልማት የሌላት ነበረች። ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ይህን ለመለወጥ ፈለገ፡፡ በዋና ከተማዋ ‹‹ታይፔ 11›› በሚል ስያሜ ሁለት ግዙፍ ህንፃዎችን ለመስራት አቀደ፡፡ ህንፃዎቹ ዲዛይናቸው በሲንጋፖር ያለውን ባህላዊ የጎጆ ቤት አሰራር ‹‹ፓጎዳ›› እንዲመስሉና በግዝፈታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው እንዲሆኑም ታስቧል፡፡ በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሲንጋፖር የምትቆምበትን ህንፃ እንስራ” ብሎ በስፋት በማቀድ ነው የተነሳው፡፡ በመጨረሻም  ከዓለማችን ረጅሞቹና ልዩ የሆኑ ህንፃዎችን ለመገንባት ተችሏል። የሲንጋፖሩ ልምድ ያለ ምንም ሪሶርስ፣ በላቀ አስተሳሰብ ብቻ አገርን መገንባት እንደሚቻል ያሳያል። በዚህ አቅጣጫ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር በመሰረተ ልማት በማጥለቅለቃቸው ዛሬ ዋና ከተማዋ የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ መናኸርያ ሆናለች፡፡ ስለዚህ የላቁ ሃሳቦችን በማመንጨት ትልቅ መሰረተ ልማት መገንባትና አገርንም በከፍተኛ ደረጃ ማስተዋወቅ እንዲሁም  ለዓለም ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡
የኩባንያችሁ የግንባታ (ኮንስትራክሽን) ፍልስፍና ምንድን ነው?
በእኛ በኩል ያለው አስተሳሰብ፤ የሚሰራው ህንፃ ከአካባቢው መብቀል አለበት የሚል ነው፡፡ ሰዎች እንደየ አካባቢያቸውና ባህላቸው የተለያዩ ስለሆኑ ማንኛውም ግንባታ አካባቢያቸውንና ባህላቸውን መምሰል ይኖርበታል። በአዲስ አበባ የተሰራውን ህንፃ ወደ አርባ ምንጭ ወይም ወደ ጅማ ሙሉ ለሙሉ ገልብጦ በመውሰድ ለመስራት አንሞክርም። በየትኛውም ከተማ የሚገነባ መሰረተ ልማት፤ የከተማውን ህዝብና አካባቢውን መምሰል አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር በእኛ በኩል ያሉትን ተመክሮዎች ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በአርባ ምንጭ የሚገኘውን ባህላዊ አዳራሽ ስንገነባው፣ በከተማው የእንሰት ተክል ያለውን ትልቅ ዋጋ  ከግምት ውስጥ አስገብተናል፡፡ በመጀመርያ ዲዛይኑን ኮባ እንዲመስል አደረግነው፤ከዚያም በክልሉ በሚኖሩ አምስት ብሄረሰቦች ያሉትን ባህላዊ የቤት አሰራሮች አዋህደን ዲዛይኑን ሰርተነዋል፡፡ ስለሆነም በአርባ ምንጭ ብቻ ሊገኝ የሚችልን ገፅታ በማላበስ፣ ግንባታውን ጨርሰን ማስረከብ ችለናል። በጅማ ያለውን የአባ ጅፋር የባህል ማዕከልና ሙዚየም ዲዛይን የሰራነው በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡ በአካባቢው ያለውን ማህበረሰባዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ሃብት በሙሉ አቅም ተጠቅመንበታል፡፡ ስለዚህም ማንኛውም ፕሮጀክት አካባቢውን የመሰለ የዲዛይን ሃሳብ ኖሮት ሲሰራ፣ ግንባታው ይበቅላል እንጂ አይተከልም፡፡
