Saturday, 27 October 2018 10:03

የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ በጥድፊያ?! - ሌላ ትውልድ “እንዳንገድል!”

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን - የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(5 votes)

    የዛሬ አንድ ዓመት ተኩል ገደማ “ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወይስ ከፍተኛ የዝርፊያ ተቋማት?” በሚል ርእስ አንዲት ጽሁፍ አዘጋጅቼ በጋዜጣም በኢንተርኔትም አሰራጭቻት ነበር፡፡ ጽሁፉን የተመለከተ አንድ የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ወንድሜ፤ “የትምህር ነገር አሳሳቢ ነው፤ አንተም የበኩልህን አስተያየት ሰንዝር” ከሚል መልእክት ጋር የትምሕርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ ጨመቅ (Executive Summary) ቅጅ ላከልኝ፡፡ ሰነዱ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በ“ከላይ ወደ ታች ዘይቤ” (top-down approach) ወርዶ፣ሰሞኑን በከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት መምሕራን “ውይይት” እየተደረገበት መሆኑ ይታወቃል፡፡
ፍኖተ ካርታውን እያነበብኩ ባለሁበት ወቅት ዮሐንስ ሰ. የተባለ ጸሐፊ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የመስከረም 19 ቀን 2011 እትም ላይ “ለተሳከረው የአገራችን ትምህርት መፍትሄው፣... ‘ከእውቀት የራቀ ትምህርት’ ነው?” በሚል ርእስ ያቀረበውን ጽሁፍ አየሁና እውነትም ይሄ ነገር ዝም ሊባል እንደማይገባው በማመን፣ይህቺን አስተያየት ለመከተብ ተነሳሁ፡፡
የዮሐንስ ሰ. ጽሁፍ ያተኮረው በፍኖተ ካርታው ላይ በቀረቡት ፍሬ ሃሳቦች ዙሪያ ነው፡፡ የእኔ ጽሁፍ ትኩረት የሚያደርገው ግን በፍኖተ ካርታው አዘገጃጀት፣ የቀረበበት ወቅት፣ በጥናቱ ተሳታፊዎችና አጠናኑ ላይ ያለውን አንደምታ በተመለከተ ይሆናል፡፡ለመንደርደሪያ ይሆን ዘንድ ከዮሐንስ ጽሑፍ የተወሰኑ ነጥቦችን ልጥቀስ፡፡
“ለተሳከረው የአገራችን ትምህርት መፍትሄው ‘ከእውቀት የራቀ ትምህርት’ ነው?” የሚለው ርእስ ግራ እንደሚያጋባ የተረዳው የአዲስ አድማሱ ጸሐፊ ዮሐንስ ሰ.፤ አእምሯችን መልስ ፍለጋ እንዳይባዝን በማሰብ፤ “ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ (ማለትም 50%)፣ አንዲት አጭር ዓረፍተ ነገር አንብበው ለመገንዘብ የሚያስችል እውቀት የላቸውም። ሩብ (25%) ያህሉ ደግሞ አንዲትም ቃል ማንበብ አይችሉም። [ይህ] ውድቀት… በእጣ ፋንታ ሰበብ የወረደ ክፉ መዓት፣ ባልታወቀ ፍጡር የተወረወረ እርግማን አይደለም… ‘ከእውቀት የራቀ የማወቅ ክህሎትን እናስተምራለን’ በሚል የተሳከረ አስተሳሰብ የተቃኘ ትምህርት... ” ውጤት መሆኑን ይነግረናል፡፡
ዝቅ ብሎ ደግሞ “እውቀትን ማስጨበጥ ሳይሆን ሙያን ማስተማር... ነው የትምህርት ዓላማ... [ይላል ፖሊሲው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ] ያለ እውቀት የህክምና ሙያ፣ ያለ እውቀት የምህንድስናም ሆነ የአናፂነት ሙያ… [እንደሚኖር ማሰብ ነው]…” በማለት በአጥኚዎቹ ላይ ይሳለቃል ዮሐንስ፡፡
