Saturday, 06 October 2018 11:01

9ኛው ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

በምሥራቅ አፍሪካ በዓይነቱና በይዘቱ ልዩ የሆነው 9ኛው አዲስ ቢውልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ከመጪው ሐሙስ መስከረም 30 እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2011 በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
ኤግዚቢሽኑን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በሳፋየር ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኤግዚቢሽን፣ ኢትኤል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ከኮንስትራክሽን ሚ/ርና ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጁ ሲሆን፣ 91 ኩባንያዎች በ20 ያህል የግንባታ ግብአትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከግሪክ፣ ከኢጣሊያ፣ ከቱርክ፣ ከዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ የተውጣጡ ኩባንያዎች በኤግዚቢሽኑ እንደሚሳተፉ የጠቀሱት የኢቴኤል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሃይማኖት ተስፋዬ፣ ኩባንያዎቹ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብአት አቅርቦትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ዕድገት ላይ የደረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ 90 በመቶ ያህሉ የውጭ አገራት ኩባንያዎች ሲሆኑ 16ቱ ደግሞ ከአገር ውስጥ እንደሆኑ የጠቀሱት የኢትኤል ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ይህ በዓይነትና በይዘቱ ከፍተኛ የሆነው ኤግዚቢሽን አገራችን በዕድገት ግስጋሴ ላይ የምትገኝ መሆኗን በአካል በማየት ለመገንዘብ ያስችላል፤ ለኢንቨስትመንት መስፋፋትም መልካም ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የአገራችንን መልካም ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ግምት ይሰጠዋል ብለዋል፡፡
ኤግዚቢሽኑ፣ ለአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋናዮችና ለሌሎች አካላት የገበያ ትስስርና የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ በዓለም ላይ ኢንዱስትሪው የደረሰበትን የምጥቀት ደረጃ ለመገንዘብ ያስችላል ያሉት ወ/ሮ ሃይማኖት፤ ከሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፈጣን ዕድገትና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የመገንባት ሀገራዊ ራዕይ አንፃር፣ እየገጠመን ያለውን የጥራት፣ የዋጋ፣ የጊዜና የደህንነት ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ሰፊ የትምህርት ማዕድ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
አገራችን ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ያላትና የምርቱ ፈላጊዎችም ቢኖሩ፣ ባለሀብቶች ዘመናዊ የማምረቻ ቴክኖሎጂ ስለማይጠቀሙ፣ 82 ከመቶ የሴራሚክ ውጤቶችን የምናስገባው ከውጭ አገር ነው ያሉት በኮንስትራክሽን ሚ/ር የኮንስትራክሽን ምክር ቤትና የባለድርሻ አካላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ንጉሴ፤ 18 በመቶ የሚያመርቱ ጥቂት አምራቾች ቢኖሩም የአመራረት ዘዴው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለሆነ የምርቱ ፈላጊዎች የውጪውን ይመርጣሉ በማለት አስረድተዋል፡፡
የአቅም ግንባታ መፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት የመስሪያ ቤቱ ትኩረት በመሆኑ ከኢትኤል አድቨርታይዚንግና ኮሙኒኬሽን ጋር ተባብረን እንሰራለን ያሉት አቶ ሳሙኤል፤ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የብዙ ዓመት ልምድ ካለው የግል ድርጅት ኢትኤል ጋር መተባበር ጠቃሚ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ምን ችግር አለባቸው? እንዴት ክፍተቱን መሙላት ይቻላል? … በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የፓናል ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡   

Read 2319 times