ይህ የምህንድስና አሰራር ኦርጋኒክ አቅጣጫ  ነው። በአካባቢው ወግና ባህል፤ ባለው የተፈጥሮ ሃብትና በነዋሪው የሰው ሃይል የሚሰራ በመሆኑ እንግዳ መሰረተ ልማት አይሆንም፡፡ ይህ አይነቱ አቅጣጫ ለማንኛውም ግንባታ የአካባቢው ተቀባይነት፣ ወሳኝ ሚና ያለውና ሃርመኒ የሚፈጥር ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ስታንዳርድ ነው፡፡ በተፈጥሮ መጠቀም በኮንስትራክሽን ዓለም አዲሱና ኦርጋኒኩ አማራጭ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ነገሮች ኢኮኖሚካል የሚሆኑት፤ ወይም ለማህበረሰብ ተስማሚ የሚሆኑት ኦርጋኒክ ሲሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በጫካ የበቀለ ቡና የራሱ ጣዕም አለው፣ ሌላ ቡና ደግሞ በኬሚካል ብታሳድገው ከተፈጥሮውም ከኬሚካሉም የሚወስደው ነገር በመኖሩ፣ ከጫካው ቡና የተለየ ጣዕም ይኖረዋል። ኦርጋኒክ ከሰውም ከአካባቢውም ጋር ይስማማል። ግጭት ሳይሆን መጣጣም ነው የሚፈጥረው፡፡ በሦስተኛው ዓለም ብዙ ኦርጋኒክ አቅም በመኖሩ በምህንድስናውና በኮንስትራክሽን መስክ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት የሚቻልበት አቅም ፈጥሮልናል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከጠቀስከው የኦርጋኒክ አቅጣጫ አንፃር በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ኢትዮጵያ ውስጥ ኮንስትራሽን የሚገኝበትን ደረጃ እንደ ህንፃ ባለሙያ አርክቴክት ስመለከተው፣ በመጀመርያ የምንግባባበት ሁላችንንም ያማከለ ስታንዳርድ ያስፈልጋል ነው የምለው፡፡  በኮንስትራክሽን መስክ ብሄራዊ መግባቢያ ሰነድ ባለመኖሩ ሁሉም የፈለገውን ይሰራል፡፡ በዚህም የከተማው አጠቃላይ ገፅታ ምንም አይነት መጣጣም የሌለው፤ ደረጃውን ያልጠበቀና ዘላቂነት የሌለው ሆኖ ቀጥሏል፡፡ መጀመርያ አንድ ግንባታን ዲዛይን ከማድረግ በፊት ለሰዎች ምቹ ነው ወይ በሚል ሁሉም የሚገዛበት ስታንዳርድ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በፎቆች ርዝመት፤ በሚቀቡት ቀለም፤ በሚለብሱት መስታወት… ዙሪያ በጥናት ላይ የተመሰረተ መመርያ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ለሁሉም የኮንስትራክሽን ባለድርሻ አካላት የሚሰራና የሚተገበር ስታንዳርድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች የሚመሯቸው የተለያዩ ማህበራት ቢኖሩም፣ በቂ ስራ እየሰሩ አይደለም፡፡ ማህበራቱ እንዲጠናከሩና ተገቢውን ስራ እንዲያከናውኑ በመጀመርያ የሚመለከተው የመንግስት አካል በአግባቡ ተደራጅቶና ተጠናክሮ መስራቱ ይጠበቃል፡፡ ህግ የሚያስከብረው አካል የተጠናከረ ሲሆን ማህበራቱ ተገቢውን እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት