Saturday, 19 May 2012 10:37

እኔ ግን ወንድ ልጆቼን ትምህርት ሳይሆን ሴቶች እንዲገቧቸው እመርቃቸዋለሁ

Written by  ቢኒያም መንበረ-ወርቅ ni77@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

እጅ ዘርግቶ፤ ሃሳብ ሰብስቦ፤ ጣቶችን አጠፍ ዘርጋ እያደረጉ ‹አሜን›… ‹አሜን›… ‹አሜን›…‹ይሁን›… ‹ይሁን› ማለት… መኪናው እንዲንጋጋ፣ ሀብቱ እንዲንበሸበሽ፣ ዱኒያ እንዲሞላ፣ ሕይወት ስኬት በስኬት እንድትሆን… ሌላም ሌላም እንዲሆን፡፡ በፈጣሪ ለሚያምኑ ሰዎች፣ ምርቃን አንድ ሰው ለሌላኛው ሰው መልካም ይሆንለት ዘንድ ለ‹አምላክ› የሚቀርብ ማመልከቻ ነው፡፡ ህልውና-እግዜርን ‹ወፍ የለችም› ለሚሉም ምርቃን የመልካም  ምኞት መግለጫ ነው - ‘እንዲህ በሆነለት’ ብሎ አጥብቆ ከልብ መመኘት ዓይነት ነገር፡፡       አፍ ከፈታሁ፣ አእምሮዬም የንግግር ቋንቋ ምስጢር ከተገለጠለት፣ ‹ክፉውንና በጎውን በመለየትም ከእነሱ እንደ አንዱ› ከሆንኩ ወቅት አንስቶ ለሰጠሁት መልካም አገልግሎት ወይንም በሌላ ምክንያት በቁጥርም ሆነ በዓይነታቸው በርከት ያሉ ምርቃኖችን መገጨቴን አስታውሳለሁ፡፡ ‹ትምህርትህን ይግለጥልህ… ትምህርትህ ይግባህ› የምትለው ምርቃንም ተማሪ መሆኔን ተከትሎ በዛ ብላ ለኔ የደረሰችኝ የመልካም ምኞት መግለጫ እንደሆነችም እገምታለሁ፡፡ (ያው ‹ሀበሾች› መረጃ አያያዝና ስታትስቲክስ ላይ ጥሩ አይደለንም እንጂ ይህን ግምት ‹የተዥጎደጎዱልኝ የምርቃን ዓይነቶችና መጠናቸው› በሚል ርዕስ ስር በመቶኛና በግራፍ አስደግፌ ብገልጸው የበለጠ ተአማኒነትን ያተርፍልኝ ነበር፡፡)

ይህች ምርቃን በሕይወቴ ውስጥ ያመጣችውን ውጤት ነጥሎ ማስቀመጥ ባይቻልም  በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሆነ ዓይነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበራት አምናለሁ፡፡ ምክንያት፡- ምርቃን እጅግ ሲያንስ እንደ ትልቅ ማበረታቻ በመሆን… ከፍ ሲልም የእያንዳንዳችን መልካም ፍላጎት በሌላኛው ሰው ላይ መልካም ውጤት ያመጣ ዘንድ እርስበርሳችን በንቃተ-ኃይላችን መተሳሰራችንን ተከትሎ ምኞቱን ወደ ሆነ ዓይነት እገዛ በመቀየር… ከዚህ እጅግ ላቅ ሲልም የቀረበለትን ማመልከቻ የሰማ አምላክ በሕይወታችን ውስጥ አዎንታዊ ጣልቃ ገብነት እንዲፈጽም በማነሳሳት መሳጭ ሚና መጫወቷ ግልጽ ነውና፡፡ ተግባባን?..(ካልተግባባን የዚች አንቀጽ ጫፍ ላይ ወራጅ አለ… ከተስማሙ ተሳፋሪዎች ጋር ወደፊት!)      ከተመራቂነት ወደ መራቂነት እየተሸጋገርክ  ነው ብለው ሰዎች በነገር ሸንቆጥ በሚያደርጉኝ በዚህ ወቅት ላይ ሆኜ ‹ትምህርትህ ይግባህ› የምትለው ምርቃን ባትደርሰኝና ትምህርትም አሁን የገባኝን ያህል ሳይገባኝ ቢቀር ኖሮ ብዙም እንደማልጎዳ አሰብኩ፡፡ አሁን ከገባኝ የምርቃኗ ውጤት ተቀንሶ እንኳ ቢገባኝ ለኔ በቂዬ ነው፡፡ ጨርሶም ባይገባኝ ሌላ የሚገባኝ ነገር ፈልጌ እንጀራዬን ሌላ ቦታ አገኘው ይሆን ይሆናል፡፡

አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ምርቃን የተመራቂውን ፍላጎትና ጉድለት መሠረት ቢያደርግ ኖሮ ለኔ የምትገባኝ ምርቃን ‹ሴቶችን ይግለጥልህ… ሴቶች ይግቡህ› የምትሰኝ ትሆን ነበር… እዛ ጋ የአንድ የአራዳ ልጅ እጅ ይታየኛል … ከእጁ  አወጣጥ መገመት እንደሚቻለው የልጁ ጥያቄ ‹ቀዮ... እንዴት ነው የምታስቢው?› ዓይነት ነገር ነው፡፡ ጥያቄው ሳይገባቸው ‹ጥሩ ጥያቄ ነው› በሚሉ ሰዎች ‹ሰፊው ሕዝብ› እንደተማረረ እያወቅሁም ቢሆን ‹ጥሩ ጥያቄ ነው› ብዬ በመጀመር ለዚህ አራዳ የሚከተለውን መልስ ልስጠው…

እኔን ያፈራች፤ እትብቴንም አበስብሳ የመሬቷ አካል ያደረገች ውድ ከተማዬን ድሮ ድሮ በዙሪያዋ ከሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ለመለየት አሁን  ግን ማዶ ለማዶ የሚተያዩ ከተሜዎች በድልድይ ለሚሸጋገሯት ሸሌ ወንዝ ጀርባዋን ሰ[ጥ]ታ እንደ ነገሩ የተቀለሰች አነስ ያለች ቤት ነበረች፡፡ ልጆች በሚቦርቁባት፣ ህፃናት ከቋንቋ ተናጋሪነት ወደ ቋንቋ ጸሐፊነትና አንባቢነት ጭምር የሚሸጋገሩበት አስደማሚ ቤት ውስጥ ለመራመድ የማያግዛቸውን አንድ እግራቸውን ተክቶ የሚሠራው መቋሚያቸውን በብብታቸውና በመሬት መሐል ወጥረው ያንን ውጫጭ ሁሉ ‹ሀ….ሁ…› እያሉ ያስጮሁታል፡፡

ይች ቤት የአ’ይዋ ቤት፤ እሳቸው ደግሞ አ’ይዋ ይባላሉ… ትውስታዬ በትክክል ከነገረችኝ መደበኛ ስማቸው ኪሮስ ነው፡፡ ቁንጥጫና ግርፊያ አማሮኝ ከሳምንት በላይ ያልቆየሁባት የአ’ይዋ ‹Kindergarten› የመጀመሪያ ቀን ግንኙነቴ ተማሪው ሁሉ የሚቆጥራቸው ፊደላት ምን እንደሆኑ አልገባኝ ብለው… የሚገቡኝም አልመስል ብለውኝ ከዱላ ባላዳነኝ ጭንቀት መንዘፍዘፌን እገምታለሁ…

‹ወደ ሰባተኛ ክፍል ተሸጋግሯል› የሚል የትምህርት ማስረጃዬን ይዤ 7ኛ ኢ ክፍል (ይች ክፍል ምናልባትም ከቀለምነው ሁሉ (people of clour) በሀብት ብዛት የሚልቁትን ሰውዬ የማስተናገድ ታሪካዊ ዕድል ያላት መሆኗን ልብ ይሏል) ከተቀላቀልኩ በኋላ በሒሳብ ክፍለ-ጊዜ ከተለዋዋጮች (ቫርያብልስ) ጋር መሥራት በሚል ሰበብ ‹ቀ› እና ‹ሸ› ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ለተከታታይ ብዙ ዓመታት ከቁጥሮች ጋር ተቃቅፈው ከች የሚሉት እነዚህ ‹ቀ› እና ‹ሸ›ዎች (ኋላ ‘X’ እና ‘Y’ ሆነዋል) ገቡኝ ስል ሳይገቡኝ፣ ያወቅኋቸው ሲመስለኝ ሳላውቃቸው ትንግርት እንደሆኑብኝ ምሥጢር እንደሆኑብኝ ‹አጃኢብ› ስል ብዙ ክረምቶች አለፉ፤ ከተለዋዋጮች ጋር መሥራት ሳይሳካልኝ የጭንቀትና የውዝግብ ዓመታት ነጎዱ…

