Saturday, 19 May 2012 10:26

ኪሎ = ቀለም (ቀለም ማለት ሰው ነው)

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

… ከየት እንደምጀምር ስላላወቅሁኝ … “ከየትም መጀመር ይቻላል ማለት ነው አልኩኝ፤ ለራሴ፡፡ ሰማይን ወርቅማ ቀለም ቀባ ብባል ከየት እጀምራለሁ? … የትስ እጨርሳለሁ? … አምስት ሺ ቀለማት አሉት ብያለሁ … ባንዲራው፡፡ የቀለሙ ብዛት አምስት ሺም ቢሆን መነሻውግን ሶስት መሰረታዊ ቀለማት ናቸው፡፡ህይወት፣ ሞት እና ሰው፡፡ መልካም፣ እኩይ እና ሰው፡፡ መሆን፣ አለመሆን እና ሰው፡፡ እውነት፣ ውሸት እና ሰው፡፡ ውበት፣ እውቀት እና ሰው፣ የቀድሞው፣ የሚመጣውና ሰው፣ እግዜር ሰይጣን እና ሰው፣ ደስታ ሀዘን እና ሰው…

ሁሉም ጋር ሰው አለ፡፡ ስለዚህ የአምስት ኪሎ በአምስት ሺ ቀለማት የተጨማለቀውን ባንዲራ “ሰው”ን በመግለፅ ለምን አልጀምርም፡፡ … አንባቢ ሆይ! የማደርገውን ለማድረግ የአንተን ፈቃድ እየጠየቅሁ አይደለም … ፈቃዴን እየፈፀምኩ እንጂ…!

“መጀመሪያ ጥበበኛ (አርቲስት) ከመሆንህ በፊት ሰው መሆን መቻል አለብህ” ደጋግሞ ይላላ አንድ በዚሁ ቦታ ላይ የሚገኝ ሰአሊ፡፡ ምን ማለቱ እንደሆነ በሩቅ ጠረኑ እንጂ በተጨባጭ አልተረዳሁትም፡ ግን የሆነ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ይመስላል፤ አባባሉ፡፡ ሰው በህይወት ሲኖር ህያው ሰው ይባላል፡፡ አልያም የሞተ ሰው፡፡

መልካም ሰው፣ እኩይ ሰው…

… መሆን የቻለ ሰው፣ አለመሆን ያልቻለ ሰው … መሆን እየቻለ ሳይሆን የቀረ ሰው፣ ውበት ያለው ሰው፣ እውቀት ያለው ሰው፣ እውቀት እያለው ውበት የራቀው ሰው፣ ውበት ማየት እንጂ መፍጠር የማይችል ሰው፣ ውበትን መፍጠር እንጂ መውደድ የማይችል (የማይወድ) ሰው …. (ፍቅርን ባልጋ መስራት እንጂ መገንዘብ የማይችል ሰው)

እንግዲህ እንዲህ እያሉ ነው፣ ቀለማቱ የሚደባቀሉት … የሚዘባረቁት፤ እንዲህ እያለ ነው፤ ከሦስት ቀለም አንድ እና ሦስትነት … ወደ አንድ አለመሆን… እና ብዙ ልዩነት የሚለወጡት፡፡ የእኔ አላማ ግን ሁልጊዜም መለያየት ሳይሆን ማገናኘት ነው፡፡ መበተን ሳይሆን መሰብሰብ፡፡

እና ወጣቱ ሰአሊ “ሰው መሆን መቻል መጀመሪያ አለብህ” ሲል እሱም መሰብሰብ በመሻት መሆኑ ይሰማኛል፡፡

ለእሱ (ምናልባት ለብዙዎቻችንም) ሰው ማለት፡- ከሞት ህይወትን፣ ከውሸት እውነትን፣ ከሰይጣን እግዜርን፣ ከሀዘን ደስታን … ወዘተ የመረጠ ማለት ነው፡፡ “ሰው” በሚል መግባቢያ የምንደጋግማት ተንሳፋፊ ሀሳብ የምትፈጥረው ጠረን “እንዲህ ነው ብለን” በአፍንጫችን ንፅህናን ሞልተን ወደ እውነተኛው አለም እንወጣለን፡፡

በመንገድ ላይ ለማኝ የሆነ ሰው እናያለን … ሰው ደስተኛ ብቻ ሳይሆን ሀዘንተኛም ይሆናል እንላለን … ንፁህዋ ጠረን ላይ ሀዘን ሲደባለቅ የሆነ ውህድ ትፈጥራለች፡፡ ንፁህ ድንግልናዋን ያጣች ግን በማጣቷ እውቀት የጨመረች ጠረን፡፡ እዚህችው ጠረን ላይ አንድ እኩይ ጨምሩባት … አንድ እውቀት እየጨመራችሁ አንድ የዋህነት እያፈረሳችሁ … አንድ የቀድሞውን እየሻራችሁ … አንድ የሚመጣውን እየሆናችሁ … ብዙ ዘመን ትኖራላችሁ፡፡ … በኑሮ እና በእውቀት ብዛት የዋህነት ሙሉ ለሙሉ የተወገደ ሲመስላችሁ፣ ራሳችሁን አዋቂ ትሉና  … ሌሎችን ለማሳወቅ ሁሉ ትሰማራላችሁ፡፡ … ግን ያልተረዳችሁት ነገር፤ አሁንም ያ “ንፅህና” እንደማይለቅ በሽታ በውስጣችሁ መቅረቱን ነው፡፡ መቅረቱን እና ልታስወግዱት አለመቻላችሁን ስትረዱ፤ ያኔ ጥበበኛ ወይንም አርቲስት ሆናችሁ ራሳችሁን ታገኙታላችሁ፡፡ ራሳችሁን ያገኛችሁበት ቦታ አምስት ኪሎ ነው እንበል፡፡ እናንተን የመሰሉ የዋህነታቸውን ሊረሱ ካልቻሉ ብዙ ሌሎች ሰዎች (ቀለሞች) መሀል፡፡

