Saturday, 20 October 2018 14:16

“ኢትዮጵያ ሪድስ” ከ55 ሺ በላይ የህፃናት መፅሐፍትን ለት/ቤቶች ለገሰ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 22 ዓይነት አዳዲስ መፅሐፍትን አሳትሞ አስመርቋል


     ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ሚኒሶታ ያደረገውና እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተመሰረተው “ኢትዮጵያ ሪድስ” (ኢትዮጵያ ታንብብ) የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት ያሳተማቸውን 22 ዓይነት አዳዲስ መጽሐፍት ባለፈው ማክሰኞ በወመዘክር ያስመረቀ ሲሆን ከ55 ሺህ በላይ የህፃናት መፅሐፍትንም ለት/ቤቶች መለገሱ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ መጽሐፍቱን በአዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደርና ሀዋሳ ለሚገኙ ከ100 በላይ  የመንግስት ት/ቤቶች የለገሰ ሲሆን እያንዳንዱ ት/ቤትም ከ400 በላይ መፅሐፍት ማግኘቱ ተጠቁሟል፡፡
 የ”ኢትዮጵያ ሪድስ” ካንትሪ ዳይሬክተር ወ/ሪት የምስራች ወርቁ እንደገለጹት፤ድርጅቱ ባለፉት 15 ዓመታት በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ከ70 በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ቤተ-መፃሕፍትን በማቋቋም አብሮ ሲሰራ የቆየ ሲሆን እስካሁንም ከመቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች የትምህርት ቤት ማህበረሰብ በተለያዩ ትምህርትና ንባብ ተኮር ፕሮግራሞች ላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡  በመፅሐፍቱ ምረቃ ላይ ንግግር ያደረጉት ወ/ሪት የምስራች፤ የተመረቁት 22 ዓይነት የህፃናት መፅሐፍት በሰባት የአገራችን ቋንቋዎች የተዘጋጁና በአገራችን አባባሎችና ተረቶች ላይ መነሻቸውን አድርገው፣ በስዕላዊ ገለፃ የታጀቡ ሲሆን በመፅሐፍቱ ሽፋን ላይ የተቀመጡት ስዕሎችም በህፃናት የተሳሉና በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ሆነው የተሰናዱ ናቸው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ንባብን እንዲላመዱ በማሰብም፤ በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በከምባትኛ፣ በጠምባርኛና በዲዚኛ (ጋምቤላ) ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሲሆን በቀጣይም እንደ አመቺነቱ በሌሎች ቋንቋዎች ለማሳተም ዕቅድ  እንዳለ ተገልጿል፡፡
ከከተማ በጣም ርቀው በሚገኙ የደቡብ አካባቢዎች የራሱን ት/ቤት በመክፈትም አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች በማስተማር፣ በት/ቤት ምገባ፣ ለመምህራን ስልጠናና የትምህርት እድል ሲሰጥ መቆየቱ የተነገረለት ድርጅቱ፤በሰውና በፈረስ ጉልበት የሚንቀሳቀሱ ቤተ-መፃሕፍት በማመቻቸት፣ የንባብ ባህል ለማዳበርና አገር ተረካቢ ህፃናትን በማነፅ እንዲሁም በትምህርት ጥራት ላይ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ሞክሯል ተብሏል፡፡
“ኢትዮጵያ ሪድስ” ካሳተማቸው 22  መፅሐፍት መካከልም፤ “ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለች”፣ “ድር ቢያብር” ፣ “ማሞ ቂሎ” ፣ “ተክሌ” ፣ “ደፋሩ አይጥ” ፣ “የጎንደር ከተማ ክብርና ዝና”፣ “50 ሎሚ” እና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡
ድርጅቱ መፅሐፍቱን መለገስ ብቻ ሳይሆን መምህራን፣ የቤተ መፃህፍት ባለሙያዎችና ወላጆች ለልጆቻቸው መፅሐፍቱን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ መፅሐፍቱ በተመረቁበት እለትም በአዲስ አበባ የሚገኙ የመፅሐፍት ልገሳው ተጠቃሚ ት/ቤት መምህራን፣ የቤተ መጻህፍት ባለሙያዎችና ወላጆች በባለሙያዎች ስልጠና አግኝተዋል፡፡ በተጨማሪም ደራሲና ገጣሚ ይታገሱ ጌትነት፤ የመፅሐፍቱ ይዘት ከህፃናት ስነ ልቦና፣ የመረዳት አቅም፣ የቋንቋና የስዕል ሁኔታ አንፃር ግምገማ አድርገው፣ ለህፃናት ተስማሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

Read 4342 times