አቅም ይፈጠርላቸዋል፡፡ ግንባታዎች መሰራት ያለባቸው ወጥ በሆነ ስታንዳርድ፤ ማህበረሰቡን ሳይጎዱና ከተፈጥሮ ተግባብተው ነው። በዚህ በኩል ለኢትዮጵያ የሚቀርበውን ተመክሮ ከሌላው የዓለም ክፍል በመውሰድ መነሳት ይቻላል። ሁሉም በሚያከብረውና በሚተገብረው ስታንዳርድ ግንባታዎች እንዲሰሩ ያደርጋል። ይህ ከተማን እኛ እንሰራዋለን፤ መልሶ ደግሞ ከተማ እኛን ይሰራናል ማለት ነው፡፡ ግንባታዎቻችን በተሟላ መንገድ ከተሰሩ ህዝብም የተሟላ አገልግሎት ያገኛል፡፡ በከተማ ውስጥ መሬት ውድ ከሆነ፣ የግንባታው ሂደት ይህን ሁኔታ ከግምት ውስጥ የሚያስገባ እንጂ በተዘበራረቀ ሁኔታ የሚጠቀም መሆን የለበትም፡፡ ከተማ የምትሰራው ለሰው ነው፡፡ ሰው ለከተማ ሊሰራ አትችልም፡፡ ስለዚህ የከተማ ግንባታዎችና ማስተር ፕላኖች የህዝቡን ሃሳብ መነሻ አድርገው የሚታቀዱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በምህንድስናው መስክ ባሉ ባለሙያዎች መካከል መከባበር ያስፈልጋል፡፡ ይህ መከባበር የሚፈጠረው ደግሞ ልምድ ያላቸውና አዳዲሶችን የሚያግባባ ብሄራዊ ስታንዳርድ ሲኖር ነው፡፡
በጅማ ከተማ የአባ ጅፋር የባህል ማዕከልና ሙዚየምን ልዩ ዲዛይን ሰርታችኋል፡፡ እስቲ ስለ ዲዛይኑ በጥቂቱ አብራራልኝ …
የአባ ጅፋር የባህል ማዕከልና ሙዚየም ዲዛይን ከምንኮራባቸው ግዙፍ ስራዎች አንዱ ነው፡፡ ዲዛይኑን ስንሰራ የአካባቢውን ታሪካዊ እሴት፣ የከተማውን አመጣጥ፣ የአባ ጅፋር የከተማ አቆራቆርንና የንግድ ማዕከልነቱን ከግምት ውስጥ አስገብተናል፡፡ ለምሳሌ በአባ ጅፋር ስርወ-መንግስት አምስት ቅርንጫፎች እንደነበሩ በማወቃችን፣ይህንኑ ታሪክ ወደ ዲዛይን ስራው አምጥተነዋል፡፡ የአባ ጅፋር መስጊድ የተሰራበትን ሁኔታ ስናጠና፣ ጎረንዳዮው ላይ ‹‹የኦዳ ዛፍ›› የመሰለ ቅርፅ ነበረ። እሱንም ወስደነዋል። ከዚያም ከአካባቢው የሚነሱትን ሰዎች ከምናነሳ አብረው እንዲያድጉ ብለን ባሰብናቸው የተለያዩ ዲዛይኖች ጨረስነው፡፡ በዲዛይን ስራው የባህል ማዕከልና ሙዚየሙ ሁለገብ አገልግሎት እንዲሰጥ በማሰብ ነው። ማዕከሉ ሙዚየም አለው፤ የቆየውን ህንፃና በውስጡ የያዘቸውን ቅርሶች ለመታደግ ነው፡፡ የስብሰባ አዳራሽ፣ ሲኒማ፣ የገበያ ማዕከል፣ ሆቴል፣ አምፊ ቲያትር… ወዘተረፈ ይገኙበታል፡፡ የአካባቢውን ባህል ይዞ እያደገ እንዲቀጥል ነው ያደረግነው፡፡ ከተማ መድረክ፤ ነዋሪዎቿ ደግሞ ተዋንያን እንዲሆኑ በማሰብ ነው። በአጠቃላይ የዲዛይን ስራው ጅማን የሚያስተዋውቅ ላንድ ማርክ ስለሚሆን ባለድርሻ አካላት ወደውታል፡፡ ወደ አፈጻጸሙ ለመግባትም እየተጠባበቅን ነው፡፡
አዲስ አበባ እንደ ስሟና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫነቷ ማራኪ ናት ማለት ይቻላል? በወንዞች ንፅህና፣ በአደባባዮች አሰራር፣ በሃውልቶች ገጽታ፣ በመናፈሻ ፓርኮች… ረገድ ያሉትን ሁኔታዎች ማለቴ ነው፡፡ መቼ ነው በከተማዋ ገጽታ ላይ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ነገር ለመሥራት የምናስበው?