በእውነታ ተጨባጭ ግዛት ላይ ንፅህናን ለመያዝ የሚሞክር … ጀዝባ ነው፡፡

በአምስት ኪሎ የሚገኘው ጀዝባ ሁለት አይነት ነው፡፡ ወደ ህይወት በተስፋ የሚያይ እና፣ ህይወትን ላለማየት ሲል ሁሉንም ተቃራኒ አቅጣጫ በቁጣ እየገላመጠ “የሚነድደው” አይነት ናቸው፡ … በህይወት ተበሳጭቶ፤ ህይወት ላይ ለመትፋት በሚያደርገው ሙከራ … ከሞት ጋር አይነ ለአይን ይገጣጠማል፡፡ … ሞት ደግሞ አይን ለአይን ተገጣጥመኸው…እና… አንዴ ፈገግ ብሎ ካየህ … መልሰህ ፈገግ አለማለት … አይቻልም፡፡ ስቆ ያስቅሀል፡፡ ከሞት ጋር አብሮ የሳቀ በህይወት ሊቆይ አይችልም፡፡

የአምስት ኪሎ የጀዝባ ህይወት፤ የሞትን ፈገግታ አይቶ መልሶ ፈገግ ላለማለት የሚደረግ መፍጨርጨር ነው፡፡ ተኮርኩረህ ላለመሳቅ እንደመሞከር … በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ምንም እይታን ወደ ህይወት ለማዞር ራሱን የጣለው ጀዝባ ይኖራል፡፡ ግን ህይወት ከጀዝባው እይታ ተሰውራለች፡፡ በሌላ ሰው እርዳታ እንጂ ከእንግዲህ በራሱ ጥረት ለማግኘት ይቸግረዋል፡፡

ህይወቱ የተሰወረበት ጀዝባ ሁለት አማራጭ ይኖረዋል፡፡ አንደኛው አማራጭ ከባድ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቀላል ነው፡፡ ቀላሉ የህይወት መልክ ጠፍቶበት በሱስ ተጐድቶ … ተጐሳቁሎ “ቀጥኖ እና ረዝሞ” ከብዙ ትግል በኋላ ፈገግ ላለው ሞት ፈገግታውን ሰጥቶ ተገላግሎ መሞት ሲሆን … ሌላኛው ደግሞ በፍቅር አማካኝነት መዳን ነው፡፡ መዳን ከባድ ነው፡፡ ፍቅር ስል፣ የፆታ ብቻ ሳይሆን፣ የአላማ፣ የፈጣሪ፣ የወላጅ … የትኛውም ከውጭ ወደ ጠፋው (ሻማ) ሰው የሚገባ ፍቅር … የጠፋበትን ህይወት በአዲስ ተስፋ እንዲያገኝ ያደርገዋል፡ … ከጠቀስኳቸው የፍቅር አይነቶች … ቀላሉ እና አርቴፊሻል አይነቱ ፍቅር … የገንዘብ/ወይ በገንዘብ የሚገኝ ፍቅር ነው፡፡ … በገንዘብ አማካኝነት የሚገኝ የሙሉነት መንፈስ (ፍቅር) ገንዘቡ ሲያልቅ ያልቃል፡፡ አርቴፊሻል ፍቅር የጋረደው እውነት/እውነታ ሲገለጥ ለተጭበረበረው ሰው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ደማቅ ከመሆኑ የተነሣ ሞት… እስኪስቅለት እንኳን አያስጠብቀውም … ተጐጂው ሞትን ፈልጐ ኮርኩሮ ስቆ እንዲያስቀው ያደርገዋል፡፡

ሁሉም ጥበብ አላማው ፍቅርን መግለፅ ወይንም መሆን ነው፡፡ ፍቅር ከሌለበት ሁኔታ ውስጥ የመጀመሪያን ያልተበረዘ የየዋህነት ጠረን በከፍተኛ ደረጃ አልሞ ለመፍጠር መሞከር… ትልቁ እና ከባዱ የስራ ድርሻ ነው፡፡ ትልቁ ብቻ ሳይሆን (ለኔ ደግሞ) ብቸኛው፡፡