የአዲስ አድማስ ጸሐፊ ዮሐንስ ሰ. ቀዳሚው የትምህርት ፖሊሲ፤ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት… እንደማይችሉ አዲሱ ፍኖተ ካርታ በጥናት ማረጋገጡን በ“ፀፀት” ከነገረን በኋላ፤ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ራሱ የቋንቋ ሰዋሰው መፋለስ የታጨቀበት መሆኑን በ“ስላቅ” ያመላክተናል፡፡ ዮሐንስ ሰ. ያልነገረን በሰዋሰው ስህተቶች የተሞላውን ሰነድ ካዘጋጁት “አጥኝዎች” ውስጥ ማንበብና መጻፍ፣ መደመርና ማባዛት… “የማይችሉት” የአዲሱ ትምህርት ፖሊሲ ውጤቶች መሳተፍ አለመሳተፋቸውን ነው፡፡
ላለፉት 25 ዓመታት አገልግሎት ላይ የዋለው የሀገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ፤ ሀገሪቱ ህገ መንግስት እንኳ ሳይኖራት፣ የምትመራበት ርዕዮተ-ዓለም ምን እንደሆነ በቅጡ ሳይታወቅ፣ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላትና በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በአግባቡ ሳይመክሩበትና ምርጫ ተካሂዶ ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት በይድረስ ይድረስ፣ የአንድን የፖለቲካ ቡድን ፍላጎት ማዕከል አድርጎ፣ ይሁንታ (mandate) በሌለው አካል የተዘጋጀ ነበር፡፡
ሰሞኑን የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው ፍኖተ ካርታም ከቀዳሚው የተለየ ሆኖ የቀረበ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት ህገ መንግስትና በምርጫ የቆመ መንግስት ቢኖርም፤“ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ ሀገሪቱ በቄሮና በፋኖ በምትታመስበት፣ በለውጥ ማዕበል በምትናጥበት፣ የፌስቡክ ቱማታ በጦፈበት፣ እዚህም እዚያም ህዝብ በሚፈናቀልበት፣ አሁን ያለው ህገ መንግስት እጣ ፋንታ ከመጪው ምርጫ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል ባልታወቀበት፣ ዜጎች ተረጋግተው በማያስቡበት… በዚህ ወቅት የመጪውን ትውልድ መፃዒ ዕድል የሚወስን የትምህርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅቶ፤ የይስሙላ ውይይት አድርጎ በማጽደቅ ለትግበራ መቻኮል ፋይዳውንም ሆነ ዓላማውን የሚያውቁት ትምህርት ሚኒስቴርና የሰነዱ አዘጋጆች ብቻ ናቸው፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት ትምህርት ለሁሉም የሀገሪቱ ህፃናት ተደራሽ ባለመሆኑና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ባለመቻሉ አራት ክፍሎች ያሉት “የትምህርትና የስልጠና ችግሮችንና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን…” የያዘ 84 ገፆች ያሉት ፍኖተ ካርታ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ስትራቴጂክ ማዕከል መሰናዳቱን አዲሱ ሰነድ መግቢያው ላይ ይነግረናል፡፡
ይህ ሰነድ የሃሳብ መጣረሱን የሚጀምረው ገና መግቢያው ላይ “… በሁሉም ዘርፎች… በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ አመርቂ ውጤቶችም ተመዝግበዋል…” በማለት ነው፡፡ ይህ አባባል “ታዲያ አመርቂ ውጤት ያስገኘ ፖሊሲ ተቀዶ ተጥሎ በሌላ እንዲተካ ለምን ጊዜና ጉልበት፣ ሀብትና ንብረት ይባክናል?” የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡
በነባሩ የትምህርት ፖሊሲ ተምረው ከሚመረቁ ወጣቶች ብዙዎቹ “garbage in garbage out” ዓይነት የመከኑ፣ እውቀት አልባ፣ ስማቸውን እንኳ በትክክለኛ ፊደል አስተካክለው መጻፍ የተሳናቸው መሆናቸውን ያስተዋሉ ሰዎችንና ከጅምሩ “ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው” በማለት ሲናገሩ ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ አስተያየቱን እንደ “ሟርት”፣ ትችቱን እንደ “የጠላት ወሬ” ሲቆጥር የነበረው ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ እንደ አዲስ ግኝት የፖሊሲውን የድክመት መርዶ ሊነግረን መነሳቱ ቢያስገርመንም ከዚህም በላይ አለመዘግየቱ ያስመሰግነዋል ባይ ነኝ፡፡
ፍኖተ ካርታው ለሦስት ዓመታት፣ በ36 “ዋና አጥኝዎች” እና በ73 “ረዳት አጥኝዎች” 15 ሺህ ሰዎች መረጃ በመስጠት ተሳትፈውበት የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ፤ ጥናቱን ያካሄዱት ሰዎች እነማን ናቸው? ከትምህርት ጋር ተያያዥነት ያለው ሙያዊ ብቃት አላቸው? ለጥናቱ መረጃ እንዲሰጡ የተመረጡት ሰዎች (የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ኘሬዝዳንቶች፣ የዞንና የወረዳ የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣…) ምን ያህል ተዓማኒነት ያለው መረጃ ይሰጣሉ? 100 ሚሊዮን ህዝብ ባላት ሀገር የ15 ሺህ ሰዎችን አስተያየት ወስዶ ጥናት ማካሄድስ ፖሊሲ ለመቅረጽ የሚያስችል ወካይ ናሙና ሊሆን ይችላል? “ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ ነው” ይሉ የነበሩት ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችስ የጥናቱ አካል ነበሩ? የሚሉት ጥያቄዎች በቂ ማብራሪያ ይፈልጋሉ፡፡
እንደኔ እንደኔ ቁም ነገሩ “ምርጥ” ፍኖተ ካርታና “ምርጥ” ፖሊሲ ማውጣት ብቻ አይደለም፡፡ የተማሪ ቁጥር ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የተሻለ መሆኑ የተነገረለትን “ምርጥ” ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚሆን እውቀትና ይህንን መሸከም የሚችል የፋይናንስ አቅም አለ? ቴክኒካዊ አቅምስ ማሟላት ይቻላል?
የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ “ጥራት ያለው ፖሊሲ” ማዘጋጀት አንዱ ግብዓት ይሆናል እንጂ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ስለ ትምህርት ጥራት ስናወራ ቀዳሚውና ዋነኛው ግብዓት ደግሞ ጥራትና ብቃት ያለው መምህር ነው፡፡ እስከዛሬ የመጣንበት የመምህራን የቅጥር ሁኔታ በብቃት ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ባለው አመለካከትና ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ባለሙያ፤ አይረቤነቱ በተነገረለት ፖሊሲ ተምሮ ወደ ስራ የተሰማራ ነው፡፡ እናም እነዚህ የመከነው ፖሊሲ ውጤቶች፣ አዲስ እየተዘጋጀ ያለውን ፖሊሲ የማስፈጸም ብቃት አላቸው ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡
በተሽመደመደ ፖሊሲ ተምሮ፣ በወገንተኛ የቅጥር ስርዓት ተቀጥሮ “garbage in garbage out” ዓይነት ስማቸውን አስተካክለው መጻፍ የማይችሉ ተማሪዎችን ሲያመርት የነበረ፣ ራሱ የመከነ የመምህራን ሰራዊት ሀገሪቱን ወደ 22ኛው ክፍለ ዘመን ማሸጋገር የሚችል ትውልድ ማፍራት ይችላል ብሎ ማሰብ ራሱ ከንቱነት ነው፡፡ ያልበቃ አብቂ፣ ያልሰለጠነ አሰልጣኝ ከመሰኘት የዘለለ ፋይዳ ያለው ሆኖ አይታየኝም፡፡