በማንኛውም ነገር ነፃ መንፈስ ነፃ ሃሳብ ለማምጣት ወይም ስታየው ደስ የሚልህን በፍላጎት ለመስራት የምትጠቀምበት ሚዲያ ያስፈልግሃል። በአዕምሮ የምታስበውን ወደ መሬት ለማውረድ ነፃነት ያስፈልጋል። የሃሳብ ነፃነት ማለት ነው፡፡ ይህን በጥቅሉ ለማምጣት፣ ለትክክለኛው ሰው ትክክለኛውን ወንበር መስጠት ነው፡፡ ሁሉም ግንባታዎች ሁለገብ ጥናት ተደርጎላቸው ሊሰሩ ይገባል፡፡ በጥያቄህ ላይ ያነሳሃቸውን ከተማ ውስጥ ያሉ ውበቶችን፣ ስራዎቹን በሚያውቁ ለትርፍ በሚሰሩ ብቁ ባለሙያዎች ማንቀሳቀስ ይሻላል፡፡ በከተማዋ ውስጥ በርካታ ቤተ ክርስትያናት መገንባታቸው አንድ በጎ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ብዙዎቹ በቂና ሰፊ ነፃ መሬት አላቸው። ይሄ የከተማውን አየር በማስተካከል ረገድ  አስተዋፅኦ አለው። ከተማው ማህበረሰቡን ሊሰራው ይገባል። የኮንስትራክሽን መስኩ በዚህ ረገድ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ብዙ ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። ቀውስ ስልህ መገናኘት የሌለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአንድ በኩል ፖለቲካዊ ፍላጎትና አወቃቀር እየሄደ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮፌሽናል ሙያ በመኖሩ በሁለቱ መካከል ግጭት ከተፈጠረ ጥሩ አይሆንም። ኢትዮጵያ ውስጥ እኮ ብዙ ታሪክ ያለውንና እንደ ቅርስ መቆየት ያለበትን ግንባታ አፍርሰን፣ እላዩ ላይ እንሰራለን። መቶ ዓመት የቆየ ማንኛውም ነገር አንድ ትውልድ ያለፈበት በመሆኑ፣ እንደ ታሪክ ሰነድ (መፅሐፍ) መታየትና መጠበቅ ነበረበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የግንባታ እንቅስቃሴ፣ ለአገራዊ ቅርሶች የሚገባውን ያህል ትኩረት አልተሰጠም፡፡ እነዚህን ቅርሶች ጠብቆና መዝግቦ ማቆየት የሚቻለው እውቀት ባለው፤ ትክክለኛ ሙያን በሚሰራና ብስለት ባለው አደረጃጀት ስር ግንባታዎች ሲካሄዱ ነው፡፡ በከተማ፣ በከተማ የተለያዩ ክፍሎች፣ በሰፈሮች ደረጃ የሚናበቡና ትኩረት ያላቸው ግንባታዎች መኖር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ ሰባት ኮኮብ የኑሮ ደረጃ መኖሩ ጥሩ ቢሆንም፤ ለዚህ አኗኗር የሚሆን የከተማ መሰረተ ልማት ግን የለም፡፡ ኒው ዮርክን የሰራ አንድ አርክቴክት ምሳሌ ባደርግልህ… አንድ ከተማ ዙርያውን በቀለበት መንገድና አረንጓዴ ስፍራዎች መከበብ ይኖርበታል፡፡ ከከተማ እምብርት እስከ ከተማው እምብርት በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያገናኙ መንገዶች ያስፈልጋሉ። በየእንዳንዱ የከተማ ክፍል አረንጓዴ መናፈሻዎች፤ ፓርኮችና አደባባዮች ያስፈልጋሉ፡፡… በሚል ነው አርቆ ያሰበው፡፡
ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው...?
