Saturday, 27 October 2018 10:20

“የኛ ሃሳብ የሰዎችን ህይወት ማዳን ነው”

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(3 votes)


   በዓለማችን ላይ የሚገኙ ስኬታማ ሰዎች በሙሉ አንድ በጥናት የተረጋገጠ  የጋራ  ባህርይ አላቸው። እነሱ አምነውበት በርካቶች  አይሆንም ወይም አይሳካም ያሉትን የሥራ ፈጠራ ሃሳብ፤ በጽናትና በቁርጠኝነት ተግተው በመሥራት ለፍሬ  በማብቃት ይታወቃሉ። የዛሬ 10 ዓመት የግል አምቡላንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ መጀመር ይቻላል ብሎ  ማንም ያሰበ  አልነበረም፡፡ ከሃሳቡ ጠንሳሽና ከ”ጠብታ አምቡላንስ” መሥራች  ከአቶ ክብረት አበበ በስተቀር፡፡
እነሆ ጠብታ አምቡላንስ ላለፉት 10 ዓመታት የአምቡላንስና የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን ጉዞው በፈተናና በውጣ ውረድ የተሞላ ቢሆንም፣ ለ10ኛ ዓመት ከብረ በዓል መድረሳቸውን  የድርጅቱ  አመራሮች  ባለፈው ሳምንት በሂልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብስረዋል፡፡
“ባለፉት 10 ዓመታት ጠብታ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ስናጋራችሁ እጅግ ኩራት ይሰማናል” ብለዋል፤ አቶ ክብረት አበበ፡፡
ጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ከ60 ሺ በላይ ለሚሆኑ ድንገተኛ ጥሪዎች ምላሽ የሰጠ ሲሆን በኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ለመስጠትም ከ70 የቢዝነስ ተቋማት ጋር አጋርነት መሥርቶ እየሰራ እንደሚገኝ  ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በአገር ውስጥ ከ30 ሺ በላይ ለሚሆኑ ህሙማን የአምቡላንስ አገልግሎት የሰጠው ጠብታ፤ ከ500 በላይ ዓለም አቀፍ የህክምና ጉዞዎችንም እንዳመቻቸ ጠቁሟል፡፡
የጠብታ አምቡላንስ አመራሮች እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በመሰረታዊ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ብቻ አልተወሰነም፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን  የመንገድ ላይ ህክምና (paramedic) ኮሌጅ የከፈተ ሲሆን የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ማስተማሪያ ዲቪዲ  በአማርኛ አዘጋጅቶ አውጥቷል፡፡
በ2001 ዓ.ም በ3 አምቡላንሶች ብቻ አገልግሎቱን የጀመረው ድርጅቱ፤ በአሁኑ ወቅት የአምቡላንሶቹን ቁጥር 13 ያደረሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ዓለም አሁን እየተጠቀመባቸው የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ  ዘመናዊ አምቡላንሶች መሆናቸውን ሃላፊዎቹ  አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህ ዘመናዊ አምቡላንሶች መካከልም  አንደኛውን በሂልተን ሆቴል ለጋዜጠኞች አስጎብኝተዋል፡፡  
“ጠብታ አስተሳሰብ (ፍልስፍና) ነው፤ የኛ ሃሳብ የሰዎችን ህይወት ማዳን ነው” የሚሉት የድርጅቱ መሥራችና ባለቤት አቶ ክብረት አበበ፤”እያንዳንዱ ዜጋ የእኔ ጠብታ የታለ? ብሎ መጠየቅ አለበት” ይላሉ፡፡
የጠብታ መሥራች ከዚህ ቀደም ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አንጋፋው ድምጻዊ ጥላሁን ገሰሰ ለህልፈት የተዳረገው በድንገተኛ ህክምና አገልግሎት እጦት መሆኑን በመግለጽ፣ ጠብታ አምቡላንስ ቢኖር ኖሮ ህይወቱን ማትረፍ ይቻል እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል፡፡
“ደረጃውን የጠበቀ ቀልጣፋ የድንገተኛ ህክምና ባለመኖሩ የተነሳ በርካታ ሊድኑ የሚችሉ ህሙማን  እየገደልን ነው” የሚሉት አቶ ክብረት፤ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላትለድንገተኛ ህክምና ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

Read 4974 times