ይህቺን አስተያየት ለመጻፍ ስነሳ ያነጋገርኳቸው በትምህርት ሙያ መስክ ለረዥም ዓመታት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማለትም በዩኒቨርሲቲ ከ30 ዓመት በላይ ያስተማሩ ምሁራን “ለመሆኑ ሀገሪቱ የትምህርት ፍልስፍና አላት ወይ? ካለ ፍልስፍናችን ምን ነበር?” የሚሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡
ቀደም ባሉት ጊዜያት ምን ዓይነት የትምህርት ፍልስፍና እንደነበር አላውቅም፡፡ በአዲሱ ፍኖተ ካርታ ላይ ግን “(1) ዜጐች በራሳቸው የሚተማመኑ፥ ብቁና በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፥ በሙያቸው ብቃት ያላቸው በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ አድርጐ አጠቃላይ ሰብእናቸውን መገንባት፤ (2) ሥራ ፈጣሪዎች፥ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፥ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረ ገባዊ እሴቶችን የተላበሱና ለሕግ ዘብ የቆሙ ዜጐችን ማፍራት (3) ብዝሃነትን ላካተተው አገራዊ አንድነትና ሠላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ” የሚሉ ሦስት የትምህርት ፍልስፍናዎችን ያስቀምጣል፡፡
እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ “ይህ የትምህርት ፍልስፍና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ራዕያችንና ከህገ መንግስታዊ ግባችን ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ?” የሚል ነው፡፡ እኔ እንደሚገባኝ (በህገ መንግስታችን ላይ እንደተቀመጠው) ሀገራዊ ግባችን “አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር” ይመስለኛል። ታዲያ በፍኖተ ካርታው ላይ የተቀመጡት፣ ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው የትምህርት ፍልስፍናዎች ሀገራዊ ግባችንን እውን ከማድረግ አኳያ የተቃኙ ናቸው? ይህም መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡
የሀገራችን የትምህርት ስርዓት በየወቅቱ የነበሩ መሪዎችን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእነርሱን ወዳጅ ሀገራት ፖሊሲዎች በአርኣያነት በመውሰድ የተቀረፁ መሆናቸውን ወደ ኋላ ተመልሶ ማየት ይቻላል። በምኒልክ ዘመን የተጀመረው ዘመናዊ ትምህርት የአውሮፓን የትምህርት ስርዓት የተከተለ ነበር፡፡ ብዙዎቹ መምህራንና የማስተማሪያ መጽሐፍት ጭምር ከአውሮፓ የመጡ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በአምስቱ ዓመት የወረራ ዘመን ደግሞ የጣሊያኖቹን አስኮላ የሚመስል የትምህርት አሰጣጥ ተጀምሮ ነበር፡፡
የጣሊያን ወረራ በሀገሪቱ ማቆጥቆጥ ጀምሮ የነበረውን ዘመናዊ ትምሕርት ሙሉ በሙሉ አዳፍኖት ነበር፡፡ በጣሊያን ወረራ ወቅት ትምሕርት ቤቶችና የትምሕርት መሣሪያዎች በመውደማቸው፣ በጊዜው የነበሩ ጥቂት መምሕራን በጦርነቱ ምክንያት በመሰደዳቸውና በመሞታቸው 4,200 ያህል ተማሪዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲበተኑ በመደረጉ በጥቂቱም ቢሆን የነበረው የዘመናዊ ትምሕርት ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ በመጨለሙ ከድል በኋላ ከባዶ መጀመር ግድ ሆኖ ነበር፡፡