ጥበብም መንፈስን መመገብ ብቻ ሳይሆን … ሰው ልጅ በህይወት እንዲቆይ የሚያደርገው ብቸኛ መድሐኒቱ ነው፡፡ ህልሙን የሚወጋው ሀኪም ካላገኘ ተጨባጩ ህልውናው በህይወት አይቆይም፡፡

ግን ጥበበኛው እንደ ናይቲንጌል (thorn bird) ከህመም ነው ፍቅርን የሚፈጥረው፡፡ አለም ላይ ያለ አስቀሚያነትን በማቅለጥ አለም ላይ ያለ ውበትን ይፈጥራል፡፡ እንደ ስራው አይነት/ባህርይ … ሰራተኛው ላይ አደጋ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡

ለምሳሌ የህክምና ባለሞያዋ ከሚያክመው ሰው በሽታ ሊጋባበት ይችላል፡፡ (Occupational Hazard) ይባላል፡፡ ሴተኛ አዳሪነትን ስራ አድርጋ የያዘች በአባላዘር በሽታ ልትጠቃ ትችላለች፡፡ ወታደር በጥይት የመመታት እድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡

… ጥበበኛውም ከቁሻሻ ውስጥ ውበትን አንጥሮ መርጦ ለማውጣት ሲዳክር ቁሻሻው ውጦት ሲቀር ይታያል፡፡ በመጠጥ ሱስ፣ በህመም ሱስ፣ በድህነት፣ በፍቅር እጦት … ሊጐዳ እና ለውበት የከፈተውን አይን … ከአስቀያሚነት በተሰነዘረ ተስፋ መቁረጫ ብርሀኑን ሊያሳጣው ይችላል፡፡ … ለሰው አጠራቅሞ፣ አውጥቶ የሚሰጠውን የብርሀን ፍቅር … ከውጭ የሚተካለት ይፈልጋል፡፡ ከውጭ የሚሰጠው ፍቅር … የመፈለግ ስሜት አክብሮት… ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡

***

… የእሾኳ ወፍ ዜማውን ለማውጣት ዝግጁ ስትሆን ሹል ከሆነው እሾክ ላይ አንገቷን አስደግፋ መዘመር ትጀምራለች፡፡ እሾኩ አንገቷን እየተጫነ በመጣ ቁጥር ዜማዋ እያማረ ይሄድና … በስተመጨረሻ እሾኩ ጉሮሮዋን በስቷት ሲገባ ወፏም ትሞታለች፤ ዘፈኑም ይጠናቀቃል፡፡

ክርስቶስም ትልቁን ፍቅሩን የገለፀባቸው ሰአታት በአደባባይ ተገርፎ በመስቀሉ ላይ እስኪሞት በነበረው ቆይታ ላይ ነው፡፡ ታላቁ አርቲስትም (ፈጣሪ) ለአፍታ የሚቆይ ደስታን ምስል ለመስራት ባሰበ ጊዜ ስራውን በወርቅ ነበር ማነፅ የፈለገው፡፡ ወርቅ ግን ሊያገኝ አልቻለም፤ አለም ላይ ያለው ወርቅ በሙሉ በዘላለማዊ  ስቃይ ቅርፅ አስቀድሞ ተሰርቶ ስለነበር፡፡ …

ግን ያንን የዘላለማዊ ስቃይ ምስል እሳት ውስጥ ከቶ አቀለጠው … ከዘላለማዊ ስቃይ ቅላጭ ወርቅ …የአፍታ ደስታን ምስል ቀረፁ፡፡ ይህም ቅርፅ ስሙ “ፍቅር” ነው፡፡ የሥራው ሂደትም ከነ አደጋው፣ በጅዝብትና ህይወት ውስጥ የሚጠቃለል ይሆናል፡፡ ተቃራኒን ከማስማማት ነው … ጥቅልነት የሚፈጠረው፡፡ ውበት የሚገኘው ከአስቀያሚነት ውስጥ ነው፡፡

***

ስለ አምስት ኪሎ አምስት ሺ ቀለም በጥቅሉ ይሄንን ብቻ ለማለት ደፈርኩ፡፡ ገፀ ባህሪዎችን ከመዘርዘር… ዝርዝሩን በጥቅል ፅንሰ ሀሳብ ባሰረው የተሻለ ስለሆነ … እነ እንቶኔ እና እንቶኒትን በተናጠል መጥቀስ አልፈለኩም፡፡ … ዋጋም የለውም፡፡ ጥበበኛውን እንደ “ሰው” እንጂ እንደ ግለሰብ ማየት ትክክል አይደለም፡፡ መጀመሪያ “ሰው መሆኑ ነው የሚያግባባን” ያለው አርቲስትም ትክክል መሆኑን ተቀብያለሁ፡፡ በጀዝብነትና ሀይማኖት “ሰው” ማለት ጥበበኛው ነው፡፡ ከሌላው አይነት ሰው የተለየ ሳይሆን በሚፈጠረው ፍቅር ልዩ መሆናችንን ለአፍታም ይሁን ለዘላለም በጥበብ ትንሽ ቀዳዳ ያሳየናል፡፡ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን አይደሉም፡፡

 

 

 

 

Read 2436 times Last modified on Saturday, 19 May 2012 10:33