በኮንስትራክሽኑና በተያያዥ መስኮች ለምንቀሳቀስ ሁሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያግባባን ብሄራዊ ሰነድ የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ ነን፡፡  እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል እንዴት መሄድ እንዳለበት የሚመራ ሰነድ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ በመንግስት አካል ጥናት ተሰርቶ ከተዘጋጀ በኋላ ሁሉም ባለድርሻ አካል ከዚህ አገር አቀፍ መመርያ የየድርሻውን ይወስዳል ማለት ነው። ጤና ጥበቃ ለጤና መስማማቱን፤ መብራት ሃይል ለኤሌክትሪክ ዝርጋታ ምቹ መሆኑን፤…ወዘተረፈ እያለ ሁሉም የየራሱን ድርሻ ያስፈፅማል፡፡ ይህ አይነቱ ልዩ መመርያ ሁሉንም ሊያግባባ ይችላል። የጠፋውንም የለማውንም ለማወቅ ያለውን እድል አዳጋች አያደርገውም፡፡ በአጠቃላይ ይህን ለመስራት በየመስኩ ትክክለኛ ሰው ትክክለኛ ቦታ ላይ መቀመጥ አለበት፡፡ ብዙ ባዶ ወንበር አለ፤ አንዳንዱ ወንበር ሰው ቢቀመጥበትም ባዶ ነው፡፡ ትክክለኛ ውሳኔ የሚያሳልፍ አካል ያስፈልጋል፡፡ የመንግስት መሃንዲስና በግሉ የሚሰራ መሃንዲስ እውቀታቸው ቢለያይይም ቢመሳሰልም፣ ያላቸው የማስፈፀም አቅም ግን እኩል አይሆንም፡፡ መንግስት ህዝብን ስለሚያገለግል ከምህንድስናው ሚና መውጣት አለበት። ምርጥ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎችን አዋቅሮ የቁጥጥር፤ የምዝገባ እንዲሁም የዳኝነት ስራን ቢያከናውን የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ መንግስት ግንባታዎችን በራሱ ባለሙያዎች ለመስራት ከሚደክም በሌሎች ኩባንያዎች ተሰርተው ካለቁ በኋላ ብቃታቸውን እያረጋገጠ፣ እየመዘገበ  በካዝና ውስጥ የማስቀመጡን ሃላፊነት በመወጣት ቢሰራ፣ ከፍተኛ ለውጥ መፍጠር ይቻላል፡፡ በአንዳንድ መስርያ ቤቶች የምናያቸው የምህንድስና ክፍሎች አሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች በቂ ባለሙያ እንዳላቸው፤ በቂ መሳርያዎች እንደያዙ፤ በብቃታቸው ተወዳዳሪ መሆናቸው… ይህን መቆጣጠር ቀላል ስራ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ሰዓሊ የፈለገውን ይስላል፡፡ የስዕል ስራው አብስትራክት፣ ኪውቢክ ወይም ሪያሊስቲክ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያ ውስጥ የሆነ ሰው ሙዚየም ውስጥ አይቶት የምርጫውን ገዝቶ ሊወስድ ይችላል። እኔ አምራች ከሆንኩ ማከፋፈል የለብኝም። ገዢ ያስፈልገኛል፡፡ አገልግሎት ቢኖር ግን ወይም ገዢ አለ፡፡ የገዢው ሃሳብ አንተ ውስጥ መኖር አለበት፤ ልትጭንበት አትችልም። ስለዚህ ፍላጎትን ያማከለ ስራ እንዲሰራ ተወዳዳሪነት መፈጠር አለበት፡፡ ውድድሩም በተደላደለና ለሁሉም እኩል እድል በሚሰጥ ምህዳር መካሄድ ይኖርበታል፡፡ መሀንዲሶች ሁሉም ካንድ ትምህርት ቤት ከወጡ የሚለያቸው ፈተና ነው፡፡ ስለዚህ የማህበረሰቡ ፍላጎት ፈተና መሆን አለበት፡፡ መልሱ ደግሞ ከባለሙያው ይመጣል፡፡

Read 1873 times