ከሰባት ዓመታት በፊት የእጅ ስልክ እንዳሁኑ በሰው ሁሉ ጓዳ ባልገባበት ወቅት የቤተ-ዘመዱን  ድምጽ ለመስማት ከአንድ ጓደኛዬ የእጅ ስልክ ተውሼ መደወል ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ ለመደወል አረንጓዴዋን ለማቋረጥ ደግሞ ቀይዋን ቁልፍ መጫን እንዳለብኝ ከማወቅ ውጭ ሌላ የማቀው ነገር አልነበረም፡፡ ምኑን እንደነካሁት ሳላውቅ ስልኩ ፒን ኮድ የሚል ባዶ ቦታ እንድሞላ ይሰጠኝ ጀመር፡፡ እኔ የዘመድ አዝማዱን ስልክ እየሞላሁ አረንጓዴዋን እጫናለሁ፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ ሙከራዎች በኋላ ግን ስልኩ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳይደለ ተገነዘብኩ፡፡ ‹ምን ነክቼ የሰው ስልክ አበላሸሁ ብዬ› መጨነቅ ጀመርኩ… የነካሁት፣ ያበላሸሁት፣ ፒንኮድስ ምን ይሆን? የሚል የያኔው ድንቁርናዬ የፈጠረብኝን እንቆቅልሽ ለመፍታት ለሰዓታት ታገልኩ…

አራዳው ጠያቂ፣ ቀደም ብለው የቀረቡት ሦስት አንቀጾች እርስበርሳቸውም ሆነ ከወሬው አጠቃላይ ሀሳብ ጋር በስቴፕለር ካልሆነ በቀር በስነ-አመክንዮ ፍሰት  አይያያዙም ብለህ እንዳትደመድም፡፡ መልሴ ይህ ነው፣ ለኔ እስካሁን የማውቃቸው ሴቶች -በተለይ እናትና እህት ያልሆኑት ሴቶች- የአ’ይዋ ቄስ ትምህርት ቤት ስገባ ያገኘኋቸው አስጨናቂዎቹ ፊደላት፣ ሰባተኛ ክፍል የገጠሙኝ ውስብስብ ‹ቀ› እና ‹ሸ›ዎች፣ ከስልኩ ሰሌዳ ላይ ያፈጠጡብኝ ‹የፒን ኮድ ክፍት ቦታዎች› ናቸውና  ይህን ያህል- ከዚህም እጅግ ከብዶ የሚሰማኝን ጉድለቴን ምርቃን ይሞላልኝ ዘንድ መፈለጌ ግር አያሰኝም!

እኔ እንዲህ በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ የሚሳካልኝ ሰው አይደለሁም፤ አሁንም ሴቶች አይገቡኝም የሚል ማጠቃለያ ላይ አልደረስኩም፡፡ ምንም እንኳ ያነበብኳቸው በጣት ከመቆጠር ያለፉ መጽሐፍት፣ ከሴቶች ጋር ያደረግኋቸው የተጠኑ ልምምዶችና ውይይቶች፣ ‹ሴቶችን እስከጥጋቸው እናቃለን› እያሉ ከሚኮፈሱ ወንዶች ያገኘኋቸው ምክሮች ሴቶችን ለመረዳት ያገዙኝ በትንሹ ብቻ ቢሆንም እኔ ግን ተስፋ አልቆርጥም፡፡

የመጽሐፍቱ ሀተታና ሊቀ-እንስት ነን የሚሉት ወንዶች ‹ትንታኔዎች› ሴቶችን እኔ ላከብራቸው በምፈልገው መጠን ለማክበር እንቅፋት የሚሆኑበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ከሴቶቹ ጋር በተደረጉ ውይይቶች የሚገኙት ሀሳቦችም በተግባር እውነት ሆነው የሚገኙት አልፎ አልፎ ብቻ ነው፡፡

ይህም ሆኖ እኔ ተስፋ አልቆርጥም… ቢያንስ እኔ ባይሳካልኝ እንዴት እንደምወልዳቸው የማላቃቸውን ወንድ ልጆቼን (ውጭ አገር የትልቅ ሰው ቤት ብቻ ሳይሆን ያልተወለዱ ልጆች ቤትም(ማኅፀን) እንደሚከራይ ማስታወስ ይገባል) ግን በምርቃኔ አግዛቸዋለሁ…. ‹ሴቶች ይገለጡላችሁ› እላቸዋለሁ፡፡ ሲያበሳጩኝም እረግማቸዋለሁ ‹ሴቶች ‹ቀ› እና ‹ሸ› ይሁንባችሁ› እያልኩ፡፡

ይህ አነጋገሬ ተስፋ የቆረጥኩ አስመሰለብኝ እንዴ?… ተስፋ አልቆርጥም ሴቶች ለኔ አንድና ያው የሆኑ የፋብሪካ ምርቶች አይደሉምና! … ይልቁንም ከመመሳሰላቸው ባልተናነሰ በርካታ የሚያነጣጥላቸው ነገር ያላቸው የራሳቸውን እድል በራሳቸው የሚወስኑ ግለሰቦች ስብስብ ናቸውና ተስፋ አልቆርጥም! ተስፋ አለኝ ተስፋ ሳልቆርጥ ትንፋሼ እንደሚቋረጥ…

 

 

Read 2659 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:42