የጣሊያን ወራሪ ኃይል ተወግዶ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የትምሕርት ስርዓት እንደ ቀድሞው ሁሉ ከምዕራባዊያን ተጽዕኖ ነጻ አልነበረም:: የየካቲቱን ሕዝባዊ አብዮት ተከትሎ የአብዮቱ የእንግዴ ልጅ የነበረው ግራ ዘመሙ ወታደራዊ ጁንታ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ የትምሕርት ዘርፉ ማርክሲስት ሌኒኒስት መሽተት ጀመረ:: በዚያ ወቅት በትምህርት ስርዓቱ አማካይነት “ሶሻሊስት አርበኞችን” ለማፍራት ብዙ የተደከመ ይመስለኛል፡፡ እኔም የዚያ ፖሊሲ ውጤት ነኝ፡፡
ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ስልጣን ሲጨብጥ (ገና በሽግግሩ ዘመን) ኢህአዴግ ከዘመተባቸው ተቋማት አንዱ የትምህርት ሴክተር ነው፡፡ ገና ህገ መንግስት ሳይረቀቅ፣ ምርጫ ተካሂዶ ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት ያገባናል የሚሉ ኃይሎች ጥሪ ተደርጎላቸው ሳይመክሩበት በጥድፊያ አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ወጥቶ ሥራ ላይ ዋለ፡፡
በወቅቱ 120 ሺህ መምህራን የመረጡት እድሜ ጠገብ የመምህራን ማህበር ፈርሶ ለስርዓቱ ታዛዥ የሆነ የመምህራን ማህበር ተቋቁሞ፣ ከትምሕርት ሚኒስቴርና መሰል የመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት የፖሊሲው መሀንዲስ ሲሆን፤ ያኔውኑ “ይህ ፖሊሲ ትውልድ ገዳይ ነው” የሚሉ ኃይሎች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ፡፡ አሁን ደግሞ ያ ፖሊሲ ጉድለት እንዳለው ታምኖ አዲስ ሰነድ ተዘጋጀ፡፡
የያኔውን ፖሊሲ አሁን እየተዘጋጀ ካለው ጋር የሚያመሳስላቸው መሰረታዊ ነገር፣ የያኔው ቋሚ መንግስት ሳይመሰረት በሽግግር ወቅት ተዘጋጀ፡፡ አሁንም የሰከነ አእምሮ በሌለበት፣ የፖለቲካ መረጋጋት ባልተፈጠረበት፣ ህዝብ በሰፊው በሚፈናቀልበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች መማር ማስተማር ባልተጀመረበት የለውጥ ሂደት ላይ እያለን ነው ይህ ሰነድ ብቅ ያለው፡፡
እዚህ ላይ ቀዳሚው ጥያቄዬ፣ ይህ ያልተረጋጋ ወቅት አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ለማውጣት ለምን ተመረጠ? የሚል ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ፍላጎትና ራዕይ ብቻ የሚያንጸባርቅ የትምህርት ፖሊሲ ማውጣት ለምን አስፈለገ? የሚል ተጨማሪ ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡
የትምህርት ፖሊሲ የአንድን ሀገር ዜጎች ሁሉ የሚመለከት፣ ለሀገሪቱ ውድቀትም ሆነ እድገት ወሳኝነት ያለው ጉዳይ በመሆኑ የሚመለከታቸው ሁሉ ሊመክሩበትና ሊዘክሩበት ይገባል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ በመምሕራን ለመምሕራን የቆመ የመምህራን ማህበርና ሌሎች የሙያ ማህበራት፣ ተማሪዎችና ወላጆች በዋናነት ሊወያዩበት ይገባል፡፡
አዲሱ የትምሕርት ፖሊሲ ማሻሻያ ፍኖተ-ካርታ፤ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ሁሉ የተወያዩበትና ያዳበሩት ካልሆነ፣ እንዳለፉት 25 ዓመታት ማዶ ለማዶ እየተያዩ አንዱ “ትውልድ ገዳይ ነው” ሲል፣ ሌላው “ለብሔር ብሔረሰቦች ተደራሽ የሆነ የሊቃውንት ማፍሪያ ነው” እያለ ሲመጻደቅ ተጨማሪ ፍሬ-አልባ ዓመታት ይቆጠራሉ የሚል ስጋት አድሮብኛል፡፡ እናም ጥድፊያውን እናቁም - ሌላ ትውልድ እንዳንገድል እላለሁ፡፡





Read 2724 times